የ2019 የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ተሳታፊው ወላይታ ድቻ የውድድር ዝግጅቱን ምን እንደሚመስል በዚህ መልኩ ዳሰነዋል።

በተጠናቀቀው ዓመት ሁለት የውድድር መልክን በፕሪምየር ሊጉ ካሳዩን ክለቦች መካከል አንዱ እንደነበር የምናወሳው ወላይታ ድቻ በአሰልጣኝ ገብረክርስቶስ ቢራራ መሪነት አመቱን ቢጀምርም በውጤት ዕጦት ምክንያት የኋላ ኋላ ከአሰልጣኙ ጋር በመለያየት በምትኩ ረዳት የነበሩትን አምጣቸው ሐይሌን በጊዜያዊነት ለጥቂት ጨዋታዎች ከሰየመ በኋላ በመጨረሻም ከኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ጋር በወቅቱ መለያየት የቻሉትን አሰልጣኝ መሳይ ተፈሪን በመንበሩ በመሾም ቡድኑ ከነበረበት አስከፊ የውጤት ምዕራፍ በማውጣት አመቱን ከ38 የሊግ መርሀግብሮቹ 11 አሸንፎ 18 የአቻ ውጤት አስመዝግቦ 9 ተሸንፎ 37 ጎል አስቆጥሮ 31 ግቦችን ደግሞ አስተናግዶ በ6 የግብ ክፍያ 51 ነጥቦችን በመያዝ 7ተኛ ደረጃን በመያዝ ለማጠናቀቅም በቅቷል።
ለ2019 የውድድር ዘመን ክረምቱን የአሰልጣኝ መሳይ ተፈሪን ኮንትራት በማራዘም ወደ ዝውውሩ መግባት የቻሉት የጦና ንቦቹ ሁለገቡን ተጫዋች ሱለይማን ሀሚድን ከመቐለ 70 እንደርታ ፣ ግብ ጠባቂው ምንታምር መለሠን ከመቻል ፣ አጥቂው ሀሰን በሽርን ከኢትዮ ኤሌክትሪክ ፣ አማካዩ በረከት ወልዴን ከነገሌ አርሲ ፣ አበባየው ሀጂሶን ከሲዳማ ቡና ፣ በኢትዮጵያ ቡና እና ወልዋሎ ተጫውቶ ያሳለፈው ግብ ጠባቂው በረከት አማረን ፣ ናይጄሪያዊውን አጥቂ አናስ የሱፍን ከአልጄሪያው ክለብ ጄኤስ ሳውራ ፣ ሴራሊዮናዊውን አማካይ ሰይድ ፎፋናን ከእስራኤሉ ሀፖል ራህና ፣ ቶጓዊውን የመስመር ተከላካይ ጆሴፍ ያኦቪ ዶሀጂን ከኮንጎውው ሴንት ኢሎይ ሉፖፖ እና ማሊያዊውን አማካይ ሲአካ ባካዮኮን ከአልጄሪያው ኤም ቢ ሩይሳት ያስፈረማቸው አስሩ ተጫዋቾች ሲሆኑ በአንፃሩ ቴዎድሮስ ታፈሠ ፣ መሳይ ኒኮል ፣ ኪዳኔ አሰፋ ፣ መልካሙ ቦጋለ ፣ ናትናኤል ናሲሩ ፣ ቴዎድሮስ ሀይለማርያም እና ሴኔጋላዊው ግብ ጠባዊ ካዲም ኒዲያዬን ውል ደግሞ ተራዝሞላቸዋል። በክለቡ ለመቀጠል ተስማምቶ የነበረው ናይጄሪያዊው አማካይ ኦውግስቲን ኦኬጂፓ እና አዲስ ፈርሞ የነበረው ሴኔጋላዊው ተከላካይ አዳማ ዋዴ በበኩላቸው ከክለቡ ጋር እንደማይቀጥሉ ታውቋል። እንደ ሙሉቀን አዲሱ ፣ ቢኒያም ገነቱ ፣ ካርሎስ ዳምጠው እና ቀሪ አምስት በድምሩ ሰባት የሚደርሱ ተጫዋቾች ደግሞ ክለቡን የለቀቁ ነባር ተጫዋቾች ናቸው።
ከነሀሴ 19/2018 ጀምሮ የቅድመ ውድድር ዝግጅታቸውን በቀን ሁለት ጊዜ እንዲሁም በሂደት ወደ አንድ ዝቅ በማድረግ በመቀመጫ ከተማቸው ሶዶ ሲሰሩ የከረሙት የጦና ንቦቹ ከዝግጅታቸው ጎን ለጎን ራሳቸውን ለመገምገም ከሀዋሳ ከተማ ጋር ሁለት ጊዜ የወዳጅነት ጨዋታዎችን 3ለ2 እና 2ለ0 ሲያሸንፉ በአንፃሩ በኢትዮጵያ ቡና 1ለ0 ሽንፈት አስተናግደው ከሁለት የስብስብ ቡድኖች ጋር ተጨማሪ የወዳጅነት ጨዋታዎችን አድርገው የፊታችን ቅዳሜ በሊጉ የመክፈቻ ጨዋታ ባስመዘገቡት የሀላባ ስታዲየም ፋሲል ከነማን በመግጠም የውድድር ዘመናቸውን በይፋ ይጀምራሉ።
አስተያየት ይስጡ