መከላከያ በአሰልጣኝ ዩሃንስ ሳህሌና በረዳቱ ዮርዳኖስ አባይ እየተመራ ቤትኪንግ ፕሪምየር ሊጉን ዳግም ሊቀላቀል ችሏል።
በኢትዮጵያ እግር ኳስ ታሪክ ውስጥ ይህ ትልቅ ስም ያለው ቡድን ከወረደበት ከፍተኛው ሊግ ወደ ቤትኪንግ ፕሪምየር ሊግ ማለፉን አስመልክተን ከቡድኑ ካፒቴን በሀይሉ ግርማ/ባባ ጋር ጋዜጠኛ መሸሻ ወልዴ /G.BOYS/ ቆይታን አድርጎ የሚከተለውን ምልልስ ይዘው ቀርበዋል።
ሀትሪክ፦ መከላከያ ከወረደበት ሊግ በመምጣት ቤትኪንጉን ዳግም ተቀላቅሏል፤ ለእዚህ ውጤት እንዴት ልትበቁ ቻላችሁ?
በሀይሉ፦ የፕሪምየር ሊጉን ውድድር ዘንድሮ ልንቀላቀል የቻልነው በዓመታዊው የከፍተኛው ሊግ ተሳትፎአችን ሁላችንም ተጨዋቾች ተዋደን ተፋቅረንና ህብረታችንም ልዩ ሆኖ ልንቀርብ ስለቻልንና በአሰልጣኞቻችንም የሚሰጠንን ስልጠና በአግባቡ ልንሰራም ስለቻልን ነው።
ሀትሪክ፦ መከላከያ ወደ ቤትኪንግ ፕሪምየር ሊግ ማለፉ ይገባዋል?
በሀይሉ፦ አዎን። ከበቂ በላይም መቶ ፐርሰንት ነው የሚገባን የውድድሩ አዘጋጅ አካልና ሌሎችም በመሰከሩልንና ባመኑበት ሁኔታም ነው ሊጉን በድጋሚ የተቀላቀልነው።
ሀትሪክ፦ ወደ ታችኛው ሊግ ወርዶ መጫወት ስሜቱ ምን ይመስላል?
በሀይሉ፦ ከባድ ነው። በተለይ ደግሞ መከላከያን የመሰለ ትልቅ ቡድን በዛ ደረጃ ላይ ወርዶ ሲጫወት ስታይ ታዝናለህም። በዚህ ቡድን ውስጥ ወርደው ከተጫወቱት ተጨዋቾች መካከልም ሶስትና አራት ተጨዋቾች ብቻም ነበር የተጫወትነው። በጊዜው ከባድ ጊዜንም ነበር ያሳለፍነው። ያም ሆኖ ግን በቁጭት ስሜት ላይ ሆነን ከአዲሱ የቡድኑ ተጨዋቾች ጋር በመጫወት ቡድኑን አሳልፈናልና ያ አስደሳች ነው የሆነልን”።
ሀትሪክ፦ በከፍተኛ ሊጉ ፈታኝ የነበረባችሁ ጨዋታ የቱ ነው?
በሀይሉ፦ ከባዱና ያስቸገረን ግጥሚያ በሁለተኛው ዙር የመጀመሪያ ጨዋታችን ላይ ከኢትዮ-ኤሌክትሪክ ጋር አድርገን የነበረው ፍልሚያ ነው። ምክንያቱም የመጀመሪያው ዙር ጨዋታ ሲጠናቀቅ እነሱ በአንድ ነጥብ ይበልጡን ነበር። ቢያሸንፉን ልዩነቱን ወደ አራት ይወስዱት ነበር። ያም ሆኖ ግን አስቸጋሪውን ጨዋታ 1-0 ስላሸነፍንና በሁለት ነጥብም ልንበልጣቸው ስለቻልን ያ ግጥሚያ ወደ ሻምፒዮናነት እንድናመራ ትልቅ አስተዋፅኦ አበርክቶልናል። ሌላው ለእኛ ፈታኝ የነበረው ጨዋታ በነጥብ ይቀራረበን ከነበረው ደሴ ከተማ ጋር ያደረግነው ጨዋታም ነበርና በዛ ጨዋታ ውጤት ማምጣታችን እነሱንም እንዲቆሙ አድርገናል።
ሀትሪክ፦ መከላከያ ሊጉን ሲቀላቀል በቡድኑ ውስጥ የተፈጠረው ስሜት ምን ይመስል ነበር?
በሀይሉ፦ ስሜቱ በጣም ከባድና ደስ የሚል ነው። ወደ ሊጉ በመግባትና ባለመግባት ሁኔታዎች ላይ ሁሉም ሲጨነቅም ነበር። በኋላም ላይ የመከላከያ ወርዶ መጫወት የማይመጥነው ስለሆነም ዓመቱን ሙሉ ለፍተን በመጫወታችን ነው ሊጉን የተቀላቀልነው። ለዚህ እንድንበቃ ደግሞ የአሰልጣኞቹ የተጨዋቾቹ የአመራሮቹና የደጋፊዎቻችንም የጋራ ስራ ነውና ሁሉም በዚህ አጋጣሚ ሊመሰገን ይገባል።
ሀትሪክ፦ መከላከያ ሲወርድ ነበርክ አሁን ሲያልፍም አለህ። በዚህ ዙሪያ ምን ትላለህ?
በሀይሉ፦ ቡድኑ ሲወርድ አዝኜ ነበር። አሁን ደግሞ ካፒቴን ሆኜ ወደ ነበርንበት ሊግ እንድንመለስ አድርጌያለው። ሌላው የእዚሁ ቡድን አካልና ጎደኛዬ ቴዎድሮስም እንደ እኔው ነበርና በሁለታችንም ውስጥ የነበረው የደስታ ስሜትም ጥልቅ ነበር።

ሀትሪክ፦ ባሳለፍከው የእስካሁን የኳስ ህይወት ደስተኛ ነህ? ከዚህ በኋላስ
በሀይሉ፦ በጣም ደስተኛ ነኝ። ለሙገርና ለመከላከያ ቡድኖችም ነው ኳስን የተጫወትኩት። ከዚህ በፊት በታችኛው ሊግ ደረጃ ወርጄ አልተጫወትኩም ነበር። አሁን ብጫወትም መልሼ ክለቤን ወደነበረበት ሊግ ላይ ስለመለስኩት ተደስቺለው።
ሀትሪክ፦ በእግር ኳስ ቆይታህ ምን ተማርክ?
በሀይሉ፦ ብዙ ነገሮችን። በተለይ መዘናጋቶች ብዙ ነገሮች ናቸው የሚያሳጡህ። ስለዚህም ሁሌ ለዋንጫ ስለመጫወት ማሰብ እንዳለብህ ካወቅህ ያን እልም ልታሳካ ትችላለህና የመጪው ዓመት ላይ መከላከያ በዛ መልኩ ይጫወታል።
ሀትሪክ፦ በመጨረሻ
በሀይሉ፦ መከላከያ ወደ ፕሪምየር ሊጉ በማለፉ በጣም ተደስቻለው። ጥሩ ጊዜን አሳልፈን ነበር። በዚህ ጊዜ ውስጥም ከእኔ ጎን ሆነው ላበረታቱኝና ሁሌም ከኘጠገቤ ለማይጠፉት ቤተሰቦቼ ወንድሞቼ የልጄ ናታን እናት ሜሮን ማንደፍሮንና የቡድን ጎደኞቼን በአጠቃላይ የመከላከያ አባላቶችንና አመራሩን ማመስገን እፈልጋለው።
አስተያየት ይስጡ