“ከበፊትም ጀምሮ ቅዱስ ጊዮርጊስን ማሸነፍ ያስደስተኛል” ምንተስኖት ከበደ /አፍሪካ/ (ኢት.ቡና)

“ለኢትዮጵያ ቡና ስትጫወት የማሊያው ክብር ከነፍስህ እኩል ዋጋ እንዳለው ልታውቅ ይገባል”

“ከበፊትም ጀምሮ ቅዱስ ጊዮርጊስን ማሸነፍ ያስደስተኛል”

ምንተስኖት ከበደ /አፍሪካ/ (ኢት.ቡና)

አፍሪካ የሚለው መጠሪያ ከመታወቂያ ስሙ የበለጠ ይታወቃል፤ በቃ ድንገት አንድ ቀን የደደቢቱ መስራችና ፕሬዚዳንት ኮ/ል አወል አብዱራሂም ጥቁረቱን ያዩና አንተ አፍሪካዊ ነህ ሲሉ አፍሪካ ብለው ይጠሩታል፡፡ “ሰብሮም” የሚለውን ስያሜ ለጌታነህ ከበደ ሰጥተውት የፀና የቅፅል መጠሪያው እንደሆነ ይህም “አፍሪካ” የሚለው ቅፅሉ ፀንቶ ምንተስኖት ከበደ ከሚለው ስሙ በላይ የሚታወቅበት መጠሪያው ሆኗል፡፡ “አፍሪካ የሚለውን ስም ለምጄ አንዳንዴ ትክክለኛ ስሜ ሲጠራ ግር ይለኛል አፍሪካ በሚለው ቅፅል ስሜም ደስተኛ ነኝ” ሲልም ይናገራል። ፀጉሩ ቁጥርጥር መሆኑ ደግሞ የአፍሪካ ሌላው መለያ ሆኗል፡፡ “የተለየ ነገር የለውም እንደ ስታይል ተሞክሮ ፀንቶ የቀረ የፀጉር ቁጥር ነው” ሲል ይናገራል ሹሩቤው አፍሪካዊ ምንተስኖት ከበደ…. እንደ እርሱ ብሆን ብዬ የተመኘሁት ተምሣሌት ተጨዋች የለኝም ያለው አፍሪካ መቀለ 70 እንደርታ በ2013 የውድድር አመት በኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ አለመካፈሉን ተከትሎ በአንድ አመት ውል የካሳዬ አራጌ ስብስብን ተቀላቅሎ በኢትዮጵያ ቡና የኋላ መስመር ላይ የማይጠፋ ሆኗል፤ የሀትሪኩ ዮሴፍ ከፈለኝ ከምንተስኖት ጋር በነበረው ቆይታ ወቅታዊ በሆኑ እግር ኳሳዊ ጉዳዮች ዙሪያ ላቀረበለት ጥያቄ የፊት ለፊቱን ድፍረት የተሞላበት ምላሹን ሰጥቶታል፡፡

ሀትሪክ፡- የአድዋ ድል ክብረ በዓል እለት ወልቂጤ ከተማን ረታችሁ…..ላንተ ምን ትርጉም ሰጠህ?

ምንተስኖት፡- /ሳቅ/ በጣም ነው የተደሰትነው …ድርብ ድል ነው ሜዳ ላይ የነበረው ድባብ የአከባበሩ ስሜት ያስደስታል እኛነታችንን የሚገልፅ በአልን ለመጀመሪያ ጊዜ ተደስቼ አክብሬዋለሁ አጋጣሚው ድል አድርገን መሆኑ ያስደስታል በአሉ የሚከበረው በኢትዮጵያ ብቻ እንደመሆኑ ኢትዮጵያ ቡና የሚለውም ስም ድሉን ምርጥ አድርጎታል በጣም ተደስቻለሁ/ሳቅ/

ሀትሪክ፡- በጨዋታው መሃል ተጎድተህ ተቀይረህ ወጥተሃል… አሁንስ እንዴት ነው ለውጥ ታይቶበታል?

ምንተስኖት፡- ትላንት ያስነክሰኝ ነበር አሁን ግን ትልቅ ለውጥ አለው /ቃለ ምልልሱ የተሰራው ረቡዕ ዕለት ነው/ የጎን ታፋዬ ላይ ነው የተጎዳሁት… መሳሳብ ነው ወጌሻችን ይስሀቅ አይቶኝ ታሽቼ ለውጥ አይቼበታለሁ፡፡

ሀትሪክ፡- ቆይታህን እንዴት አገኘኸው… ?
ውሉ ሊራዘም ይችላል?

ምንተስኖት፡- ያው የመቐለ 70 እንደርታ ተጨዋች እንደመሆኔ ውል ያለኝ ለአንድ አመት ብቻ ነው ምናልባት አሁን ባለው ሁኔታ ውል ባድስ ደስ ይለኛል ነገር ግን የቢሮውና የአሰልጣኞቹ ውሣኔ ይወስነዋል የሚመጣውን ነገር ግን ለመቀበል ዝግጁ ነኝ እዚህ ቆይቼ ውሌን ባድስ ግን ደስ ይለኛል፡፡

ሀትሪክ፡- የደጋፊን ጫና የመቋቋም አቅም አለኝ ብለህ ታምናለህ?

ምንተስኖት፡- አዎ በሚገባ አቅም አለኝ… በደጋፊ ታጅቤ ስጫወት ለ2ኛ ጊዜ ነው በአዳማና በኢትዮጵያ ቡና…ለመከላከያ ብጫወትም ሜዳ ገብቶ የሚደግፍ በርካታ ደጋፊ የለውም እንዲያውም የኢትዮጵያ ቡና ደጋፊ ሜዳ ገብቶ አለመመልከቱ ቅር አሰኝቶኛል አለም ላይ የተፈጠረው ነገር ያመጣው ጣጣ በመሆኑ ግን ከመቀበል ውጪ አማራጭ የለኝም፡፡

ሀትሪክ፡- አሰልጣኝ ካሳዬ አራጌ ጨመረልኝ የምትለው ነገር አለ?

ምንተስኖት፡- አለ… ብዙ ነገር አድርጎልኛል እግር ኳስ ቀሎኝ እንድጫወት አድርጎኛል ልምምዱ ደግሞ አዕምሮዬ እንዲያድግ አድርጎታል ከጓደኞቼ ጋር እንዴት መቀባበል፣ መቼና የት ድረስ መሄድ እንዳለብኝ አስተምሮብኛል ስለተቸኮለ ብቻ በፍጥነት ግብ ጋር መድረስ እንደማይቻል አሳይቶኛል…. ደስ የሚልና የሚገርም ለውጥ ራሴ ላይ አይቻለሁ፡፡

ሀትሪክ፡- በተሰለፍክባቸው ጨዋታዎች ደስተኛ ነህ?

ምንተስኖት፡-አዎ በተለይ በተሰለፍኩባቸው ጨዋታዎች ደስተኛ ነኝ፤ በገባሁባቸው ጨዋታዎች በሙሉ አሸናፊ እኛ ነበርን ለዚህም ነው በገባሁባቸው ጨዋታዎች ደስተኛ የሆንኩት፡፡

ሀትሪክ፡- ባልገባሁባቸው ጨዋታዎች ደስተኛ አልነበርኩም ወይም አይደለሁም እያልክ ነው?

ምንተስኖት፡- “በተለይ” ብያለሁኮ ባልገባሁባቸውም ጨዋታዎች ለምን አልገባሁም ብዬ የምናገርበት ጊዜ ላይ አይደለሁም ምክንያቱም አለቃ አለኝ አሰልጣኝ አለኝ ብቁ ነህ ሲል ያስገባኛል ተጠባባቂ ከሆንኩ ደግሞ እድሉን እስካገኝ መጠበቅ ነው… በቆይታዬና ቡድኑ ውስጥ በመኖሬ ደስተኛ ነኝ፡፡

ሀትሪክ፡- የሚገባኝን ያህል ተከብሬያለሁ ዋጋ ተሰጥቶኛል ብለህ መናገር ትችላለህ?

ምንተስኖት፡- ከጠበኩት በላይ ክብር አግኝቻለሁ ከደጋፊ የማገኛቸው ድጋፎች ከአሰልጣኞችና ከቡድኑ የሚገኙት ምክሮች ያስደስቱኛል ያውም ደጋፊው መግባት በማይችልበት ሰዓት ትልቅ ምክር ሰጥቶኛል አይዞህ ብለው ያበረታቱኝ ደጋፊዎቹ ናቸው በአጠቃላይ ከጠበኩት በላይ አግኝቼዋለው፡፡

ሀትሪክ፡- የኢትዮጵያ ቡና ዋነኛ ተቀናቃኝ ፋሲል ከነማ ብቻ? ወይም ቅዱስ ጊዮርጊስ?

ምንተስኖት፡- የመጀመሪያ ተቀናቃኝ ቅዱስ ጊዮርጊስ ነው አሁን ባለው የሊጉ መሪ ፋሲል ከነማ በመሆኑ ሌላው ተቀናቃኝ ደግሞ ፋሲል ከነማ ነው፡፡

ሀትሪክ፡- የዋንጫ ፉክክሩ ሶስትዮሽ ብቻ ነው ማለት ይቻላል?

ምንተስኖት፡-ይቻላል…የሶስታችን የዋንጫ ፉክክር ነው ብዬ አስባለው በተለይ ደግሞ የኛና የፋሲል ከነማ ፉክክር የበለጠ ነው ብዬ አምናለሁ፡፡

ሀትሪክ፡- ማሸነፍ የምትወደው ተጋጣሚ ማን ነው?

ምንተስኖት፡- ሁሌም ቢሆን ማሸነፍ ደስ የሚለኝ ቅዱስ ጊዮርጊስን ነው የምር ነው ደስ የሚለኝ… ይሄ ስሜት ከቡና በፊትም ያለ ነው፡፡

ሀትሪክ፡- ምክንያቱን ትነግረኝ?

ምንተስኖት፡- በእግር ኳሱ ብዙ ደጋፊ ያለው ትልቅ ክለብ መሆኑና አብዛኛው ክለብ ፈርቶ መምጣቱን ስታይ ያንንን ለመገልበጥና ለመስበር ቅዱስ ጊዮርጊስን ሁሌ ስናሸንፈው ደስ ይለኛል፡፡
ሀትሪክ፡- የሊጉ ልዩነት ፈጣሪ ማነው ትላለህ?
ምንተስኖት፡- የክለብ አጋሬ አቡበከር ናስር ነው…ይሄማ ጥርጥር የለውም ሌላው የትም ቦታ ላይ ሆኖ ልዩነት የሚፈጥረው ዳዊት እስጢፋኖስ ነው ከዳዊት ጋር አብሬው ልጫወት ተመኝቼ በመከላከያ ተሳክቶልኛል በቀጣይም አብሬው እንድጫወት እመኛለሁ፡፡

ሀትሪክ፡- የሊጉን ዳኝነት እንዴት አገኘኸው?

ምንተስኖት፡- ዳኝነትን ስናይ.. በተለይ ረዳት ዳኞች ላይ የጎላ ስህተት ነው የሚታየው… ከጊዜ ጊዜ ይሻሻል ቢባልም ያለፈውን ጨዋታ እያዩ እንኳን ስህተታቸውን ያላረሙ ዳኞች አሉ የዛኑ ያህል ደግም በጣም ጎበዞች አሉ ስህተቶች ግን አልተቀረፉም ግልፅ የሆኑ ስህተቶችን እያየን ነው በተለይ ረዳት ዳኞች ላይ እርምት ያስፈልጋል፡፡

ሀትሪክ፡- ዳኛን የሚያሸንፍ ክለብ የለም የሚሉ ወገኖች አሉ… ትስማማለህ?

ምንተስኖት፡- ይሄ ልክ አይደለም ኢትዮጵያ ቡናና ከወልቂጤ ግር ፍፁም ቅጣት ምት ተከልክሎኮ አሸንፏል፡፡ ከአዳማ ጋር የኦፍሳይድ ግብ ተለቆበትም አሸንፏል በርግጥ ሁሌ ዳኛን ብቻ ተጠያቂ ማድረግ ልክ አይደለም ራስን ማየትም ያስፈልጋል ዳኛኮ በአንድ ጨዋታ ላይ ልክ ያልሆነ ፍፁም ቅጣት ምት ሊሰጥ ይችላል ተገቢ የሆነ ደግሞ ሊከለክል ይችላል ወይም የኦፍሳይድ ግብ ሊያፀድቅ ይችላል ነገር ግን ተለይ ዘንድሮ ያንን መቀልበስ ይቻላል ባይ ነኝ፡፡ ለምሣሌ ቅዱስ ጊዮርጊስ ከፋሲል ከነማ ጋር ሲጫወቱ በተጨማሪ ሰዓት አርቢትር ቴዎድሮስ ምትኩ ሪጎሬ ሰጥቷል ሌላ ጊዜ ቢሆን ሆኖ ላይሰጥ ይችል ነበር ዳኛን ብቻ ግን መጠየቅ ተገቢነቱ ላይ ጥያቄ አለኝ።

ሀትሪክ፡- ቡና አዳማን 4ለ1 ሲረታ ስለ ድሉና ስለ አቡኪ ሀትሪክ ነው የተወራው ማንም ሰው ስለ ኦፍሳይዱ ግብ አላወራም….ቡና በጨዋታው አሸንፏል ቢሸነፍ ኖሮ ግን ሰበቡ ወደ ዳኞች ይዞር ነበር ይህን እንዴት ታየዋለህ?

ምንተስኖት፡- ዋናው ጉዳይ ራስን ማየት ያለማየት ችግር ነው፤ ሁሉንም ነገር ዳኞቹ ላይ መደምደምማ ተገቢ አይደለም ሁሉም ዞር ብሎ ራሱን ሊያይ ይገባል የዳኞች ስህተታቸው እንጂ ብዙ ልክ ነገራቸው አይወራም ይሄ ራስን በማየት ይስተካከላል ብዬ አስባለሁ፡፡

ሀትሪክ፡- ኢትዮጵያ ቡና ዋንጫውን ካነሳ በ10 አመት ውስጥ ለመጀመሪያ ጊዜ ይሆናል… ውስጣችሁ ዋንጫ ዋንጫ እያለ ነው?

ምንተስኖት፡- ከመቶ ፐርሰንት በላይ ነዋ…. ሁሉም ዋንጫ ዋንጫ እያለ ነው ጭራሽ የዋንጫ ስሜት ተፈጥሯል አሪፍ ልጆች አሉበት ቅኖች ናቸው ይሄ ሜዳ ላይ የሚታይ ነው ምንም ጥያቄ የለውም ኢትዮጵያ ቡና ዋንጫ ይወስዳል፡፡

ሀትሪክ፡- ፋሲል ከነማ ካልተሸነፈኮ ዋንጫ አታነሱም… ይሄን አላየኸውም?

ምንተስኖት፡- ሁሉንም አያሸንፍማ… ቅዳሜ እናሸንፈዋለን አሸንፈን ልዩነቱን በ2 ነጥብ እናጠበውና የሚሆነውን ማየት ነው ፋሲል ከነማን በመርታት አሸናፊነታችንን እናስቀጥላለን፡፡ የማይካደው ትልቅ ጨዋታ ነው ግን እኛም ትልቅነታችንን የምናሳይበት ግጥሚያ ይሆናል፡፡

ሀትሪክ፡- የአቡበከር ናስርን ጉዞ እንዴት አየኸው? ቡና አቡኪን በመያዙ እድለኛ ነው አይደል?

ምንተስኖት፡- አቡኪን ስለያዝን እድለኛ ነን በፍፁም የሚደርስበት አጥቂ የለም ከዚህ በኋላም በርካታ ግቦችን አስቆጥሮ ሪከርዱን ያሻሽላል በትንሽ ጨዋታ ብዙ ግብ ማስቆጠሩ መታወቅ አለበት ጊዜው የራሱ ነው፡፡

ሀትሪክ፡-የዲ.ኤስ.ቲቪ መምጣት በኳሳችን ላይ የሚታይ ልዩነት ፈጥሯል ማለት ይቻላል?

ምንተስኖት፡- ልዩነትማ ፈጥሯል ሌላው ቢቀር በዲሲፕሊን ደረጃ ለውጥ አለ በበፊቱ ዳኛ መክበብ መሳደብ መጎተል አሁን የለም ይሄ አንዱ ለውጥ ነው በፊት 1ለ0 ማሸነፍ ወይም አቻ መውጣት የተለመደ ነበር ብዙ ሩጫ የሌለበት እየተራመዱ የሚያጫወቱበት የሚል ትችት ይሰማበት ነበር አሁን ግን የለም በርግጥም በዲ.ኤስ.ቲቪ መታየቱ ተፅዕኖ ፈጥሯል ለውጥም አለውም ባይ ነኝ፡፡

ሀትሪክ፡- ኢትዮጵያ ቡና ቤት ውስጥ የገረመህ ምንድነው?

ምንተስኖት፡- ልምምዱ ይገርማል… ሁሌም የምገርምበትን ልምምድ እየሰራሁ ነው… ሌላ የተለየ ነገር የለም።

ሀትሪክ፡- ያ ማለት የ12ቱ ክለቦች አሰልጣኞችና ካሳዬ መሀል የሚደረግ ፍልሚያ ነው ማለት ይቻላል?

ምንተስኖት፡- ኧረ ይሄን ያህል አይጋነንም ሁሉም የየራሱ የስልጠና ሂደት አለው የካሳዬ ግን ይለያል አንተ እንዳልከው ግን የተጋነነ አይደለም፡፡

©natanim pictures

ሀትሪክ፡- ከአሰልጣኝ አሸናፊ በቀለ፣ ከአሰልጣኝ ስዩም ከበደ፣ ከአሰልጣኝ ገ/መድህን ኃይሌና ከአሰልጣኝ ካሳዬ አራጌ …. የቱ ይለያል?

ምንተስኖት፡- ትንሽ ካሳዬ ይለያል ነገር ግን ገ/መድህንም ጥሩ እንዲያውም የካሳዬ ስልጠና እንዲቀልልኝ ያደረገው የገ/መድህን ስልጠና ነው ብዬ አምናለሁ ተቀራራቢ ነገር አላቸው ከገብሬ ጋር ብዙም ሳንቆይ በተፈጠረው ችግር ተለያየን እንጂ ጥሩ ልምምድ ያሰራል የካሳዬ የቀለለኝ ቶሎም የተቀበልኩት በገ/መድህን ኃይሌ የስልጠና ሂደት ነው፡፡

ሀትሪክ፡- በአንተ ቦታ ኢትዮጰያ ውስጥ ምርጡ ማነው?

ምንተስኖት፡- የፋሲል ከነማው አምበል ያሬድ ባዬ ምርጫዬ ነው።ከውጪ የሪያል ማድሪዱ አምበል ሰርጂዮ ራሞስ ነው፡፡

ሀትሪክ፡- እንደ ተከላካይ ከሰርጂዮ ራሞስ ምኑን ወደድክ?
ምንተስኖት፡- ሰርጂዮ ራሞስ መጫወት ካለበት ይጫወታል ግብ ማስቆጠር ካለበትም ያስቆጠራል እውነተኛ አምበል ነው ለቡድኑ ሟች መሆኑ በአጠቃላይ እንድወደው አድርጎኛል፡፡

ሀትሪክ፡- ከውጪ የማን ደጋፊ ነህ?

ምንተስኖት፡- የዩናይትድ

ሀትሪክ፡- ኒውካስትል ዩናይትድ ወይስ?

ምንተስኖት፡- /ሳቅ በሳቅ/ ለምን ሊድስ ዩናይትድ አላልክም ?/ሳቅ/ ማንቼን ለመደገፍ የተለየ ምክንያት የለኝም በልጅነቴ ቀድሜ አይቼው ውስጤ ገብቷል /ሳቅ/

ሀትሪክ፡- እሁድ ምሽት ከሊጉ መሪ ማን.ሲቲ ጋር ጨዋታ አላችሁ ውጤት ምን ይጠበቅ?

ምንተስኖት፡- ቅዳሜ ኢትዮጵያ ቡና ፋሲል ከነማን እሁድ ማን.ዩናይትድ ማን.ሲቲን ይረታሉ /ሳቅ/

ሀትሪክ፡- የመሀል ተከለካይን ቦታ እንዴት መረጥከው?

ምንተስኖት፡- ከፕሮጀክት ስመጣ ቦታዬን ስከመር ነበር በኋላ በአሰልጣኝ ገዛኸኝ ከተማ ስር ኢትዮጵያ ቡና ቢ እያለሁ አንተ መሆን ያለብህ ሊብሮ ቦታ ነው ብሎ ነው አሁን ባለሁበት ቦታ የቀረሁት፡፡

ሀትሪክ፡- የቦታውን ለውጥ ታዲያ ወደድከው?

ምንተስኖት፡- ወድድኩት… ለመልመድም አልተቸገርኩም የኳስ እንጂ የቦታ አፍቃሪ ባለመሆኔ ቶሎ ወድጄ ለምጄዋለሁ፡፡

ሀትሪክ፡- ግብ ማስቆጠር አይሻልም… አጥቂ መሆን አይመረጥም?

ምንተስኖት፡- እዚህ ቦታ ላይም ሆኜ አስቀጥራለሁ /ሳቅ/

ሀትሪክ፡- /ሳቅ/ ሰርጂዮ ራሞስ ከሆንክ ነዋ

ምንተስኖት፡- /ሳቅ በሳቅ/

ሀትሪክ፡- ግብፅና ሱዳን በግድቡ ዙሪያ ዘራፍ እያሉ ነው.. ለጦርነትም እየስፈራሩ ነው የምትለው ነገር አለ?

ምንተስኖት፡- ምንም አያመጡም.. ፍርሃት ፈጥረውብኝም አያውቁም ለሀገራቱ ማለት የምችለው የጦርነትን አማራጭ እንዳያስቡት ነው/ሳቅ/

 

ሀትሪክ፡- ባለትዳር ነህ.. ባለቤትህና ልጆችህን አስተዋውቀኝ?

ምንተስኖት፡- ባለቤቴ ሳራ አክሊሉ ትባላለች አዳማ እያለሁ ነው የተዋወኳት የመጀመሪያዋ ልጄ ማራማዊት ሁለተኛው ልጄ ደግሞ አሜን ይባላል እንደምወዳቸው ልነግራቸው እፈልጋለሁ፡፡

ሀትሪክ፡- ጨረስኩ.. የምታመሰግነው ካለ?

ምንተስኖት፡- ፈጣሪዬ እግዚአብሔር አመሰግናለሁ… በመቀጠል ቤተሰቦቼን፣ ባለቤቴንና ልጆቼን፣፣ ጓደኞቼን ድጋፍ ያደርጉልኝ የቡና ደጋፊዎችን በኔ ነገር ላይ አንድ ነገር ጣል ያደረጉትን እድል የሰጠችኝን ሀትሪክን ከልብ አመሰግናለሁ፡፡

ስለ ኮቪድ 19

“በጣም የሚያስፈራው አብዛኛው ሰው ኮቪድ 19 እንደቀላል እያየው ነው ሁሉም ራሱን ሊከላከል ይገባል እላለሁ ማክስ ማድረጉ፣ በውሃ ማስታጠቡ ያለማክስና ሳኒታይዘር መታየት ልክ አይደለም የተባለበት ጊዜ የተረሳ ይመስላል፡፡ ስርጭቱ እየተስፋፋ ሲመጣ ከሚባለው በላይ ጥንቃቄ ያስፈልጋል ብዬ አስባለው ስፖርተኛው ብቻ ነው ቶሎ ቶሎ የሚመረመረው ሌላው ህብረተሰብ በሚችለው አቅም ራሱንመጠበቅ አለበት ባይ ነኝ”

ስለ አባይ ግድብ

“የመጀመሪያው የውሃ ሙሌት ዜና አስደስቶኛል ትልቅ ስራ ነው የተሰራው፡፡ ህብረተሰቡ ተባብሮ ከጎኑ ሊቆምለት የሚገባ ስራ ነው በኔ በኩል በ8100 ሆነ በቦንድ ግዢ የምችለውን እያደረኩ በመሆኔ ደስተኛ ነኝ፡፡ ግድቡ ሲጠናቀቅ ሀገር የሚለውጥ ተግባር ስለሚሆንበጋራ ልንጠብቀው ይገባል ተጠናቆ እስካይ ጓጉቼያለሁ”

ዮሴፍ ከፈለኝ

Editor at Hatricksport