የጨዋታ ዘገባ | ተጠባቂው ጨዋታ በአቻ ውጤት ተጠናቋል

በአምስተኛው ሳምንት የመጨረሻ ቀን ጨዋታ በቅድሚያ የተገናኙት ቅዱስ ጊዮርጊስ እና ሲዳማ ቡና ጨዋታቸውን በአንድ አቻ ውጤቴ አጠናቀዋል።

ሁለቱም ክለቦች ከአራተኛ ሳምንት ጨዋታቸው የተወሰኑ ለውጦችን አድርገው ወደ ሜዳ ገብተዋል ። ፈረሰኞቹ መከላከያን ከገጠመው ቋሚ አሰላለፍ አራት ለውጦችን ሲያደርጉ ሲዳማ ቡናዎች ድሬደዋ ከተማን ከገጠመው ቋሚ 11 ሶስት ለውጦችን በማድረግ ወደ ጨዋታቸውን ጀምረዋል ።

በፈረሰኞቹ በኩል ደስታ ደሙ ፤ ጋቶች ፓኖም ፤ ተገኑ ተሾመ እና እስማኤል ኦጎሮ አንዲሁም በሲዳማ ቡና በኩል ደግሞ ግርማ በቀለ ፤ ብሩክ ሙሉጌታ እና ብርሀኑ አሻሞን ወደ ቋሚ አሰላለፍ በማካተት ጨዋታውን ጀምረዋል ።

በጨዋታው የመጀመሪያው ደቂቃዎች ቅዱስ ጊዮርጊሶች የተሻለ ብልጫ ቢያሳዩም ወደ ግብ ቀርበው የግብ ሙከራ ከማድረግ ረገድ የተሳካ ነገር ማድረግ አልቻሉም ነበር ። ሁለቱም ክለቦች ተመጣጣኝ እንቅስቃሴ በማሳየት ቢቀጥሉም ጠንከር ያለ የግብ ሙከራ ማድረግ ግን ተስኗቸው ነበር ።

በጨዋታው 33ኛ ደቂቃ ላይ ሲዳማ ቡናዎች መሪ መሆን የቻሉበትን የመጀመሪያውን ግብ አገኙ ።

በተጋጣሚ የቀኝ መስመር ሳጥን አካባቢ የነበረው ብሩክ ከሀብታሙ የደረሰውን ኳስ ደስታ ደሙን በመሸወድ ለይገዙ ቦጋለ ያቀበለው ሲሆን ኳሱን ነፃ ሆኖ የተቀበልዎ ይገዙ የፈረሰኞቹ ግብ ጠባቂ ሉክዋጎ ባቀበለው በኩል መትቶ በማስቆጠር ሲዳማ ቡናን መሪ ማድረግ ቻለ ። የጨዋታው የመጀመሪያው አጋማሽም በዚሁ ውጤት ተጠናቀቀ ።

በሁለተኛው የጨዋታ አጋማሽ ፈረሰኞቹ ከመመራታቸው አንፃር ግብ ለማግኘት ከሲዳማ ቡና በተሻለ ወደ ግብ ለመድረስ ሞክረዋል ። ሲዳማ ቡናዎች የያዙትን ውጤት በማስጠበቅ ጨዋታውን ለማጠናቀቅ ጥረቶችን አድርገዋል ። አጋማሹ በርካታ የግብ ክልል መመላለሶች ቢኖሩትም በሙከራ ረገድ ይህ ነው የሚባል ጠንካራ የግብ ሙከራ አልተደረገም ነበር ።

75ኛው ደቂቃ ላይ ፈርሰኞቹ አቻ የሚያደርጋቸውን ግብ በአጥቂያለቸው እስማኤል ኦሮ ኦጎሮ አማካኝነት አስቆጠሩ ። በተጠቀሰው ደቂቃ ቡልቻ ሹራ የነጠቀውን ኳስ ለናትናኤል ዘለቀ አቀብሎ ናትናኤል መልሶ ለኦጎሮ ሲያቀብለው እስማኤል ኦሮ ኦጎሮ ዞሮ በመምታት በተክለማርያም ሻንቆ ግብ ላይ አስቆጠረ ።

ከግቧ በኋላ በሁለቱም በኩል ፈጣን ምልልሶች ቢኖሩም ተጨማሪ ግብ ማስቆጠር አልቻሉም ነበር ። በዚህም ውጤት መሰረት ፈረሸኞቹ ነጥባቸውን 7 ሲያደርሱ ሲዳማ ቡና ደግሞ ነጥባቸውን 6 አድርሰዋል ።

Writer at Hatricksport

Facebook

Habtamu Mitku

Writer at Hatricksport