“አጨዋዋታችን ስህተት ስለነበረ አይደለም የተሸነፍነው”
“የኛ ተጫዋቾች ኳስ ሲያገኙ ነው የሚጫወቱት ሲያጡ አይጫወቱም”
“የአቅማችን ልዩነት ጎልቶ ታይቷል”
“አቋሜን አልቀይርም አሁንም ወደ ፊትም ቀጥተኛ አጨዋወት ነው የምጫወተው”
- ማሰታውቂያ -

“ረጅም ጊዜ አልቆይም በስልጠናው ላይ”
ገብረመድህን ኃይሌ ፦ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ዋና አሰልጣኝ
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ዋና አሰልጣኝ ገብረመድህን ሀይሌ ሁለቱን የጊኒ ጨዋታዎች አስመልክቶ የድህረ ጨዋታ ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥተዋል።
አሰልጣኙ የጊኒ ብሔራዊ ቡድን በቀዳሚ ሁለት ጨዋታዎች(ከታንዛኒያ እና ዲሞክራቲክ ኮንጎ) ከነበረው ተቀይሮ መምጣቱን የገለፁ ሲሆን በጉዳትና በተለያዩ ምክንያቶች ያልነበሩ ተጫዋቾችን መልሰው ማግኘተቻው ተናግረዋል። በዚህም ልዩነት ፈጣሪ ተጫዋቾችን በማግኘተቻው ተጠቃሚ እንዳደረጋቸው አንስተዋል።
ቡድናቸው የስነ ልቦና ችግር እንዳለበት ያነሱት አሰልጣኙ አንድ ጎል ሲገባ ሌላ ጎል በቀላሉ የማስተናገድ ችግሮች ነበሩ ብለዋል።
በተለይም በሁለተኛው ጨዋታ ጋር ተያይዞ ባነሱት ሀሳብ በመጀመሪያው አጋማሽ 3 – 0 ተመርተው አጋማሹን ቢፈፅሙም በሁለተኛው አጋማሽ ግን በተሻለ ለማጥቃት መጣራቸውን እና የጊኒ ቡድን ጥቅጥቅ ብሎ በመጫወቱ አስከፍተው ዕድል ለመፍጠር መቸገራቸውን ጠቁመዋል።
ስለ ቡድኑ ውጤት በተመለከተ ከማንም በላይ የማዝነው እኔ ነኝ ሲሉ ተናግረዋል። “ኢትዮጵያ ስትሸነፍ ከማንም በላይ ነው የምቆረቆረው ፤ ተዋናይ ስለሆንኩን ማለት ነው። ከማንም በላይ እጎዳለሁ ፤ ስሜቱም በጣም ከፍተኛ ነው የሚሆነው።”
ያለን ወቅታዊ እና ተጨባጭ ሁኔታ መገንዘብ ያስፈልጋል ያሉት አሰልጣኝ ገብረመድህን ከቅርበት እና ርቀት ሲታይ አንድ አይደለም ግልፅ የአቅም ልዩነት አለ ብለዋል።
ለአብነት ያህልም የፍጥነት እና የጨዋታ ግንዛቤን በማንሳት ቡድኑ ከተጋጣሚያቸው ያነሰ መሆኑን በመግለፅ በተለይም ከኳስ ውጪ በሚደረግ እንቅስቃሴ ያለብን ችግር በጣም ከፍተኛ ነው ሲሉ ተናግረዋል።
በቀጣይም በደንብ ሊሰራበት ይገባል ባሉት ከኳስ ውጪ ያለ እንቅስቃሴ ደጋግሜ ለተጫዋቾቹ ነግሬያቸዋለሁ የኛ ተጫዋቾች ኳስ ሲያገኙ ነው የሚጫወቱት ሲያጡ አይጫወቱም ብለዋል።
አሰልጣኝ ባለፉት ሶስት ተከታታይ ጨዋታዎች ላይ የተጠቀሙትን እና በአራተኛው ጨዋታ ስለቀየሩት የፍሬዘር ካሳ እና የያሬድ ባየህ የመሀል ተከላካይ ጥምረት ተከታዩን ብለዋል።
“ፍሬዘር እና ያሬድ አንድ ላይ ተጣምረው በአንድ ተጣምረው የተጫወተለበት በአንድ ጨዋታ ላይ በጣም ጥሩ ነበሩ።በጣም ደስተኛ ነበርን። ከዛ በሁለተኛ ቀን ደግሞ ሙሉ ለሙሉ ሁለቱም ጥሩ አልነበሩም። ተጫዋቾቻችን በየጨዋታው የተለያየ አቋም ማሳየት ትንሽ ችግር ፈጥሮብናል። በዚህ ላይ የስነ ልቦና ድጋፍ ያስፈልጋቸዋል በአንድ ነገር ቶሎ የመርካት ነገር ይታይባቸዋል። ብዙዎቹ ማለት ነው።”
“የፍሬዘር እና ያሬድ የመጀመሪያ ጨዋታ በጣም ጥሩ ነበር። በሁለተኛው ጨዋታም ሁለቱም እነሱ ነበሩ የመጡት ፤ ግን ደግሞ ብዙ ስህተት የሰሩት እነሱ ናቸው።”
ከአጨዋወት ጋር በተያያዘ ለተነሳላቸው ጥያቄም “አቋሜን አልቀይርም አሁንም ወደ ፊትም ቀጥተኛ አጨዋወት ነው የምጫወተው ፤ ከዚህ በኋላ ምን ያህል ጊዜ ሊኖረኝ ይችላል ? ባለኝ አጭር ጊዜም ቢሆን ማለት ነው ፤ ረጅም ጊዜ አልቆይም በስልጠናው ላይ ማለት ነው ፤ እኔ ባመንኩበት ነው የምቀጥለው።”
አጨዋወታችን ስህተት ስለነበረ አይደለም በግልጽ ልዩነት ስላለን ነው የተሸነፍነው ሲሉ አሰልጣኝ ገብረመድህን ሀይሌ ተናግረዋል።


