ወደ ግብፅ ሊጓዝ ተቃርቦ የነበረው አጥቂ ወደ ኢትዮጵያ መድን ሊያመራ ሲቃረብ ጋናዊው አማካይ በበኩሉ በጉዳት ክለቡን ለቋል።
ያለፈውን አንድ አመት የልጅነት ክለቡ ወላይታ ድቻን በመልቀቅ በቅዱስ ጊዮርጊስ መለያ በፕሪምየር ሊጉ ስንመለከተው የነበረው አጥቂው ቢንያም ፍቅሩ በአሰልጣኝ ገብረመድህን ሐይሌ ለሚሰለጥነው ኢትዮጵያ መድን እስከ ውድድር ዘመኑ መባቻ ድረስ ለመጫወት ስምምነት ላይ መድረሱን ያገኘውት መረጃ ጠቁሞኛል። ከወላይታ ድቻ ወጣት ቡድን ከተገኘ በኋላ አራት የውድድር ዘመናትን ከዋናው ቡድን ጋር አሳልፎ በመጨረሻም ወደ ግብፅ ተጉዞ በድጋሚ ወደ ሀገር ቤት ተመልሶ ከቅዱስ ጊዮርጊስ ጋር ያለፉትን አንድ አመት ከግማሽ ያህሉን አሳልፏል።
ከፈረሰኞቹ ጋር ቀሪ የስድስት ወራት ውል እየቀረው እስከ አሁን መልቀቂያ መውሰድ ብቻ የቀረው አጥቂው ወደ ግብፅ ሊያመራ ከጫፍ የደረሰ መስሎ የነበረ ቢሆንም የሀገሪቷ የዝውውር መስኮቱ መዘጋቱን ተከትሎ የአሰልጣኝ ገብረመድህን ሐይሌውን ኢትዮጵያ መድንን ሊቀላቀል ስለመሆኑ አረጋግጫለሁ።
ኢትዮጵያ መድን ከቀድሞው የሀዋሳ ከተማ አማካይ ጋናዊው ሚሼል ኡቱሉ ጋር በጉዳት ምክንያት ተለያይቷል።


