ለሁለት ክለብ በመፈረማቸው መነጋገሪያ የነበሩ ሁለት ተጫዋቾች ጉዳይን በመረጃችን ይዘናል።

ለ2019 የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ በክረምቱ ከተደረጉ ዝውውሮች መካከል መነጋገሪያ የነበረው ለመቻል እና ለኢትዮጵያ ቡና የፈረሙት የአማካይ ስፍራ ተጫዋቹ አብዱልከሪም ወርቁ እና የቀኝ መስመር ተከላካዩ አለምብርሀን ይግዛው ጉዳይ በዋናነት ይጠቀሳል። ዝውውሩ በይፋ ከመከፈቱ አስቀድሞ በመቻል የነበራቸውን ውል በመፈፀማቸው ለኢትዮጵያ ቡና የሁለት አመት ውል መፈረም የቻሉት ሁለቱ ተጫዋቾች ከቀናቶች በኋላ ደግሞ በመቻል ለመቆየት ስምምነት መፈፀም ችለዋል። በተለያየ ቀናት ለሁለት ክለብ የፈረሙት እና ያስፈረሟቸው ሁለቱም ክለቦች በተለያየ ቀናት ወደ ኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌድሬሽን አምርተው የዝውውር ቀኑ ባይከፈትም ለማሳወቅ በሚል ባመሩበት ወቅት ሁለቱም ተጫዋቾች ለሁለት ክለብ መፈረማቸው ይረጋገጣል። ጉዳዩን የተመለከተው ፌድሬሽኑ ተስማምታችሁ ውሳኔያችሁን አሳውቁን በሚል በሰዓቱ መግለፅ ቢችልም ሁለቱም ክለቦች ግን መስማማት ሳይችሉ በመቅረታቸው በመጨረሻም ተጫዋቾቹ ለሁለት አመታት ቅጣት ሊጣልባቸው መሆኑን አረጋግጫለሁ።
ተጫዋቾቹ በማንአለብኝነት ለሁለት ክለብ መፈረማቸው የተጫዋቾቹን ታማኝነት ያጠለሸ መሆኑ በብዙሀኑ ዘንድ የማይካድ ሀቅ ቢሆንም የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌድሬሽን በአንፃሩ በየክለቡ ቢሮ እና በክልል እግር ኳስ ፌድሬሽኖች ውስጥ የሚፈፀሙ ዝውውሮችን አልቀበል በእኔ ፅህፈት ቤት የሚፈፀምን ዝውውር ብቻ ነው የማፀድቀው የሚል ህግ ቢያወጣም ከዝውውር ቀነ ገደቡ መከፈት በፊት በተፈፀመ ጉዳይ ሁለቱን ተጫዋቾች ሊቀጣቸው ከጫፍ ደርሷል።
የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌድሬሽን ተስማሙና ወደ እኔ ቅረቡ የሚል ትዕዛዝን በማስተላለፉ ሁለቱም ተጫዋቾች አንድ አንድ ተካፈሉን ካልሆነ ደግሞ ወደ ሌላ ክለብ ሄደን እንድንጫወት ፍቀዱልን ብለው ደጋግመው ቢጠይቁም በተለይ በክለቦቹ አሰልጣኞች መካከል ያለው ቁርሾ ችግሩን በይበልጥ ከፍ እንዳደረገው ሀትሪክ ስፖርት አረጋግጧል። የኢትዮጵያ ቡና የእኔ ንብረት ናችሁ እና ወደ ልምምድ ግቡ በሚል ደብዳቤን ጭምር ለተጫዋቾቹ ያቀረበ ቢሆንም ሁለቱም ተጫዋቾች ከየትኛውም ክለብ ጋር ልምምድ እየሰሩ አይገኝም። ስለሆነም በያዝነው ሳምንት የሀገሪቱ የእግር ኳስ የበላይ አካል በተጫዋቾቹ ላይ የቅጣት በትርን ሊያሳርፍ መቃረቡን ሰምቻለሁ።
አስተያየት ይስጡ