ውጤት ለእኛ በቂ አይደለም” ይገዙ ቦጋለ /ሲዳማ ቡና/

በሲዳማ ክልል ሀለታ ጩኮ ነው ተወልዶ ያደገው፤ ወጣት ሲሆን በዋናው ስሙ መጠሪያ ደግሞ ይገዙ ቦጋለ ይባላል። በቅፅል ስሙ ደግሞ “ባ” ተብሎ ይጠራል።

ቤትኪንግ ፕሪምየር ሊጉ ስያሜውን ከማግኘቱ በፊት የሲዳማ ቡና እግር ኳስ ክለብን ከወጣት ቡድኑ አንስቶ በአጥቂ ስፍራው ላይ እያገለገለ የሚገኘው ይኸው ተጨዋች በዋናው ቡድን የእስካሁን ቆይታው በተከታታይ ዓመታቶች ላይ በመጀመሪያው ሲዝን 3 በቀጣዩ ሲዝን የሊጉ ውድድር በኮቪድ ወረርሽኝ እስከተቋረጠበት ሰዓት ድረስ 7 እና ዘንድሮ ደግሞ 5 ግቦችን በወጣትነቱ ዕድሜ በማስቆጠር አበረታች ብቃቱን እያስመለከተን ይገኛል።

ለኢትዮጵያ እድሜያቸው ከ23 ዓመት በታች ለሆናቸው ብሄራዊ ቡድን ተመርጦ በልምምድ ላይ የሚገኘውን ይህን ተስፈኛ ተጨዋች ጋዜጠኛ መሸሻ ወልዴ /G.BOYS/ በኳስ ህይወቱና በቡድኑ ሲዳማ ቡና ቆይታው እንደዚሁም ሌሎች ጥያቄዎችንም እያነሳለት የሰጠውን ምላሽ በሚከተለው መልኩ አቅርበነዋል።

ወደ እግር ኳስ ተጨዋችነት ስለመጣበት መንገድ

“መጀመሪያ እንደማንኛውም ኳስ ተጨዋች በሰፈር ደረጃ ነው በፕሮጀክት መልኩ እየሰለጠንኩ በመምጣት ኳሱን ልጀምር የቻልኩት። አሰልጣኛችንም በላይ ድጉና ይባል ነበርና እሱ ቀርፆኝም ነው ብዙ ነገሮችንም እያወቅኩኝ የመጣሁት”

በማለት ወጣቱ ተጨዋች ይገዙ ቦጋለ ስለ ኳስ አጀማመሩ ይናገራል። በልጅነት ዕድሜው የእግር ኳስ ተጨዋች የመሆን እልምና ፍላጎት እንደነበረውም ይገዙን ጠይቀነው ሲመልስ

“በፍፁም፤ በወቅቱ ኳሱን እጫወት የነበረው በአጋጣሚ እና ለስሜት እንጂ እዚህ ደረጃ ላይ እደርሳለው ብዬ አስቤ አልነበረም። እንደ አጋጣሚ ግን በችሎታዬ ላይ ዕለት ተዕለት መሻሻሎችን ስመለከት በኳሱም በጣም እየተሳብኩ መጣውና ለክለብ ተጨዋችነት ልበቃ ቻልኩ”።

በቤተሰቦቹ አካባቢ የእግር ኳስን ልጅ ሆኖ በሚጫወትበት ሰዓት ስላጋጠመው ሁኔታም ጠይቀነው

“በዛን ወቅት ላይ እኔ እንድማር እንጂ ኳስን እንድጫወት ማንም አይፈልግም ነበር፤ የሚያበረታታኝም አልነበረም። በራሴ ጥረትም ነው ለኳሱ ከነበረኝ ጥልቅ ፍቅር በመነሳት ኳስ ተጨዋችም ልሆን የቻልኩት” ብሏል።

እግር ኳስ ተጨዋች ባትሆን ኖሮስ የሚል ጥያቄን ያቀረብኩለት ይገዙ ቦጋለ ምላሹን ሲሰጥ

“እስከ 12ኛ ክፍል ድረስ ትምህርቴን ያጠናቀቅኩበት ሁኔታ ስለነበር የመንግስት ሰራተኛ ነበር የምሆነው”። ብሏል።

የሲዳማ ቡናው የአጥቂ ስፍራ ተጨዋች ይገዙ ቦጋለ ወደ ክለብ ተጨዋችነት ስለገባበት ሁኔታም ላነሳንለት ጥያቄ ምላሹን ሲሰጥ

“በእግር ኳስ ለእኔ የመጀመሪያዬ ክለብ ለሆነው የሲዳማ ቡና ቡድን ውስጥ ልገባ የቻልኩት በክልሉ ላይ ይካሄድ በነበረው የተለያዩ የሻምፒዮና ውድድሮች ላይ የእኛን ወረዳ ወክዬ በምጫወትበት ሰዓት ከዛ ላይ ተመልምዬ ነው የሲዳማ ቡና የተስፋ ቡድንን ልቀላቀል የቻልኩት። እዛም ለሁለት ዓመት ያህል ቆይታን ካደረግኩ በኋላ ወደ ዋናው ቡድን እንዳድግ ተደረግኩኝ” ብሏል።

በሲዳማ ቡና ክለብ ውስጥ ያለህ ቆይታ ምን ይመስላልም ብለን ይገዙን ጠየቅነው በሰጠን ምላሽ

“የተስፋው ላይም የዋናው ቡድን ቆይታዬ ላይም ጥሩ ጊዜን አሳልፌያለው። በተተኪው ቡድን ደረጃ እስከ ዋንጫ ድረስም ሄደን በሐዋሳ ከተማ ተሸንፈን ነው ሻምፒዮና ያልሆነው። የዋናውን ቡድን ከተቀላቀልኩበት ጊዜ ጀምሮ ደግሞ በተከታታይ ዓመታቶች ላይ ጎሎችን እያስቆጠርኩም ነውና ጥሩ የውድድር ጊዜያቶችን አሳልፌያለው። ዘንድሮ ግን ቡድናችን ያስመዘገበው ውጤት ለእኔ ብቻ ሳይሆን ለብዙዎች ከጠበቅኩት በታች ስለሆነ ያ ብቻ ደስተኛ አላደረገኝም” ብሏል።

የእግር ኳስን መጫወት ሲጀምር ለእሱ አርአያና ሞዴሉም ስለነበረው ተጨዋች ጠይቀነውም ሲመልስ

“የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን አጥቂ ሳላህዲን ሰይድ ለእኔ የሁልጊዜም ምርጡና የማደንቀው ተጨዋች ነው። እሱን ተምሳሌቴ አድርጌም ነበር በአጥቂው ስፍራ ላይ ስጫወት የነበርኩት። ከባህርማዶ ተጨዋቾች ደግሞ የማንቸስተር ዩናይትድም ደጋፊ ነኝና የራሽፎርድም አድናቂ ነኝ” ብሏል።

በቤትኪንግ ፕሪምየር ሊግ ሲዳማ ቡና ዘንድሮ ስለነበረው ተሳትፎም ይገዙ ይናገራል።

“በዘንድሮ የውድድር ዘመን ተሳትፎአችን ምንም እንኳን ወደ መጨረሻዎቹ ጨዋታዎቻችን አካባቢ መሻሻሎች ቢኖሩም እንደ አጠቃላይ የቡድኑን የውድድር ዘመን ስንመለከተው ግን ከሌላው ጊዜ አንፃር ውጤታችን በተለያዩ ምክንያቶች ተበላሽቷል። ያልተጠበቀ ውጤትንም ነበር ያስመዘገብነው። የእዚህ ቡድን አጀማመርም ነበር ብዙ ነገሮችን ሊያመሰቃቅልብንም የቻለው። አዲስ አሰልጣኝ ወደ ቡድኑ ከመጣ በኋላ ግን ብዙ ነገሮች ተቀይረዋልና ይሄን አጠናክረን በማስጓዝ ጠንካራውን ሲዳማ ቡና ክለብ ዳግም ልንመልሰው ይገባል”።

ቤትኪንግ ፕሪምየር ሊግ በዲ ኤስ ቲቪ መተላለፉን ባወቅክበት ወቅት ምን አልክ የሚል ጥያቄንም ለይገዙ አነሳውለት እሱም ይህን ምላሽ ሰጠኝ

“የውድድሩ ጨዋታዎች የቀጥታ ስርጭትን አግኝተው በዲ ኤስ ቲቪ ለመተላለፍ መቻላቸው እንደ ሀገርም ሆነ ለእኛ ተጨዋቾች ወደ ተለያዩ ሀገራት በፕሮፌሽናል ተጨዋችነት ወጥቶ ለመጫወት በጣም ይጠቅማል። ይኸውም ከዚህ በፊት በነበረው የሊግ ውድድር ወደ ውጪ ሀገር ወጥተህ ለመጫወት ቪዲዮችን አታገኝም። ብታገኝም ጥራት የለውም። አንተነትህንም በደንብ አያሳውቅምና የምትቸገርበት ሁኔታ አለ። አሁን ግን እያንዳንዱ ጨዋታ ጥራት ባለው መልኩ ስለሚቀረፅና ፊልሙንም ማግኘት ስለምትችል። ከዛ ውጪም ደግሞ ፊልሙን ደግመህ እየተመለከትክም ራስህንም የምታሻሽልበት ሁኔታዎችም ስላሉ አንተ ጠንክረ እና ጥሩ ስራ ስራ እንጂ የተሻለ ደረጃ ላይ መድረስህ አይቀርምና ጨዋታዎቹ መተላለፍ መቻላቸው ትልቅ ጠቀሜታ ነው ያለው”።

በቤትኪንግ ፕሪምየር ሊጉ ለቡድንህ ዘንድሮ ያስቆጠርካቸው ግቦች በቂ ነው ብለህ ታስባለህ ብለንም ለይገዙ ጠየቅነው በዚህ ዙሪያ ሲመልስ

“በፍፁም፤ በጉዳት መጀመሪያ አካባቢ ብዙ ጨዋታዎች አመለጡኝ እንጂ ከዛ በላይ ግቦችንም አስቆጥር ነበር። አሁን ያገባዋቸው ግቦች ሊጉ ሊያልቅ አካባቢ ያሉ ናቸው። በቀጣዩ ዓመት ላይ ግን ብዙ ጎል አስቆጥሬ ከፈጣሪ እርዳታና እገዛ ጋር ለኮከብ ግብ አግቢነት እፎካከራለው”።

የቤትኪንግ ፕሪምየር ሊጉን ፋሲል ከነማ ኮከብ ተጨዋችነቱን ደግሞ የኢትዮጵያ ቡናው አቡበከር ናስር ሊወስዱት ችለዋል፤ በዚህ ዙሪያ የአንተ ምላሽ ምን ሊሆን ይችላል የሚል ጥያቄን ያቀረብንለት የሲዳማ ቡናው ተጨዋች ሲመልስ

“ፋሲል ከነማ የሊጉን ዋንጫ ያነሳው ስለለፋና ጥሩም ቡድን ስለነበር ነው። ሁሉንም በማሳመንም ነው ድሉን የተቀዳጀው። አቡበከርን በተመለከተ ደግሞ ስለ እሱ እንዲህ ነህ ብለህ የምትለው ተጨዋች አይደለም። በጥሩ ብቃት ላይ የሚገኝና ለታዳጊ ተጨዋቾችም አርአያ የሆነ ተጨዋች ነው። እሱን በታላቅ የውድድር መድረክ ላይ እመለከተዋለውም ብዬ ተስፋን አደርጋለውና ፋሲል ከነማም ሆነ አቡኪ ያገኙት ስኬት የሚገባቸውም ነው” ብሏል።

ከእግር ኳስ ውጪ መዝናኛው ስለሆነው ነገርም ሲናገር

“ከኳስ ውጪ ፊልም ማየት ደስ ይለኛል። ኮሜዲ ፊልሞችም ምርጫዎቼም ናቸው” በማለት ይናገራል።

በቡድናቸው ውስጥ ስለሚያዝናናቸውም ኮሜዲ ተጨዋች ጠይቀነው

“እሱማ አበባየው ዩሃንስ ነው። ቀልድ ይችላል። በጣም ያስቀናልም” ብሏል።

ስለ ምግብ መጠጥ እና የሙዚቃ ምርጫውም የተጠየቀው ይኸው ተጨዋች ምላሹን ሲሰጥም

“እንጀራ በምስር ወጥን ከምግብ ውሃን ከመጠጥ ስወድ ከሙዚቃ ደግሞ ስለማላዳምጥ ምርጫ የለኝም። የእኔ ምርጫ መዝሙርን ማድመጥ ነው”።

“ባ” ተብለህ እንደምትጠራ ሰማን ምን ማለት ነው ማንስ ነው ይህን ስም ያወጣልህ? ለምንስ ወጣልህም አልነው እሱም ሲመልስ

“እንደ ማንቸስተር ዩናይትድ ደጋፊነቴ በአንድ ወቅት ማንቸስተር ከቼልሲ ጋር ጨዋታቸውን ያደርጉና የቼልሲው ዴምባባ በመቀስ ምት ጎል ያስቆጥራል። ያን ብዙዎች ተመልክተው ነበርና እኔም በነጋታው በፕሮጀክት ደረጃ ስጫወት በዛ መልኩ በፎርቢች ጎል ሳስቆጥር ዘሪሁን በላይ /ጊምቦ/ የተባለ ጓደኛዬ ነው ዴምባባ ከሚለው ስም ተነስቶ በማሳጠር በመጨረሻዋ ፊደል ባ ብሎኝ ሊጠራኝና በዛም ስም እንድታወቅበት ያደረገኝ”።

ለብሔራዊ ቡድን የመመረጥ ዕድሉን አግኝተሃልና ምን አይነት ስሜት ተሰማህም አልነው እሱም ሲመልስ

“የእውነት በጣም ነው ደስ ያለኝ። ቡድኑን ስቀላቀልም ብዙ ትምህርትንም ነው ያገኘሁት። በተለይም ደግሞ አሰልጣኛችን ውበቱ አባተ ከሚሰጠን ጥሩ ልምምድ በተጨማሪ ለወደፊቱ የኳስ ህይወትህም ምን ምን ነገሮችን ማድረግ እንደሚጠበቅብክም የሚያስተላልፍልህ ቁም ነገሮችም አሉና ያ አንተን ተጠቃሚ ነው የሚያደርግህም” ብሏል።

በእግር ኳስ የወደፊት ግብህ የት ድረስም ነው አልነው

“በመጀመሪያ እንደማንኛውም የእግር ኳስ ተጨዋች ሀገሬን ወክዬ መጫወት እፈልጋለው። አሁን ቅድሚያ ለተመረጥኩበት የ23 ዓመት በታች ቡድን ጥሩ ነገሮችን ስለመስራት እያሰብኩ ነው። ከዛ ለዋናው ቡድን ተጠርቼ የሀገሬን ስም ማስጠራትና ከሀገር ወጥቶም መጫወት እልሜ ስለሆነ እነዛን ለማሳካት ጠንክሬ እሰራለው። ከዛ ዉጪም ሲዳማ ቡና በቤትኪንግ ፕሪምየር ሊጉ መሻሻል ያመጣው ወደ መጨረሻዎቹ ጨዋታዎች አካባቢም ነውና የመጪው ዓመት ላይ ጠንካራ ቡድንን ፈጥረን በጥሩ ቡድንነቱ የሚታወቀውን ቡድን ልናስመለክት ይገባል” ብሏል።

በእግር ኳስ ተጨዋችነትህ ማሻሻል ያለብህም አልነው

“አንድአንዴ በአጨራረስ ላይ ያለብኝን ችግር መቅረፍ አለብኝ። ይሄ ደግሞ በመጪው ዓመት ላይ የሚቀረፍ ይሆናል” ብሏል።

ከሲዳማው ቡና ይገዙ ቦጋለ ጋር ከመለያየታችን በፊት ማመስገን ወይንም ደግሞ ማለት ስለሚፈልገው ነገር ዕድል ሰጠነውና ሀሳቡን በዚህ መልኩ አጠቃለለው

“በእግር ኳሱ ለትልቅ ደረጃ እንደምበቃ አውቃለው። ይህን ካልኩ በእስካሁን የኳስ ህይወቴ ከእኔ ጎን ሆነው ሲያግዙኝ የነበሩትን ቅድሚያ ፈጣሪዬን በመቀጠል ደግሞ ቤተሰቦቼን በተለይ እናቴን አሰልጣኝ ዘርዐይ ሙሉን መኔግስቱ ሳሳሞን የሲዳማ ቡና ደጋፊዎችንና ሌሎችም ስማችሁን ያልጠቀስኳችሁን ሁሉ አመሰግናለው”።

Editor at Hatricksport website

Facebook

መሸሻ ወልዴ

Editor at Hatricksport website