የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን የቀድሞ አሰልጣኝ ኢንስትራክተር ሰውነት ቢሻውን ለማመስገን እና ዕውቅና ለመስጠት የማስጀመሪያ መርሀግብር ተካሄደ።

ኢትዮጵያን ከ31 ዓመታት በኋላ ወደ አፍሪካ ዋንጫ እንድትመለስ በአሰልጣኝነት የመሩት የወቅቱ የካፍ ኢንስትራክተር ሰውነት ቢሻው በሀገሪቱ እግርኳስ ላይ ላበረከቱት የ44 ዓመታት አስተዋጽኦ በስማቸው አካዳሚ ሊገነባ እንደሆነ ተገልጿል። ዛሬ ከሰዓት ጁፒተር ሆቴል ላይ በነበረ ጋዜጣዊ መግለጫ በኮሚቴነት የተዋቀሩት ጋዜጠኛ ሰይድ ኪያር ፣ ጋዜጠኛ ምስግና መብራቱ ፣ የቀድሞው የኢትዮ ኤሌክትሪክ ስራ አስኪያጅ አቶ ኢሳያስ ደንድር ፣ የኢትዮጵያ ቡናው ደጋፊ የሱፍ መሐመድ ፣ የቅዱስ ጊዮርጊስ ደጋፊ እና የታሪክ ማህደሩ ጌዲዮን ስዩም እና የኤሌክትሪክ ደጋፊ የሆነው ሰለሞን ተሾሙ በስፍራው ለተገኙ ጋዜጠኞች ማብራሪያ የሰጡ ኮሚቴዎች ናቸው።

በስማቸው ለሙገነባው አካዳሚ የ9 ሺህ ካሬ ሜትር ቦታን ከአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የተበረከተ ሲሆን በአሁኑ ሰዓት ታዳጊዎች ላይ እየሰሩ የሚገኙት ኢንስትራክተር ሰውነት ቢሻውን ለማመስገን ዛሬ የተጀመረው መርሃግብር በቀጣይ ሀብት የማሰባሰብ ስራ እንደሚሰራ እና ለዚህም በሀገር ውስጥ እና በውጪ ያሉ ኢትዮጵያውያን አላማውን ደግፈው እገዛ እንዲያደርጉ ጥሪ ቀርቧል። በሀገር ውስጥ ላሉ የስፖርት ቤተሰቦችም የባንክ አካውቶች ይፋ ተደርጓል።

ሰኔ መጨረሻ ላይ ለማድረግ በታሰበው የዕውቅ እና የምስጋና የመዝጊያ መሰናዶ ላይ የኢንስትራክተር ሰውነት ቢሻውን የ44 ዓመታት የእግርኳስ ሕይወት የሚዘክር ዘጋቢ ፊልም እና መፅሐፍ ይፋ እንደሚሆንም በመግለጫው ተጠቁሟል።

አስተያየት ይስጡ