የኢትዮጵያ ተጋጣሚ ኒጀር ሁለተኛ የወዳጅነት ጨዋታዋን አሸነፈች

ለአፍሪካ ዋንጫ የምድብ ማጣሪያ የሶስተኛና አራተኛ ጨዋታዎች ኢትዮጵያን በደርሶ መልስ የሚገጥመው የኒጀር ብሔራዊ ቡድን ዛሬ ምሽት ባደረገው ሁለተኛ የወዳጅነት ጨዋታ የሴራሊዮን አቻውን አንድ ለምንም ረታ፡፡

አዲሱ የኒጀር ብሔራዊ ቡድኑ አሰልጣኝ ፈረንሳያዊው ዣን-ሚሸል ካቫሊ ከቡድኑ ጋር ሁለተኛ ድላቸውን በማስመዝገብ ካሁኑ የደጋፊውን ቀልብ መሳብ ችለዋል። አሰልጣንኙ ቡድኑን ባለፈው ሳምንት ከተረከቡ በኋላ ያደረጓቸውን ሁለት ጨዋታዎች በማሸነፍ የ100% የአሸናፊነት ግስጋሴያቸውን አስቀጥለዋል። አሰልጣኙ ሁለት ጨዋታዎችን አድርገው ሁለቱንም ሲያሸንፉ ምንም ግብ ሳይቆጠርባቸው ሶስት ግቦችን አስመዝግበዋል።

በጄኔራል ሴኚ ኩንቼ ብሔራዊ ስታዲየም የተደረገውን ጨዋታ ኒጀር አንድ ለባዶ ስታሸንፍ ግቡን ያስቆጠረው ለቡርኪናፋሶው ራሂሞ ክለብ የሚጫወተው ኢሳ ጂብሪላ ነው፡፡

ኢሳ ጅብሪላ ባለፈው ቅዳሜ ቡድኑ ቻድን ሁለት ለምንም ሲረታ ሁለተኛውን ግብ ከመረብ ማሳረፉ ይታወሳል።

Teshome Fantahun

Editor at Hatricksport