“እሱ አያስጨንቅህም አሁን ከአምስት ቀን በኋላ እለቅልሀለሁ”
“ትልቅ ቡድን ይዘን አይደለም ጊኒን የገጠምነው”
“ዲሞክራቲክ ኮንጎ እዚህ ቢመጣ በእርግጠኝነት ነው የምላችሁ ኢትዮጵያ ያሸንፋል”
“የተጋነነ ነገር ያለ አድርጋችሁ አትውሰዱት የአለም መጨረሻ አልያም ፍፃሜ አይደለም”
- ማሰታውቂያ -
ገብረመድህን ኃይሌ ፦ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ዋና አሰልጣኝ

አሰልጣኝ ገብረመድህን በሰጡት የዛሬው ጋዜጣዊ መግለጫ አስቀድመን ካጋራናችሁ ባለፈም ሌሎች ሀሳቦችን በጥያቄ እና መልስ አብራርተዋል።
የጊኒ ብሔራዊ ቡድን ከባድ ተጋጣሚ ነበር ልዩነታችን በጣም ግልፅ ነው ያሉት አሰልጣኝ ገብረመድህን የተጋነነ ነገር ያለ አድርጋችሁ አትውሰዱት የአለም መጨረሻ አልያም ፍፃሜ አይደለም። የጊኒን ቡድን የገጠምነው ሌላ ትልቅ ቡድን ይዘን አይደለም ብለዋል።
ቡድኑ በርሳቸው ስር ያደረጋቸውን ጨዋታዎች በሙሉ ከሜዳው ውጪ መጫወቱን በማንሳትም የጊኒ ሁለቱም ጨዋታዎች ጊኒ በሜዳው የተጫወተ ነው የሚመስለው በርካታ ደጋፊዎቹን ይዞ ነበር ብለዋል። በቀጣይም ብሄራዊ ቡድኑ ወደ ሀገሩ ተመልሶ ካልተጫወተ ከባድ ይሆናል ያሉት አሰልጣኙ ብሔራዊ ቡድኑ ወደ ሀገሩ ተመልሶ እንዲጫወት ሁሉም የድርሻውን እንዲወጣም ጠይቀዋል።
በሜዳችን የምናደርጋቸው ጨዋታዎች መኖር በቀጣይም ወጥተን ለምንጫወታቸው ጨዋታዎች ተፅእኖ አላቸው ሲሉም ተናግረዋል።
በምድቡ የሚገኘውን እና በሁለተኛው የምድብ ማጣሪያ ጨዋታ 2 – 0 በሆነ ውጤት የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድንን ያሸነፈው የዲሞክራቲክ ኮንጎ ቡድንን ሀገራችን ላይ ብንገጥመው እናሸንፈው ነበር የሚል ሀሳብ አሰልጣኙ ተናግረዋል።
“እዚህ ቢመጣ ዲሞክራቲክ ኮንጎ በእርግጠኝነት ነው የምላችሁ ኢትዮጵያ ያሸንፋል። ምንም ጥርጥር የለውም በብዙ ነገር ማለት ነው።ሴራ ሊዮንን ብታዩ እዚህ ቢመጣ ምን ያህል ተከናንቦ እንደሚሄድ ግልፅ ነው። ስለዚህ ጊኒም ቢመጣ እዚሁ ይሸነፋል። እዛ ሊያሸንፈን ይችላል ግን ይሸነፋል።”
ከቆይታቸው ጋር በተያያዘ ለቀረበላቸው ጥያቄም ተከታዩን መልሰ ሰጥተዋል። “እሱ አያስጨንቅም አሁን ከአምስት ቀን በኋላ እለቅልሀለሁ ፤ ችግር የለውም ውሉ ሲያልቅ ይጠናቀቃል። ውሉ በ23 ነው የሚያልቀው ለምን እንደሚያስጨንቃችሁ አይገባኝም እኔ” ሲሉ መልስ ሰጥተዋል።
ትውልደ ኢትዮጵያዊያን ተጫዋቾችን አምጥተን ለብሄራዊ ቡድን ማጫወት አለብን ያሉት አሰልጣኙ የኮሞሮስ ብሔራዊ ቡድንን እንደ ምሳሌ በማንሳት እነዚህ ተጫዋቾች ማጫወት ከቻልን ሀገር ውስጥ ላሉ ተጫዋቾችም ብዙ ነገር ያስተምራሉ ሲሉ ሀሳባቸውን ሰጥተዋል።


