ሲዳማ ቡናን በሊጉ አናት ላይ ያስቀመጡት አሰልጣኝ ያሬድ ገመቹ ማናቸው።
ሀዋሳ ውስጥ ኳስን በአዝናኝ መልኩ ተጫውተው ካሳለፉት መካከል አንዱ ነው። በሀዋሳ ዱቄት የነበረው የተጫዋችነት ዘመኑ እስከ ኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ድረስ ቢያደርሰውም ጉዳት ሀገሩን ከማገልገል ውጥኑ እክል ሆኖበታል። እግር ኳስን አብዝቶ ከመውደዱ የተነሳ ተጫዋቾችን ሰብስቦ በማሰልጠን በዘጠናዎቹ አጋማሽ ወደ ስልጠናው የገባው የአሁኑ አሰልጣኝ ያሬድ ገመቹ (ውሮ) ከሽመልስ በቀለ የተነሳው ተጫዋቾችን ለሀገሪቱ የማበርከት በረከት ብዙሀኑ እንጀራቸው እንዲሆን በእግር ኳስ ፕሮጀክት ደረጃ የሰራው ስራም ለሀዋሳ እና አካባቢው እጅግ የማይረሳ ትዝታን ጥሎ አልፏል። ራሱን እያሳደገ ከፕሮጀክት ተነስቶ ፣ ከተማ ፣ ክልል አልፎም ደግሞ እስከ ሀገር አቀፍ የደረሰው የማሰልጠን ህይወቱ መሐል ላይ ገታ በማድረግ ፌድራል ዳኛ ሆኖ በኢትዮጵያ እግር ኳስ ውስጥ በመሐል ዳኝነትም ጭምር መስራት ችሏል።
የማሰልጠን ጥማቱ ከውስጡ ሊወጣ ያልቻለው እና አትክልት መኮትኮት እንዲሁም የቤት እንሰሳትን እየተንከባከቡ መዋልን አብዝቶ የሚወደው አሰልጣኝ ያሬድ ደቡብ ፓሊስ ፣ ስልጤ ወራቤ እና የቀድሞው ውሀ ስራዎች ወይም ኢኮስኮን ካሰለጠነ በኋላ በመሐል የድግሪ እና የማስተርስ ትምህርቱን በመከታተል የስፖርት ሳይንስ እና የእግር ኳስ ኮቺንግን ከማግኘቱ ባለፈ የእግር ኳስ የኤ ላይሰንስ የአሰልጣኝነት ሰርተፊኬትም ባለቤት መሆን ችሏል። በመቀጠል የሀዋሳ ከተማ ረዳት አሰልጣኝ ፣ የሲዳማ ቡና ረዳት አሰልጣኝ ፣ የሀድያ ሆሳዕና ረዳት አሰልጣኝ ሆኖ መስራት ከቻለ በኋላ 2015 ላይ ሀድያ ሆሳዕናን በዋና አሰልጣኝነት በመረከብ ክለቡ በኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ታሪክ 39 ነጥቦችን ለመጀመሪያ ጊዜ መሰብሰብ ሲችል አሰልጣኙ ይህንን ታሪክ በመስራትም ስማቸውን በብዕር አድምቀው ፅፈዋል።
2016 እና 2017 በወላይታ ድቻ ቆይታው ክለቡን ለተከታታይ አመት የኢትዮጵያ ዋንጫ የፍፃሜ ተፈላሚ በማድረግ በያዝነውም አመት በካፍ ኮንፌዴሬሽን ዋንጫ ላይ እንዲካፈል ጭምር ያደረጉት አሰልጣኙ 2011 ላይ የአሰልጣኝ ዘርአይ ሙሉ ረዳት ሆነው በመቐለ አንድ ነጥብን ብቻ በማጣቱ በወቅቱ ሻምፒዮን መሆን ወዳልቻለው ሲዳማ ቡና በዋና አሰልጣኝነት ዘንድሮ መመለስ ከቻሉ በኋላ ክለቡ በኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ታሪክ ሲዳማ ቡናን እየመሩ እስከ አሁን በተደረጉ 21 ጨዋታዎች 36 ነጥቦችን ሰብስበው ሊጉን በደረጃ አናት አስቀምጠው እንዲመራ አስችለዋል።
- ማሰታውቂያ -
በበርካቶች ስራው ላይ ብቻ አተኩሮ እንደሚሰራ የሚነገርለት አሰልጣኝ ያሬድ ገመቹ በዝምታ ውስጥ በስራዎቹ ራሱን ለብዙሀኑ ማሳየቱን ቀጥሏል።


