የ2019 የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ተሳታፊው ሸገር ከተማ የውድድር ዝግጅቱን ምን እንደሚመስል በዚህ መልኩ ዳሰነዋል።

በተጠናቀቀው የ2018 የሲቢኢ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ላይ በታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ መካፈልን የጀመረው ሸገር ከተማ ከከፍተኛ ሊግ ወደ ላይኛው ዕርከን ካበቃው አሰልጣኝ በሽር አብደላ ጋር በመለያየት አሸናፊ በቀለን ቀጥሮ ጉዞ ማድረግ ቢችልም ከውጤት ማጣት ባሻገር ከቡድኑ ተጫዋቾች ጋር አሰልጣኙ በነበራቸው ያለ መግባባት ለስንብት የበቁ ሲሆን ከአዲስ አሰልጣኝ ይልቅ ረዳት አሰልጣኝ በነበሩት ዶ/ር እያሱ መርሀፅድቅ መሪነት አመቱን በ38 የሊግ መርሀግብር 11 አሸንፎ 17 የአቻ ውጤቶችን በማስመዝገብ 10 ጨዋታዎችን ደግሞ በማሸነፍ በተጋጣሚ መረብ ላይ 34 ጎሎችን በማዋሀድ 31 በማስተናገድ በ3 የግብ ክፍያ በ50 ነጥቦች 10ኛ ደረጃን በመያዝ ለሊጉ የሁለተኛ አመት ተሳትፎአቸው ትኬት ቆርጠው አመቱን ቋጭተዋል።
ለ2019 የሲቢኢ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ውድድር አስቀድመው በረዳት እና በጊዜያዊ ዋና አሰልጣኝነት እየመሩ አመቱን ያጠናቀቁትን ዶ/ር እያሱ መርሀፅድቅን በቋሚ ውል ዋና አሰልጣኝ አድርጎ በመሾም በመቀጠል ወደ ዝውውር የገባው ክለቡ የ9 አዳዲስ ተጫዋቾችን ፊርማም በገበያው ማግኘትም ችሏል። አማካዩ አብነት ደምሴን ከሀዋሳ ከተማ ፣ ተከላካዩ ብሩክ ባይሳን ከአርባምንጭ ከተማ ፣ አጥቂው ሀብታሙ ታደሠን ከሲዳማ ቡና ፣ አማካዩ መለሠ ሚሻሞን ከሀድያ ሆሳዕና ፣ ከከፍተኛ ሊጉ እዩኤል አበባየውን ከየካ ክፍለከተማ ፣ ከአንደኛ ሊግ አጥቂው ኡመድ ኡፒትን ከፉሪ ክፍለከተማ እና ተከላካዩ እንዳልካቸው ታደለን ከቡታጅራ ከተማ እንዲሁም ቶጓዊውን ግብ ጠባቂ የሱፍ ሞሮን ከኢትዮ ኤሌክትሪክ በማስፈረም አራት በክለቡ ከነበሩ ተጫዋቾች ጋር በመለያየት ወደ ዝግጅት መግባት የቻሉ ሲሆን በአማካይ ስፍራ ላይ ለአዳማ ፣ ሰበታ ፣ ባህርዳር እና ንግድ ባንክ የተጫወተው ፉዓድ ፈረጃ ለክለቡ ፊርማውን አኑሮ የነበረ ቢሆንም በጉዳት ምክንያት ከክለቡ ጋር መለያየቱ ታውቋል።
ከነሀሴ 20/2018 ጀምሮ በአዳማ ከተማ ነባር እና አዳዲስ ተጫዋቾችን በመያዝ ወደ ቅድመ ውድድር ዝግጅት የገቡት ሸገር ከተማዎች በጂም እና በሜዳ ተግባራት በሊጉ ላይ ጠንካራ ሆኖ ለመገኘት ልምምዳቸውን ሲሰሩ የሰነበቱ ሲሆን የዝግጅት ምዕራፋቸውን በወዳጅነት ጨዋታ ለማሳደግ በሚል ከስብስብ ቡድኖች ጋር ጀምረው በመቀጠል ኢትዮጵያ ቡና እና ሀድያ ሆሳዕናን በተመሳሳይ 2ለ1 በሆነ ውጤት በማሸነፍ ከፋሲል ከነማ ጋር 1ለ1 በመለያየት በመቻል 5ለ2 በመሸነፍ ለፕሪምየር ሊጉ ራሳቸውን ያዘጋጁ ሲሆን የፊታችን ዕሁድ በአዲስ አበባ ስታዲየም ኢትዮጵያ ቡናን በሚገጥሙበት ጨዋታ የውድድር ዘመን ጉዟቸውን በይፋ ይጀምራሉ።
አስተያየት ይስጡ