በሳምንቱ የመጀመሪያ ቀን ጨዋታ የሊጉ መሪ ሲዳማ ቡና ወሳኝ ድል ሲያሳካ ሸገር ከተማ እና ባህርዳር ከተማ በተመሳሳይ ሲያሸንፉ ፋሲል ከነማ እና መቻል ያለ ጎል ቋጭተዋል።
ወደ ሊጉ የላይኛው ደረጃ ላይ ከፍ ለማለት ፋሲል ከነማ እና መቻልን ያገናኘው የአዳማ ሳይንስ እና ቴክኖሎጂ ስታዲየም ጨዋታ ሁለቱም ቡድኖች አሸንፎ ለመውጣት ጥረት ሲያደረጉ ያሳዩበት ሙሉ ዘጠና ደቂቃ ማየት ብንችልም ያለ ጎል 0ለ0 በመጨረሻም ተጠናቋል።
ሲዳማ ቡና የሊጉ መሪነት ወደ አምስት ያሰፋበትን ወሳኝ ድል ምድረገነት ሽረን በመርታት አስመዝግቧል። በመጀመሪያው አጋማሽ በእንቅስቃሴ ሲዳማ ቡናዎች የተሻሉ ቢመስሉም በሙከራዎች ካልታጀበው አጋማሽ ከዕረፍት መልስ በብዙ ነገር የተሻለበት ነበር። ምድረገነት ሽረዎች የተጫዋች ለውጥን በማድረግ ጥሩ ለመንቀሳቀስ ጥረት ቢያደርጉም 73ኛው ደቂቃ መስፍን ታፈሠ ከጀርባው ለተገኘው ፍራኦል ጫላ የሰጠውን ኳስ ከግራ ወደ ውስጥ ሲያሻማ የሽረ ተከላካዮች ስህተት ታክሎበት ጎል አስቆጥረው መሪ መሆን ችለዋል።
በቀጣዮቹ ደቂቃዎች ወደ አቻነት ለሚመጡት ሽረዎች ቢመስሉም አሁንም በመከላከል ስህተት እንደ መጀመሪያው ጎል ሁሉ መስፍን ታፈሠ አመቻችቶ ፍራኦል መንግስቱ ከተመሳሳይ ቦታ ያሻገረውን ኳስ መክብብ ደገፉ በግንባር ገጭቶ የግብ ዘቡ መክብብ ደገፉ ሲመልሳት አጠገቡ የነበረው አቤል ያለው ጎል አስቆጥሮ ጨዋታው በመጨረሻም 2ለ0 በሆነ ውጤት አሸናፊ ሆኖ በጨምበላላ ዋዜማ ባገኙት ወሳኝ ድል ሊጉን መምራታቸውን አጠናክረው ቀጥለዋል።
ሀዋሳ ላይ ሸገር ከተማ ተቀይረው በገቡ ሁለት ተጫዋቾች ወሳኝ ድልን አሳክቷል። ከጨዋታው መጀመር አንስቶ የተሻለውን ጊዜ ሜዳ ላይ ሲያሳልፍ የተስተዋሉት ሸገር ከተማዎች በሁለተኛው አጋማሽ በብዙ ነገሮች ተሻሽለው በመቅረብ ቀይረው ወደ ሜዳ ባስገቧቸው ሁለት ወጣት ተጫዋቾች ወሳኝ ድልን አግኝተዋል። 50ኛው ደቂቃ ላይ ወደ ቀኝ ሔኖክ አዱኛ ያቀበለውን ኳስ ተቀይሮ የገባው ሚሊዮን ሐይሉ ወደ ውስጥ መሬት ለመሬት ልኳት ሌላኛው ተቀያሪ አሚር አብዶ ወደ ጎልነት ለውጧት ቡድኑ ቀዳሚ ማድረግ ችሏል።
ጨዋታውን እየተቆጣጠሩ የቀጠሉት ሸገሮች 67ኛው ደቂቃ ላይ ሔኖክ አርፊጮ ከቡልቻ ሹራ ያቋረጠውን ኳስ ለማውጣት ጥረት ሲያደርግ ቡልቻ ተደርቦ በመጨረሻም ኳሷን ያገኘው ሚሊዮን ሐይሉ ሁለተኛ ጎል አድርጓት በመጨረሻም በሸገር 2ለ0 አሸናፊነት ተቋጭቷል። ለሁለቱም ጎሎች መቆጠር ግን የሀድያ ሆሳዕናዎች ደካማ መከላከል በጉልህ ያየንበት ነበር።
ምሽቱን ቅዱስ ጊዮርጊስን ከባህርዳር ከተማ ጋር ያፋለመው ጨዋታ የጣናው ሞገድን አሸናፊ በማድረግ ተደምድሟል። ፈረሸኞቹ በመጀመሪያው አጋማሽ በይበልጥ ኳሱን ተቆጣጥረው ለግብ የቀረቡ ዕድሎችን በመፍጠር ሻል ያሉ ቢመስልም ከዕረፍት መልስ ግን ሙሉ በሙሉ ባህርዳሮች በተለይ የአጥቂ ቁጥራቸውን ከፍ ካደረጉ በኋላ ጎል አግኝተዋል።
53ኛው ደቂቃ ላይ ተቀይሮ የገባው አማኑኤል ገብረሚካኤል ከፍ አድርጎ የሰጠውን ኳስ በፍጥነት ያገኘው ወንድወሰን በለጠ በጥሩ እይታ የቅዱስ ጊዮርጊስ መከላከል ስህተት ታክሎ ለአንተነህ ተፈራ ሰጥቶት አጥቂው በግሩም ሁኔታ መረብ ላይ አስቀምጧታል። 67ኛው ደቂቃ ላይም ወንድወሰን በለጠ ከግራ መስመር አቆጣጫ አቅሙን ተጠቅሞ እየነዳ ወደ ሳጥን ይዞ ገብቶ ያቀበለውን አንተነህ ተፈራ ለራሱም ለቡድኑም ሁለተኛ ጎል በማድረግ ባህርዳር ከተማ 2ለ0 አሸናፊ መሆን ችሏል።
አስተያየት ይስጡ