ሁለተኛ ቀኑን በያዘው የይበልጣል ኤልያስ ገቢ ማሰባሰቢያ ፕሮግራም ቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ተካፋይ የሆኑትን ወላይታ ዲቻን እና አርባ ምንጭ ከተማን ያገናኘው ጨዋታ በአንድ አቻ ውጤት ተጠናቋል።
በጨዋታ መሐል በርካታ ሰዎች የገንዘብ ድጋፍ ያደረጉ ሲሆን ከእነዚህ መሐል የቀድሞ የወላይታ ቱሳ ተጫዋቾች የነበረው እንዲሁም 1998 የውድድር አመት በኢትዮጵያ ጥሎ ማለፍ ሻምፒዮና የውድድሩ ኮከብ ተጫዋች የነበረው ሙሴ ጳውሎስ አንድ መቶ ሺህ ብር ለይበልጣል ኤልያስ ድጋፍ አድርጓል።
በሌላ በኩል የኢኮኖሚ ባለሙያ እና ለብዙ ድርጅቶች አማካሪ በመሆን እየሰራ ያለው ሀሮን ጋንታ ሰላሳ ሺህ ብር ድጋፍ አድርጓል።የወላይታ ደጋፊዎች ማህበር እና ተጓዥ ደጋፊዎች አምስት ሺህ ብር ድጋፍ አድርገዋል።ድጋፉ ቀጥሎም በርካታ ግለሰቦች ቃል ገብተዋል።
በጨዋታው የእረፍት ሰዓት ላይ ንግግር ያደረገው ይበልጣል ህዝቡ እያደረገለት ላለው ድጋፍ በማመስገን በጣም በአጭር ጊዜ ወደ ዋናው የባርሴሎና ቡድን አድጎ እንደሚያኮራቸውም ቃል ገብቷል።
በመጨረሻም በነገው እለት የዞኑ ከፍተኛ አመራሮችን ጨምሮ በርካታ ባለሃብቶች የሚሳተፉበት የእራት ግብዣ በጉተራ አዳራሽ ይደረጋል።የደቡብ ብሔር ብሔረሶች እና ህዝቦች ክልልም ለይበልጣል ኤልያስ ክልሉን የሚመጥን ድጋፍ እንደሚያደርጉለትም ለማወቅ ችለናል።
ሀትሪክ ስፖርትም ለታዳጊው ይበልጣል ኤልያስ መልካም እድልን ትመኛለች።
አስተያየት ይስጡ