ከሳኦቶሜ እና ፕሪንስፔ ጋር የአፍሪካ ዋንጫ የቅድመ ማጣሪያ መርሀግብር ያለበት የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ነገ አመሻሹን ልምምድ ይጀምራል።
ለአፍሪካ ዋንጫ የቅደመ ማጣሪያ ጨዋታ ከሳኦቶሜ እና ፕሪንስፔ ጋር የደርሶ መልስ ጨዋታ ያለበት የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን በአዲሱ አሰልጣኝ ዮሐንስ ሳህሌ አማካኝነት ከቀናት በፊት መጋቢት 16 እና 22 ለሚደረገው የማጣሪያ ጨዋታ ለሀያ ሦስት ተጫዋቾች ጥሪ መደረጉ ይታወሳል። ወደ ምድብ ድልድሉ ለመግባት ከፊቱ ወሳኙን መርሀግብር የሚያከናውነው ዋሊያው በዛሬው ዕለት የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ለዚህ ጨዋታ መቋረጡን ተከትሎ ቡድኑ በነገው ዕለት ልምምድ እንደሚጀምር ለማወቅ ችለናል።
ነገ ሰኞ መጋቢት 7 ረፋድ 4 ሰዓት ላይ ጥሪ የተደረገላቸው ሁሉም ተጫዋቾች ካሳንቺስ በሚገኘው ጁፒተር ሆቴል ተሰባስበው ማረፊያቸውን ካደረጉ በኋላ ከሰዓት ወደ አመሻሹን በአዲስ አበባ አልያም ዝናብ ካስቸገረ ደግሞ በአበበ ቢቂላ ስታዲየም የመጀመሪያ ልምምዳቸውን እንደሚሰሩ ማረጋገጥ ተችሏል።
ከብሔራዊ ቡድኑ ጋር በተያያዘ ለዋልያዎቹ ለመጀመሪያ ጊዜ ከአመታት በፊት በአሰልጣኝ ዮሐንስ ሳህሌ ተመርጦ የነበረው እና በድጋሚ ከአሰልጣኙ ጋር የተገናኘው ግዙፉ አማካይ ጋቶች ፓኖም የብሔራዊ ቡድኑ አምበል እንደሚሆንም ይጠበቃል።
አስተያየት ይስጡ