ቅዱስ ጊዮርጊስ ከተጨዋቾች ዝውውርና ቅጥር በፊት መሰረታዊ ችግሩን እየመረመረ መሆኑን አስታወቀ፡፡
የዝውውር መስኮቱ ሀምሌ1/2013 ከመከፈቱ በፊት የተለያዩ የዝውውር ወሬዎች ቢወሩም ተአማኒነት የሌላቸውና ገና የውስጥ ክፍተቱን ለማወቅ ተግቶ እየሰራ መሆኑን ስማቸው እንዲጠቀስ ያልፈለጉ የክለቡ የስራ አመራር ቦርድ አባል በተለይ ለሀትሪክ ገልፀዋል፡፡
“ጠንካራውን፣ አሸናፊውንና የሚፈራውን ቅዱስ ጊዮርጊስ መመለስ እንፈልጋለን መሰረታዊ ችግራችንን ለማወቅና መፍትሔውን ለማግኘት ወደ ራሳችን በመመልከት መሠረታዊ ፍተሻ እያደረግን ነው ስለ አሰልጣኝ ቅጥርና ተጨዋቾች ዝውውር የምናወራው ችግሮቻችንን አውቀን የመፍትሔ አቅጣጫ ካስቀመጠን በኋላ ነው ከዚህ በፊት የምናወራው ዝውውርና አዲስ ሹመት የለም” ሲሉ የክለቡ የቦርድ አባል አስረድተዋል፡፡ እኚሁ የፈረሰኞቹ አመራር “ባለፉት 4 አመታት ዋንጫ አጥተናል ይሄ በክለባችን ያልተለመደ ደካማ ታሪክ ነው አንድ ተጨዋች አሰናብተን ሌላ ብናመጣ የመዋቅር ፍተሻ ካላደረግን ለውጥ የለውም ብለን እናምናለን በየቦታው የተቀመጠው ሰውና አሰራሩ ምን ያህል ጥንካሬ ነበረው? ለቦታውስ ይመጥናል ወይ? በማለት መርምረን ችግሩን ነቅሰን ካወጣን በኋላ ነው ወደ ዝውውሩ የምንገባው” ሲሉ ተናግረዋል፡፡
ፈረሰኞቹ ካለፉት 4 አመታት በሶስቱ በጅማ አባጅፋር፣ መቐለ 70 እንደርታና ፋሲል ከነማ ዋንጫ ሲነጠቁ በ2012 በኮቪድ 19 ወረርሽኝ ውድድሩ በመቆሙ ባለፉት 4 አመታት ዋንጫ ያላገኙባቸው አመታቶች ሆነዋል ይህም ክለቡ ውስጥ ቁጣ ቀስቅሷል፡፡ የቦርድ አባሉ አፅንኦት የሰጡት “ክለባችን አሸናፊ ቡድን ነው የድንቅ ታሪክ ባለቤትም ነው ይህን ለማስቀጠል እየሰራን ነው ዝውውር ለማድረግ ጊዜ ይጠይቃል ወቅትና ሰዓቱ ሲፈቅድ ወደ ዝውውሩ እንገባለን አሁን ትኩረታችን ራሳችንን በመፈተሽ ላይ አድርገናል እርግጠኛ የምሆነው ከስር ችግራችንን አይተን ስንመጣ ጠንካራውን ቅዱስ ጊዮርጊስ እንደምንመልስ ነው” ሲሉ ለሀትሪክ አስረድተዋል፡፡
“በኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ላይ ክለባችን ጠንካራ ተፎካካሪና አሸናፊ ቡድን ማድረግ ግዴታችን በመሆኑ ይህን ለማሳካት እየሠራን ነው የአሰልጣኝ ለውጥ የተጨዋቾች ዝውውር የአመራር አቅም ሌሎች ጉዳዮችን ካለፉት 4 አመታት ጀምሮ የነበረ ክፍተታችን ሁሉ መርምረን የመፍትሔ አቅጣጫ አስቀምጠን ወደ አሰልጣኝ ቅጥርና የተጨዋቾች ዝውውር ከገባን ምርጡንና አሸናፊውን ቅዱስ ጊዮርጊስ በ2014 ታዩታላችሁ” ሲሉ የተናገሩት እኚሁ አመራር “ችግራችንን ውጫዊ ሳይሆን ውስጣዊ አድርገን እየመረመርን ነው ለዝውውር አንቸኩልም ለተወሩ ወሬዎች ሁሉ ምላሽ ስንሰጥም አንገኝም በዋናነት ግን ጠንካራ ተፎካካሪና የዋንጫ ቡድን ሆነን ለመቅረብ ውስጣችንን እየፈተሽን ነው እንደሚሳካልንም ርግጠኞች ነን” በማለት ከሀትሪክ ለቀረበላቸው ጥያቄ ምላሽ ሰጥተዋል፡፡
አስተያየት ይስጡ