የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ዋና አሰልጣኝ መሳይ ተፈሪ የቡድኑን ዝግጅት በተመለከተ በጋዜጣው መግለጫው በርከት ያሉ ነጥቦች አንስቷል።
በተለይም በተደጋጋሚ የግብፅ ብሔራዊ ቡድን ጨዋታዎችን በደንብ ተመልክተናል ያለው አሰልጣኝ መሳይ በራሳችን ላይም ከዚህ ቀደም የነበሩብንን ክፍተቶች በመለየት ስራዎችን ሰርተናል ብሏል።
በጋራ በሚሰሩ ነገሮች ላይ በጣም ትኩረት ሰጥተን ሰርተናል በማጥቃትም ሆነ በመከላከል ወቅት ማድረግ ስለሚገቡን ነገሮች በተናጠል ልምምዶችን አድርገናልም ሲልም ተናግሯል።
ከአጨዋወት መንገድ ጋር በተያያዘ በ3-5-2 የጨዋታ ቅርፅ እንደሚጫወቱ የተናገሩ ሲሆን የመረጧቸው ተጫዋቾችም ለዚህ የጨዋታ መንገድ የሚሆኑ ስለመሆናቸው አብራርቷል።
- ማሰታውቂያ -
“3-5-2 ሲሆን ሶስቱ የመሀል ተከላካዮች ቆመው የሚጫወቱ አይደሉም። በተለይ ዳር ዳር ያሉትን ስንመርጥ በተወሰነ መልኩ እየሄዱ ማጥቃት የሚችሉ ተጫዋቾችን ነው የመረጥነው። በተጨማሪም በዳር እና በዳር ያሉት የመስመር ተጫዋቾች የአማካይ ባህሪ ነው ያላቸው።”
አክሎም ከግላዊ ይልቅ የቡድን ስራን ማስቀደማቸውን በመግለፅ ለመከላከል አይደለም የተዘጋጀነው ብሏል።
“ባላንስ የሆነ ነገር ነው ሰርተን የመጣነው መከላከሉንም አንንቅም ማጥቃቱንም አንተውም። ለመከላከል አይደለም የተዘጋጀነው እግር ኳስ ሁለቱንም ነገር ባላንስ አድርጎ መሄድ ይፈልጋል።”
ለዚህም የሚሆኑ ተጫዋቾችን በሁለቱ ጨዋታዎች ለመተግበር ካሰቡት ጨዋታ መንገዳቸው አንፃር በመለካት ምርጫው መደረጉን ጠቁሟል።
በአርቡ ጨዋታ የሚሆነውን ነገር ብንመለከት ጥሩ ነው ጨዋታው የሚነግረን ነገር አለም ሲል አሰልጣኝ መሳይ ገልጿል።
የግብፅ አጥቂዎችን በተመለከተም በግል ያላቸው ነገር ይታወቃል ያለው አሰልጣኝ መሳይ የመሀመድ ሳላህን ስም በመጥቀስ በጨዋታ ወቅት ምን ሊያደርጉ እንደሚችሉ እናውቃለን ፤ እንዴት ማቆም አለብን በሚለው ላይ በሚገባ ተዘጋጅተናል ብሏል።
ከተጫዋቾች ምርጫ መስፈርት ጋር በተያያዘ በዋነኝነት ወቅታዊ ብቃት ሲሆን የአጨዋወት መንገድ ፣ አካል ብቃት ፣ ዲሲፕሊን የመሳሰሉ ነገሮችም ከግምት ገብተው ብዙ አውጥተን አውርደን ነው ለ24 ተጫዋቾች ያደረግነው ሲል ተናግሯል።
“ከእኛ የጨዋታ መንገድ ጋር በተገናኘ የምንፈልገውን ነገር የሚሰሩ ልጆችን መርጠናል። እነ ሱራፌል ፣ ከነዓን እና ጋቶችን አላካተተንም። ያላካተትነው የምንፈልጋቸው ነገሮች አሉ ፤ በደንብ የምንፈልጋቸው የጨዋታ መንገዶች አሉ። አሁን እኛ ከምንከተለው አንፃር አላካተተንም።”
በሀገር ውስጥ የሚጫወቱ ተጫዋቾች ጥሩ ብቃት እያሳዩ ያሉ ቢኖሩም ሁሉንም መምረጥ አንችልም የተሻሉትን መርጠን በቡድኑ አካተናል ብሏል።
አቡበከር ናስርን በተመለከተም ለጨዋታው ዝግጁ መሆኑን በማንሳት ሙሉ ጤናማ ከሆነ ምን ማድረግ እንደሚችል የሚታወቅ ነው ሲል ገልፆታል።
“አቡበከርን በተመለከተ መረጃዎችን ወስደናል። ከሱ ጋርም ተነጋግረናል። ያለውን ሁኔታ ከቡድኑ ጋር እየሰራ እንደሆነ እና ጤነኛ እንደሆነ ቼክ አድርገን ነው ፤ አብሮን የመጣው። ከመጣ በኋላም የሚያሳየን ነገር ጥሩ ነገር ነው ያየንበት እኛ ከምንፈልገው ነገር አንፃር ይሰራልናል ያሉ ልጆችንም ያግዛል ብለን ነው ወደ እኛ ያካተትነው።”
የተጫዋቹ ወቅታዊ ብቃትም ጥሩ ነው ያለው አሰልጣኝ መሳይ አበቡከር ጤናማ ከሆነ ሜዳ ላይ ጥሩ ነገር መስራት የሚችል ልጅ ነው ብሏል።
“የአቡበከር ውቅታዊ ብቃትን በቅርበት ያሉ ሰዎች ሊናገሩ ይችላሉ ብዬ አስባለሁ። ጥሩ ሁኔታ ላይ ነው ያለው። ይታወቃል አቡበከር ጤናማ ከሆነ ጥሩ ነገር መስራት የሚችል ልጅ ነው። ጠንካራ ነገር የተሻለ ነገር ሊያመጣ የሚችል ጎበዝ ልጅ ነው።”
አሰልጣኝ መሳይ በተጨማሪም የቡድኑን ውጤታማነት በተመለከተ በሰጠው ግብረ መልስ በአንድ ጊዜ የሚለወጥ ነገር አይኖርም በሂደት ግን ለውጦቸን ታያላችሁ ፤ እያንዳንዱን ችግሮቻችንን አናልፍም ገምግመን እያረምን መፍትሄ ሰጥተን እንዲሁም እርማት ወስደን ነው የምንሄደው ምክንያቱም ይህ የግል ጉዳይ አይደለም የሀገር ጉዳይ ነው ብሏል።


