ወልቂጤ ከተማን እና ፋሲል ከነማን ያገናኘዉ የሁለተኛው ሳምንት የቤትኪንግ ኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ጨዋታ በአፄዎቹ አሸናፊነት ተጠናቋል።
በአፄዎቹ በኩል ባለፈዉ ሳምንት ሀድያ ሆሳዕናን በረቱበት ጨዋታ ከተጠቀሟቸዉ ተጫዋቾች መካከል ሳሙኤል ዮሐንስን በበዛብህ መለዮ ቀይረዉ ወደ ሜዳ ሲገቡ በአንፃሩ በወልቂጤ ከተማዎች በኩል ደግሞ ከአዳማ ከተማ ጋር አቻ ከተለያዩበት ጨዋታ እስራኤል እሸቱን ፣ አህመድ ሁሴንን ፣ ረመዳን የሱፍን እና ዮናስ በርታን በ ያሬድ ታደሰ ፣ ጫላ ተሽታ ፣ ዉሀብ አዳምስ እና አበባዉ ቡጣቆ ተክተዉ ወደ ሜዳ ገብተዋል።

ጨዋታዉ እንደተጀመረ የመጀመሪያዎቹን አስር ደቂቃዎች ያክል ፋሲል ከነማዎች በመስመር ተከላካያቸዉ ሰይድ ሀብታሙ አማካኝነት ወደ ቀኝ ባዘነበለዉ ቦታ ላይ በተደጋጋሚ ወደ ተቃራኒ የግብ ክልል ለመድረስ ጥረት ሲያደርጉ ተመልክተናል። ከዚህ በዘለለ ግን በተደጋጋሚ ከራሳቸው የግብ ክልል ኳስን መስርተው ለመዉጣት ሲያደርጉት የነበረዉ ሙከራ ግን እምብዛም ዉጤታማ ነዉ ለማለት አያስደፍርም ነበር። በአንፃሩ በወልቂጤ ከተማዎች በኩል ደግሞ በራሳቸዉ የሜዳ ክልል ላይ በዝተዉ በመገኘት የተቃራኒ ቡድንን ኳስ በማበላሸት እና ረጃጅም ኳሶችን ለአጥቂዉ ጌታነህ ከበደ በመጣል ግብ ለማስቆጠር ሲያደርጉት በነበረዉ ሙከራ ዉጤታማ መሆን አልቻሉም ነበር።

በዚህ ሂደት የቀጠለው የሁለት ክለቦች ጨዋታም በ19ኛዉ ደቂቃ ላይ ግብ ተስተናግዶበታል። በዕለቱ በቀኝ መስመር በኩል ጥሩ ሲንቀሳቀስ ያመሸዉ ሰይድ ሀብታሙ በእጅ የወረወረውን ኳስ ሀብታሙ ተከስተ ቀጥታ ወደ ግብ ሲልካት በወልቂጤ ከተማዎች የግብ ክልል አካባቢ ይገኝ የነበረዉ በዛብህ መለዮ ኳሷን ወደ ግብነት ቀይሯት አፄዎቹን መሪ ማድረግ ችሏል። ግቧን ያስቆጠረው በዛብህ መለዮም መለያዉን አዉልቆ ደስታውን በመግለፁ ምክንያትም ቢጫ ካርድ ተመልክቷል።

ከግቧ መቆጠር በኋላ ወደ ጨዋታው ለመመለስ ጥረት ሲያደርጉ የነበሩት ክትፎቹ የመጀመሪያዎቹን ሀያ ደቂቃዎች ያክል ከነበራቸዉ የጨዋታ አቀራረብ በመሻሻል በተደጋጋሚ በአንድ ሁለት ቅብብል እንዲሁም የአጥቂ ስፍራ ተጫዋቾቻቸውን ኢላማ ያደረጉ ኳሶችን በመጠቀም ወደ አፄዎቹ የሜዳ ክልል በመግባት ተጭነዉ ለመጫወት ሲሞክሩ ተስተዉሏል። በዚህም በ32ኛዉ ደቂቃ ላይ የአማካይ ስፍራ ተጫዋቹ አብዱልከሪም ወርቁ ከአስራ ስድስት ከሀምሳ ዉጭ አክርሮ የላካት ኳስ ምንም እንኳን ወደ ኢላማዋን ሳትጠብቅ ወደ ዉጭ ብትወጣም በክትፎቹ በኩል የተደረገ ለግብ የቀረበ ሙከራ ነበር ማለት ይቻላል።

በድጋሚ በ39ኛዉ ደቂቃ ላይም ወልቂጤ ከተማዎች ከግራ መስመር በኩል ያገኙትን ቅጣት ምት አበባዉ ቡጣቆ ወደ ግብ ሞክሯት ግብ ጠባቂው ሚኬል ሳማኬ የተቆጣጠራት ኳስ በክትፎቹ በኩል ከተደረጉ የመጀመሪያው አጋማሽ ሙከራዎች መካከልም ተጠቃሽ ናት። ተመጣጣኝ የሚባል የሜዳ ላይ ፋክክርን ሲያስመለክተን የነበረዉ የሁለቱ ክለቦች ጨዋታም የመጀመሪያው አጋማሽ በፋሲል ከነማ የ1ለ0 መሪነት ተጠናቋል።
ከዕረፍት መልስ በ47ኛዉ ደቂቃ ላይ የአፄዎቹ የፊት መስመር ተጫዋች ፍቃዱ አለሙ ከሽመክት ጉግሳ የተቀበለዉን ኳስ ከርቀት ወደ ግብ የላካት ቢሆንም ግብ ጠባቂው ጎቦሆ እንደምንም ወደ ዉጭ አዉጥቷታል።
በአንፃሩ በ48ኛዉ ደቂቃ ላይ ደግሞ የክትፎቹ ፊት አጥቂ ከአማካዩ ጋር አንድ ሁለት ተቀባብለው ወደ ወደ አፄዎቹ የግብ ክልል ከደረሱ በኋላ ጌታነህ ከበደ በግንባሩ የሞከራት ኳስ ምንም እንኳን ከጨዋታ ዉጭ ነዉ በሚል በዕለቱ ዳኛ ጨዋታው በመልስ ምት እንዲቀጥል ቢወስኑም በክትፎዎቹ በኩል የምታስቆጭ አጋጣሚ ነበረች።

በድጋሚ በ50ኛዉ ደቂቃ ላይ የወልቂጤ ከተማዉ አማካይ አብዱልከሪም ወርቁ በተከላካዩ ያሬድ በመጠለፉ ምክንያት የተገኘዉን ፍፁም ቅጣት ምት ጌታነህ ከበደ ቢመታዉም የአፄዎቹ ግብ ጠባቂ ሳሜኬ ሚካኤል አድኗታል።

በፍፁም ቅጣት ምቱ በኋላ በቅፅበት ወደ ጨዋታዉ የተመለሱት አፄዎቹ በፈጣን የመልሶ ማጥቃት በ53ኛዉ ደቂቃ ላይ ያገኙትን ኳስ በዛብህ መለዮ ከርቀት አክርሮ ወደ ግብ የላካት ቢሆንም ግብ ጠባቂው ጎቦሆ እንደምንም ተቆጣጥሯታል።
እስራኤል እሸቱን እና አህመድ ሁሴንን በያሬድ እና ጫላ ቀይረዉ በማስገባት የማጥቃት ሀይላቸዉን ለማጠናከር የሞከሩት ወልቂጤዎች በአማካዩ አብዱልከሪም እና አማካኝነት በተደጋጋሚ ከሚያደርጓቸዉ ሙከራዎች ዉጭ ይህ ነዉ የሚባል የጎላ የግብ ሙከራ ማድረግ ሳይችሉ ለዉሀ እረፍት ወጥተዋል።

በ78ኛዉ ደቂቃ ላይ ደግሞ ሱራፌልን ቀይሮ ወደ ሜዳ የገባው ሳሙኤል ዮሐንስ ድንቅ ሙከራን ማድረግም ችሎም ነበር። በድጋሚ ከአምስት ደቂቃዎች በኋላ በወልቂጤ ከተማዎች የግብ ክልል መገኘት ችለዉ የነበሩት ፋሲል ከተማዎች በአማካዩ በዛብህ መለዮ አማካኝነት ለግብ የቀረበ አስቆጭ ሙከራን ማድረግ የቻሉ ቢሆንም በተደጋጋሚ ሲደረጉበት የነበሩትን ሙከራዎች ሲያመክን ያመሸዉ ቸክትፎዎቹ ግብ ጠባቂ ጎቦሆ አሁንም በድጋሚ ኳሷን እንደምንም ወደ ዉጭ አዉጥቷታል።

በተደጋጋሚ ረጃጅም ኳሶችን በመጠቀም ግብ ለማስቆጠር ሲጫወቱ የነበሩት ክትፎቹ ዉጥናቸዉ ሰምሮ ግብ ማስቆጠር ሳይችሉ ቀርተዉ በአፄዎቹ አንድ ለምንም ለመሸነፍ ተገደዋል።
አስተያየት ይስጡ