የአዉሮፓ ባህል እና ስፖርት ፌደሬሽን ከሌሎች አቻ የጤና ማህበራት ጋር በመተባበር ለመከላከያ ሰራዊት እና በጦርነቱ ምክንያት ለተፈናቀሉ ወገኖች የገቢ ማሰባሰቢያ ለማድረግ በሚል ባዘጋጀው የእገርኳስ ዉድድር ከጥር 6 ጀምሮ በኢትዮጵያ ወጣቶች እና ስፖርት አካዳሚ ሲካሄድ ቆይቶ በዛሬዉ ዕለት ፍፃሜዉን አጊኝቷል።

በአስር ቡድኖች መካከል ሲደረግ በቆየዉ የእግርኳስ ዉድድርም በዛሬዉ ዕለት ከረፋድ ጀምሮ የጥሎ ማለፍ እና የፍፃሜ ጨዋታዎች ተከናዉነዉበት ስታዲየም ዙሪያ የጤና ቡድንን አሸናፊ አድርጎ ተጠናቋል።

አስቀድሞ ረፋድ ላይ በጥሎ ማለፉ የተገናኙት ስታዲየም ዙሪያ የጤና ቡድን እና ኢትዮ አፍሪካ ሲሆኑ መደበኛውን የጨዋታ ክፍለጊዜያቸዉን በአቻ ዉጤት በማጠናቀቃቸው ምክንያት ወደ መለያ ምት አምርተዉ ስታዲየም ዙሪያ የጤና ቡድን ተጋጣሚውን ኢትዮ አፍሪካን በመለያ ምት በመርታት ለፍፃሜ ማለፍ ችሏል።

ከሰዓት በተደረገዉ ሁለተኛው የጥሎ ማለፍ ጨዋታ ደግሞ አበበ ብቂላ የጤና ቡድን ኳስሜዳ ሰፈር የጤና ቡድንን 2ለ1 በመርታት ለፍፃሜው ማለፍ የቻለ ሲሆን በፍፃሜውም ስታዲየም ዙሪያ የጤና ቡድን የፍፃሜ ተፋላሚዉን አበበ ብቂላ የጤና ቡድንን 1ለ0 በሆነ ጠባብ ዉጤት በመርታት የዋንጫ ባለቤት መሆን ችሏል።

የዉድድሩ የመዝጊያ ስነስርዓትም በነገዉ ዕለት መገናኛ አካባቢ በሚገኘዉ ቤልቪዉ ሆቴል ከምሽት 12:00 ሰዓት ጀምሮ ይካሄዳል።
አስተያየት ይስጡ