ቅዱስ ጊዮርጊስ ተከታታይ ድሉን ወደ ቋቱ ሲከት ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ከጨዋታ ብልጫ ጋር 3ለ0 ሲያሸንፍ ድሬዳዋ ከተማም ወሳኝ ድል አግኝተዋል።

ረጅሙን ዘመናት የኢትዮጵያ ቡና ፕሬዝዳንት በመሆን ያገለገሉት መቶ አለቃ ፍቃደ ማሞን በክብር በመሸኘት አዲሱን ፕሬዝዳንት ዶ/ር እስራኤል ደገፉን ከጨዋታው ቀደም ብሎ በመቀበል የጀመረው የሁለቱ ቡድኖች ጨዋታ ቀን ሰባት ሲል የሳምንቱ የመጀመሪያ ጨዋታ በኢትዮጵያ ቡና እና ሸገር ከተማ መካከል መደረግ ችሏል። ጥሩ አጀማመር የነበራቸው ሸገሮች 42ኛው ደቂቃ ላይ በሳጥኑ ትይዩ ራምኬል ጀምስ በዳዊት ካሳው ላይ በሰራው ጥፋት የተሰጠውን የፍፁም ቅጣት ምት ቾል ላም የዳኛውን ፊሽካ ሳይጠብቅ በፍጥነት በማስጀመር አሚር አብዶ የተቀበለውን ኳስ መረብ ላይ አሳርፎ ቡድኑን መሪ አድርጓል።

በሁለተኛው አጋማሽ ተሻሽለው የቀረቡት ቡናማዎቹ 61ኛው ደቂቃ ላይ የአቻነት ጎልን አስቆጥረዋል። የሸገሩ ቡልቻ ሹራ በግራ ሳጥን ይዞ ገብቶ በዳላንድ ኢብራሂም የተያዘበትን አስቆጪ ኳስ በመልሶ ማጥቃት ቢኒያም ጌታቸው ወደ ግራ ሳጥን ይዞ ለመግባት ሲል ገዛኸኝ ደሳለኝ በራሱ ግብ ጠባቂ ባህሩ ነጋሽ ተጠልፎ በእጅ ነክተሀል በሚል በዕለቱ ዋና ዳኛ ሔኖክ አበበ የፍፁም ቅጣት ምትን ይሰጣሉ ቀደም ብሎ ቢጫን ያገኘው ተከላካዩ ከአንደኛ ረዳት ዳኛው ተመስገን ሳሙኤል ጋር ከተደረገ ንግግር በኋላ የቀድሞው የቡናማዎቹ ተከላካይ ገዛኸኝ በቀጥታ ቀይ ካርድ ከሜዳ ከወጣ በኋላ የተገኘችውን ዕድል ከረጅም ቅጣት የተመለሰው አቡበከር አዳሙ ሲመታው የግብ ዘቡ ባህሩ ነጋሽ ቢመልሰው በድጋሚ ኳሷን ያገኘው አቡበከር የአቻነት ለእርሱ የአመቱ ሰባተኛ ጎሉን በማከል ጨዋታው በመጨረሻም 1ለ1 ተቋጭቷል።

ቅዱስ ጊዮርጊስን ከኢትዮ ኤሌክትሪክ ያገናኘው ጨዋታ በፈረሰኞቹ ድል አድራጊነት ተደምድሟል። የቀድሞው የቅዱስ ጊዮርጊስ ተጫዋቾችን በአሰልጣኝ የቴክኒክ ቦታ ላይ ያገናኘው ይህ መርሐግብር 10ኛው ደቂቃ ላይ ሀብታሙ ሸዋለም በራሱ ጥረት ይዞ ሳጥን ያደረሰውን ኳስ በጥሩ ቅብብል በድጋሚ ከአቤል ሀብታሙ ተቀብሎ ወደ ውስጥ ያሻገረውን ኳስ በፍቃዱ አስረሳኸኝ በግንባር ገጭቶ ቡድኑን ወደ መሪነት አሸጋግሯል።

ከዕረፍት መልስ ከፍ ባለ በራስ መተማመን ወደ ሜዳ የመለሱት ፈረሰኞቹ 53ኛው ደቂቃ ላይ ከቀኝ ሔኖክ ዮሐንስ በረጅሙ ወደ ግብ ክልል ያሻገረውን ኳስ በረከት ወልደዮሐንስ በግንባር ጨርፎ ከኋላ ለተገኘው ተገኑ ተሾመ አቀብሎት በጥሩ የራስ መተማመን በተረጋጋ ሂደት የሱፍ ሞሮ መረብ ላይ በማሳረፍ ጨዋታው ወደ 1ለ1 ተሸጋግሯል። በይበልጥ በተደራጀ ሽግግር ጫናዎችን ማሳደርን የቀጠሉት ቅዱስ ጊዮርጊሶች 76ኛው ደቂቃ ሀብታሙ ጉልላት ከቀኝ በረጅሙ የጣለውን ኳስ ናትናኤል ዱባለ በግንባር ገጭቶ የሰጠውን ፍፁም ጥላሁን በስታዲየሙ የተገኘውን ደጋፊ በደስታ ጮቤ ያስረገጠች ጎል በማስቆጠር ፈረሸኞቹ 2ለ1 አሸናፊ ሆነዋል።

ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ከሙሉ ብልጫ ጋር መቐለ 70 እንደርታን 3ለ0 አሸንፈዋል። ገና ጨዋታው ጀምሮ በሁለተኛው ደቂቃ ሁዘይፋ ሻፊ ከጨዋታ ውጪ በሚመስል ሂደት ከናትናኤል ዳንኤል ያገኘውን ኳስ ወደ ጎልነት ለውጦ ሀምራዊ ለባሾቹን ቀዳሚ ማድረግ ችሏል። እጅግ ከፍ ባለ መልሶ ማጥቃት እና በሽግግር የጨዋታ መንገድ የተጋጣሚያቸውን መከላከል ደጋግመው ያደረጉት ንግድ ባንኮች መደበኛው አጋማሽ ተጠናቆ በተሰጡት ሰባት ደቂቃዎች ውስጥ 47ኛው ደቂቃ ላይ አዲስ ግደይ ከማዕዘን አሻምቶ የቡድኑን ሁለተኛ ጎል ናትናኤል ዳንኤል በግንባር ገጭቶ ሶፎኒያስ ሰይፈ መረብ ላይ አስቀሞጧታል።

ከዕረፍት መልስም ከቆሙበት የቀጠሉት ንግድ ባንኮች 56ኛው ደቂቃ ሁዘይፋ ሻፊ የሰጠውን ኳስ ናትናኤል ዳንኤል ለራሱ ሁለተኛ ለቡድኑ ሦስተኛ ጎል ማድረግ ችሏል።
አመሻሹን ምድረገነት ሽረን ከድሬዳዋ ከተማ ያገናኘው የመጨረሻው የዕለቱ ጨዋታ በንፅፅር የተሻለውን መልክ ይዘው የቀረቡት የአሰልጣኝ ይታገሱ እንዳለው ድሬዳዋ ከተማ 52ኛው ደቂቃ ድልአዲስ ገብሬ ወደ ምድረገነት ሽረ የግብ ክልል አሻምቶ በተከላካዮች ተገጭቶ የተመለሰውን ኳስ በሀይሉ ግርማ በተሳሳተ አቅጣጫ ወደ ራሱ ሜዳ ወደ ኋላ ለቡድን ጓደኞቹ የመለሰውን ኳስ ከጀርባ ሆኖ ያገኘው መሐመድ ኑርናስር አግኝቾ ጎል በማስቆጠር ጨዋታው በዚህችው ብቸኛ ጎል በብርቱካናማዎቹ 1ለ0 አሸናፊነት ተጠናቋል።
በጨዋታው ላይ የምድረገነት ሽረው አሰልጣኝ ዳንኤል ፀሐዬ ከዳኛ ጋር በተፈጠረ አለመግባባት በሁለት ቢጫ በቀይ ከሜዳ ወጥተዋል።
አስተያየት ይስጡ