” ለዋልያዎቹ የዘጠኝ ሚሊዮን ብር ሽልማት ተዘጋጅቷል ” አቶ ኢሳያስ ጅራ
የዋልያዎቹ የሽኝት ፕሮግራም ትላንት ምሽት በስካይ ላይት ሆቴል ትልልቅ የመንግስት ባለስልጣናት ፣ የኪነጥበብ ባለሙያዎች ፣ የእግርኳሱ ባለሙያዎች እንዲሁም ጥሪ የተደረገላቸዉ ዕንግዶች በተገኙበት ተካሂዷል።
አመሻሽ 1 ሰዓት ገደማ ፕሮግራሙ ከመጀመሩ አስቀድሞ ዋልያዎቹ በሀገር ባህል ልብስ አጊጠዉ ወደ ስፍራዉ ሲደርሱ በአዳራሹ ከታደሙት እንግዶች ለየት ያለ አቀባበል የተደረገላቸዉ ሲሆን ፤ የዋልያዎቹን መድረስ ተከትሎ የኢትዮጵያ ህዝብ መዝሙር በጋራ ተዘምሮ ፕሮግራሙ በይፋ ተጀምሯል።

በፕሮግራሙ መጀመሪያ ላይ ንግግር ያደረጉት የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌደሬሽን ፕሬዚዳንት ኢሳያስ ጅራ ካነሷቸዉ ነጥቦች መካከልም :- ይህ የብሔራዊ ቡድኑ ዉጤት በቀላሉ እንዳልመጣ ቡዙ ዉጣ ዉረዶች እንደታዩበት እና ይሄንን ተቋቁመው ለዉጤት እንዲበቁ የበኩላቸውን ለተወጡት የአመራር አካላት ምስጋናቸውን አቅርበዋል።
ከዚህ በመቀጠልም ለብሔራዊ ቡድኑ አጠቃላይ ዝግጅት መንግስትን ሚሊየን ብር ጠይቀዉ የነበረ ቢሆንም 35 ሚሊዮን እንደተፈቀደላቸዉ የገለፁ ሲሆን ለዚህም ሀገሪቱ ካለችበት ወቅታዊ ሁኔታ አንፃር መንግስትን እንደሚያመሰግኑ ገልጸዋል።

ከዚህ ጋር ተያይዞም የብሔራዊ ቡድኑን ዝግጅት ከካሜሩን ይልቅ በሳውድአረቢያ ለማድረግ ታስቦ የነበረ ቢሆንም በሳውዲ የኮቪድ በረራ ክልከላ ምክንያት መቅረቱን የፌዴሬሽኑ ፕሬዝዳንት አቶ ኢሳያስ አሳዉቀዋል።
በመቀጠልም በEY production የተዘጋጀውን እና የ45 ደቂቃ ያክል ቆይታ ያለዉ የዋልያዎቹ አሻራ የሚል ዘጋቢ ፊልም በስፍራው ለነበሩት እንግዶች ለእይታ የበቃ ሲሆን ፤ ይህ ዘጋቢ ፊልምም በቅርቡ በተመረጡ የቴሌቪዥን ጣቢያዎች ላይ ለእይታ እንደሚበቃ ተገልጿል።
በተጨማሪም በስፍራው ይገኝ የነበረዉ የክብር ዕንግዳዉ አርቲስት እና ጋዜጠኛ ታማኝ በየነም ካደረገዉ የማነቃቂያ ንግግር መካከልም ”ለሀገራችሁ እናንተም ወታደሮች ናችሁ” የሚለው በዋናነት ይገኝበታል።
በስራ ምክንያት በፕሮግራሙ ላይ መገኘት ያልቻሉት የኢፌዴሪ ፕሬዝዳንት ክብርት ሳህለወርቅ ዘውዴ ለዋልያዎቹ ያላቸዉን መልዕክት በቪዲዮ ያስተላለፉ ሲሆን በመልዕክታቸውም :-” በርቱ! የኢትዮጵያ ህዝብ ከእናንተ ጋር ነው ሀገራችንን ለዚህ መድረክ ስላበቃችኋት ምስጋናዬን አቀርባለሁ ብለዋል ።

ከዚህ በተጨማሪም ፌዴሬሽኑ ለአጋሮቹ እና ለመንግስት የማስታወሻ ስጦታዎችን አበርክቷል።
በመቀጠልም በካሜሩን የአፍሪካ ዋንጫ ላይ የሚሳተፈው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ዋና አሠልጣኝ ውበቱ አባተ እና አምበሉ ጌታነህ ከበደ ከቡድን መሪው አቶ አበበ ገላጋይ ጋር በመሆን የኢትዮጵያን ሰንደቅ ዓላማ ከስፖርት እና ባህል ሚኒስትር ክቡር ቀጀላ መርጋሳ እና የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ፕሬዘዳንት አቶ ኢሳይያስ ጂራ ተረክበዋል።


በስፍራው ይገኙ የነበሩት ታላላቅ የመንግስት የስራ ሀላፊዎች ለዋልያዎቹ የመልካም ምኞት መልዕክት ካስተላለፋ በኋላም የፕሮግራሙ መዝጊያ በነበረው የኬክ ቆረሳ ወቅት የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌደሬሽን ፕሬዚዳንት አቶ ኢሳያስ ጅራ ብሔራዊ ቡድኑ ከምድቡ የሚያልፍ ከሆነ የዘጠኝ ሚሊየን ብር ሽልማት እንደሚያበረክቱ ገልጸው የምሽቱ የሽኝት ፕሮገራምም በዚሁ ተገባዷል።

አስተያየት ይስጡ