በገለልተኛ ሜዳ ሞሮኮ ላይ ሳኦቶሜ እና ፕሪንሲፔን በአፍሪካ ዋንጫ ቅድመ ማጣሪያ የገጠመው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን 3ለ0 አሸንፏል።
በሦስቱ የምስራቅ አፍሪካ ሀገራት አዘጋጅነት ለሚደረገው ለ2027ቱ የአፍሪካ ዋንጫ ለማለፍ ቀደም ብሎ በሚደረገው የምድብ የማጣሪያ ድልድል ውስጥ ለመካተት በቅድመ ማጣሪያ መርሀ-ግብርን ሞሮኮ ላይ ከሳኦቶሚ እና ፕሪንስፔ ጋር የመጀመሪያ ማጣሪያውን ያደረገው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን 3ለ0 በሆነ ውጤት አሸንፏል።

በመጀመሪያው አጋማሽ በይበልጥ ወደ ፊት ተስቦ መጫወትን መርጦ የታየው ዋልያው 23ኛው ደቂቃ ላይ የሳኦቶሜ ተከላካዮች በቅብብል ወቅት ወደ ግብ ዘቡ ወደ ኋላ የመለሱትን ኳስ ቀድሞ ያገኘው ከነዐን ማርክነህ አጋጣሚዋን መረቡ ላይ በማሳረፍ ቡድኑን መሪ ማድረግ ሲችል 32ኛው ደቂቃ ላይ ደግሞ በተከላካዮች የቅብብል ስህተት ከሳኦቶሚዎች እግር ስር ኳስን ያገኘውን አቤል ያለው በድንቅ አጨራረስ መረቡ ላይ ሁለተኛ ጎል አድርጓታል።

ጨዋታው ከዕረፍት ሲመለስ አሁንም ከቆሙበት ብልጫቸው የቀጠሉት ዋልያዎቹ በተለይ ተጋጣሚያቸው በድግግሞሽ ይሰሯቸው በነበሯቸው ስህተቶች ከግራ መስመር አቅጣጫ 78ኛው ደቂቃ ላይ አቤል ያለው የደረሰውን ኳስ አራት ተከላካዮችን በብልጠት አልፎ ለራሱ ሁለተኛ ለቡድኑ ሦስተኛ ጎል በማድረግ ጨዋታው 3ለ0 ፍፃሜን አግኝቷል።

የዚህ ጨዋታ የመልስ መርሀ-ግብር የፊታችን ማክሰኞ መጋቢት 22 በድሬዳዋ ስታዲየም የሚደረግ ሲሆን የድምር ውጤት አሸናፊው ወደ ማጣሪያ ድልድሉ የሚቀላቀል ይሆናል።
አስተያየት ይስጡ