ለብሔራዊ ቡድን ከመቋረጡ በፊት ዛሬ ሁለት ጨዋታዎች የተደረጉበት የሊጉ ጨዋታዎች ኢትዮ ኤሌክትሪክ ሦስተኛ ተከታታይ ድሉን ሲያሳካ መቐለ እና ወላይታ ድቻ ነጥብ ተጋርተዋል።
ወላይታ ድቻን ከመቐለ 70 እንደርታ ጋር ያደረጉት ጨዋታው ያለ ጎል ተቋጭቷል። ጥሩ ፉክክሮች ነገር ግን ጥራት ባለቸው ሙከራዎች ብዙም መድመቅ የተሳነው የሁለቱ ቡድኖች ጨዋታ ከወራጅ ቀጠናው ከፍ ለማለት ወሳኝ የነበረ ቢሆንም 0ለ0 በሆነ ውጤት ተቋጭቷል።
ሀዋሳ ላይ ነገሌ አርሲን ከ ኢትዮ ኤሌክትሪክ ባገናኘው ጨዋታ የአሰልጣኝ ዘሪሁን ሸንገታው ቡድን ሦስተኛ ተከታታይ ድሉን አስመዝግቦበታል። በተጋጣሚያቸው ላይ ከጅምሩ ብልጫውን በመውሰድ መንቀሳቀስን የጀመሩት ኤሌክትሪኮች 20ኛው ደቂቃ ጎል አስቆጥረዋል። አቤል ሀብታሙ ከፓስካሌ ዴዝሪ ተጨርፋ ያገኛትን ኳስ አሾልኮ ሲሰጠው ሀሰን ሁሴን በድንቅ አጨራረስ የግብ ዘቡ እድሪሱ አብላሂን ጭምር በማለፍ ቡድኑን መሪ ያደረገች ጎልን መረቡ ላይ አሳርፏል።
29ኛው ደቂቃ ላይ ጨዋታው እንደደረሰ የነገሌ አርሲው የመሐል ተከላካይ ፓስካል ዴዝሪ ወደ መጨረሻው የሜዳ ክፍል የተጣለን ኳስ በእጅ በመንካቱ የዕለቱ ኢንተርናሽናል ዋና ዳኛ ሀይማኖት አዳነ በቀጥታ ቀይ ካርድ ከሜዳ ካስወጡት ከሰባት ደቂቃዎች በኋላ ነገሌዎች ሁለተኛ ጎል አስተናግደዋል። አንዋር በድሩ በጥሩ ዕይታ አመቻችቶ ሀሰን ሁሴን አሁን የነገሌን ተከላካዮች ስህተት ተጠቅሞ ለራሱም ሆነ ለቡድኑ ሁለተኛ ጎል አስገኝቷል። ከዕረፍት መልስም ከተጋጣሚያቸው በተሻለ ኤሌክትሪኮች ለተጨማሪ ጎሎች መቃረብ ቢችሉም ጎልና መረብን ማዋሀድ ሳይችሉ ቀርተው በመጨረሻም 2ለ0 ረተው ተከታታይ ሦስተኛ ድልን አሳክተዋል።
ትላንት ኢትዮጵያ መድን አርባምንጭ ከተማን 2ለ0 ኢትዮጵያ ቡና አዳማ ከተማን 3ለ2 ወልዋሎ ድሬዳዋ ከተማን 1ለ0 ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ሀዋሳ ከተማን 4ለ2 መርታታቸው ይታወሳል።
አስተያየት ይስጡ