በሀዋሳ እየደተረገ በሚገኘው የኢትዮጵያ ከ20 ዓመት በታች ፕሪምየር ሊግ ማጠቃለያ ውድድር ላይ በማጣሪያው ሲሳተፉ የቆዩ ክለቦችን ክፉኛ ያስቆጣው ጉዳይ።

የኢትዮጵያ ከ20 አመት በታች ፕሪምየር ሊግ የማጠቃለያ ውድድር በሀዋሳ በያዝነው ሳምንት መጀመር የቻለ ሲሆን የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌድሬሽን ግን አቃቂ ቃሊቲ እና ሆሊ ቪዢን የተባሉ ሁለት ቡድኖችን አመት ሙሉ በነበረው በመደበኛው የፕሪምየር ሊጉ የምድብ ማጣሪያ ጨዋታዎች ላይ ምንም አይነት ተሳትፎን ሳያደርጉ በቀጥታ ወደ ማጠቃለያ ውድድሩ እንዲገቡ መደረጉ ከፍተኛ መነጋጋሪ ሆኗል።
ከዚህ ቀደም ፌዴሬሽኑ ከሁለቱም ምድብ ከአንድ እስከ አምስት ሆነው የጨረሱ በድምሩ 10 ቡድኖች ወደ ማጠቃለያ አልፋችዋል በሚል ዝርዝራቸውን ይፋ አድርጎ በሁለት ምድብ ውድድሩ ይደረጋል ተብሎ ቢጠበቅም የምድብ ድልድሉ በሦስት ምድብ ተከፍሎ የተሳታፊ ቁጥር በድንገት ወደ አስራ ሁለት አድጎ ውድድሩ በሀዋሳ እየተደረገ መሆኑ ክለቦችን በእጅጉ አስቆጥቷል።
ይህ ያልተጠበቀ የፌዴሬሽኑ አሰራር የውድድሩን ህግና መመሪያ የሚጥስ ፣ የስፖርቱን ፍትሀዊነት የሚያዛባ እና የኢትዮጵያ እግር ኳስ ያለበትን ስር የሰደደ የአስተዳደር ችግር ፍንትው አድርጎ የሚያሳይ ነው በሚል፣ በውድድር ዓመቱ ከፍተኛ ልፋትና ወጪ አውጥተው ወደ ማጠቃለያው ላለፉት ክለቦች ከፍተኛ ቅሬታን ፈጥሯል።
በተለይም በዕጣ ማውጣቱ ስነ-ስርዓት ላይ ከተለያዩ የክለብ ተወካዮች በኩል እነዚህ ቡድኖች እንዴት ወደ ውድድሩ ሊገቡ ቻሉ የሚሉ ጠንካራ ጥያቄዎችና ተቃውሞም ቢቀርብም ፌድሬሽኑ ግን በራሱ ውሳኔ ውድድሩን ማድረግን ቀጥሏል።
ሆኖም ከፌዴሬሽኑ አመራሮች በኩል ለቀረቡት ጥያቄዎች ምንም አይነት ማብራሪያና ምላሽ ሳይሰጥ መታለፉ የክለቦቹን ቁጣ ይበልጥ ያባባሰው ሲሆን ፣ ምንም አይነት የማጣሪያ ጨዋታ ያላደረጉት እነዚህ ቡድኖች በማጠቃለያው ውድድር ውስጥ ተካትተው ውድድር መጀመራቸውም ከፍተኛ ውጥረት እንዲፈጠር ምክንያት ሆኗል።
አስተያየት ይስጡ