ምድረገነት ሽረ ፣ ወልዋሎ እና መድን ተጫዋች አስፈርመዋል።
በአሰልጣኝ ግርማ ታደሠ የሚመራው ወልዋሎ አዲግራት ዩኒቨርሲቲ ሰሞኑን ይነሳበት የነበረውን የደመወዝ ክፍያ በማስተካከል የቡድኑ ሙሉ አባላት ወደ ልምምድ የገቡ ሲሆን በዛሬው ዕለት የቀድሞው የአርባምንጭ ከተማ ፣ ኦሜድላ እና ደብደረብርሀን ከተማ የመስመር አጥቂ ተመስገን መንገሻን ከሲዳማ ቡና እስከ ውድድር ዘመኑ ፍፃሜ በውሰት አስፈርሟል። ይህ ተጫዋች በመጀመሪያው ዙር የፕሪምየር ሊጉ ጨዋታ ሲዳማ ቡና ወልዋሎን 4ለ1 ሲረታ ጎል ማስቆጠሩ የሚታወስ ሲሆን ከጌቱ ሀይለማርያም ቀጥሎ የክለቡ ሁለተኛ ፈራሚ ሆኗል።
ሽረ ምድረገነት የመሐል ተከላዩ ደሳለኝ ከተማን የግሉ አድርጓል። የቀድሞው የደብረብርሃን ከተማ እና በመቻል ቤት ደግሞ ላለፉት ሦስት አመታት ያሳለፈ ሲሆን ከመቻል ጋር በመለያየት ማረፊያው የአሰልጣኝ ዳንኤል ፀሐዬው ክለብ ሆኗል።
ኢትዮጵያ መድን አልፍሬድ ኑኩሩንዚዛ የተባለን ብሩንዳዊ የመስመር አጥቂ የግሉ አድርጓል። በሁለት አጋጣሚዎች ለሀገሩ ቡማሙሩ ክለብ የተጫወተው እና ለሌላኛው ኤጂል ኖይር ክለብ ቆይታን ማድረግ የቻለው የ23 ዓመት አጥቂ ሳሙኤል ሳሊሶን ካስፈረመ በኋላ ለመድን ሁለተኛው የአጋማሹ ፈራሚ ሆኗል።


