“ህዳሴ ዋንጫ” በሚል ስያሜ የሚደረገው 19ኛው የአዲስ አበባ ከተማ ዋንጫ በዛሬው ዕለት በይፋ ተጀምሯል።
በአዲስ አበባ ስታድየም በተደረገው የመክፈቻ ጨዋታ መቻል በሁለተኛው አጋማሽ ባስቆጠራቸው ግቦች ቅዱስ ጊዮርጊስን 4 ለ 0 አሸንፏል።
ከጨዋታዉ በኋላ ከሀትሪክ ስፖርት ድህረ ገፅ ጋር ቆይታን ያደረገው የመቻሉ አሰልጣኝ ሙሉጌታ ምህረት ስለ ጨዋታው ተከታዩን ብሏል።
“ጨዋታው እንደ መጀመሪያ ጥሩ ነው። ጨዋታው ከቅዱስ ጊዮርጊስ ጋር ስለሆነ ሜዳ ላይ የነበረው ነገር ለቀጣይ ለኛ ለኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ራሳችንን በደንብ የምናይበት ስለነበረ ከሞላ ጎደል ጥሩ ነበርን ዛሬ።”
- ማሰታውቂያ -
የጨዋታው የመጀመሪያ አጋማሽ ያለ ግብ ከተጠናቀቀ በኋላ በሁለተኛው አጋማሽ የመጀመሪያ ደቂቃዎች መቻል ሶስት ግቦችን አስቆጥሯል።
የመጀመሪያው አጋማሽ ላይ በቀላሉ የግብ ዕድሎችን ለመፍጠር የተቸገረው ቡድኑ በሁለተኛው አጋማሽ መረጋጋቱ ግቦችን እንዲያገኝ እንዳስቻለው አሰልጣኙ ገልጿል።
“ምንም የተለየ ነገር የለም። ሁለተኛው አጋማሽ ላይ መረጋጋት ብቻ ነው ያደረግነው። 2 ለ 0 ከመራን በኋላ ተጫዋች በቀይ በመውጣቱ ያገኘነው ዕድል ተጠቅመን የተሻለ ነገር ብልጫም ወስደን ማሸነፋችን ጥሩ ነው።”
ዋናው የፕሪሚየር ሊጉ ወድድር ነው ያለው አሰልጣኝ ሙሉጌታ ምህረት ይህ አቋማችንን የምናይበት ነው ቢሆንም ግን ለቡድናችን ግንባታ ጥሩ ነው ሲል ተናግሯል።
መቻል በክረምቱ የዝውውር መስኮት በርከት ያሉ ተጫዋቾችን መቀላቀሉ የሚታወቅ ሲሆን የቡድኑን ውህደት ደረጃ በተመለከተ አሰልጣኝ ሙሉጌታ ሲል ተናግሯል።
“ቡድኑ ገና ቅንጅት ላይ ነው። ቀስ በቀስ ወደ ምንፈልገው ቦታ ለመምጣት ጊዜ ይፈልጋል። ልጆቹ ላይ የሚታየው ነገር ግን ጥሩ ነው።”
ተጋጣሚው በተመለከተም ቅዱስ ጊዮርጊስ ትልቅ ቡድን ነው ያለው አሰልጣኝ ሙሉጌታ ምህረት ፕሪሚየር ሊጉ ጥሩ ተፎካካሪ ቡድን ይሆናል ብዬ አስባለሁ ሲል ገልጿል።
በመጨረሻም ተጨማሪ ተጫዋች ወደ ያስፈርም እንደሆነ የተጠየቀው አሰልጣኙ ያሉን ተጫዋቾች በቂ ስለሆኑ ከዚህ በኋላ ትኩረቱ የቡድን ዝግጅት ላይ ብቻ መሆኑን ተናግሯል።


