የጨዋታ ዘገባ | ወላይታ ድቻ የሊጉ መሪ መሆን የቻለበትን ድል አስመዝግቧል

በዕለቱ ሁለተኛ ጨዋታ የተገናኙት ሰበታ ከተማ እና ወላይታ ድቻ ጥሩ ፉክክር ባደረጉበት ጨዋታ የጦና ንቦቹ 4 ለ 2 በማሸነፍ የሊጉን መሪነት መረከብ ችለዋል ።

ሰበታ ከተማ በአራተኛው ሳምንት ከተጠቀሙት ቋሚ አሰላለፍ ሶስት ለውጦችን በማድረግ የገቡ ሲሆን ጌቱ ሀይለማርያም ፤ አንተነህ ተስፋዬ እና ፍፁም ገብረማርያም ወደ ቋሚ አሰላለፉ የተመለሱ ተጫዋቾች ናቸው ። በወላይታ ድቻ በኩል አንድ ቅያሪ ብቻ በማድረግ ሀብታሙ ቦጋለን ጨዋታውን እንዲጀምር አድርገዋል ።

በጨዋታው ጅማሮ ላይ ወላይታ ድቻ በተሻለ ጨዋታውን ተቆጣጥረው ለመጫወት ያደረጉት ጥረት ለብዙ ደቂቃዎች የዘለቀ አልነበረም ። በአንፃሩ ሰበታ ከተማዎቾ ቀስ በቀስ ወደ ጨዋታው በመመለስ በኳስ ቁጥጥሩም ብልጫ በመውሰድ ወደ ፊት ለመሄድ ጥረቶችን አድርገዋል ።

በጨዋታው 8ኛ ደቂቃ ላይ ቃልኪዳን ዘላለም የተሰነጠቀለትን ኳስ ይዞ ወደ ግብ በመሄድ ማስቆጠር ቢችልም ኳሱን ሊነጥቀው ከኋላው ሲከተለው በነበረው ሃይለሚካኤል አደፍርስ ላይ ጥፋት ሰርተሀል በሚል የመሀል ዳኛው ግቡን ሽረውታል ።

15ኛው ደቂቃ ላይ ቃልኪዳን ዘላለም ሁለት ተጫዋቾችን አልፎ ዘደ ሳጥን ውስጥ ለመግባት ሲሞክር በበረከት ሳሙኤል ጥፋት ተሰርቶበት የጦና ንቦቹ የፍፁም ቅጣት ምት አገኙ ። የፍፁም ቅጣት ምቱን በቄንጠኛ አመታት መቶ ለማስቆጠር የሞከረው ስንታየሁ መንግስቱ በለአለም ብርሀኑ በቀላሉ ተይዞበታል ።

በኳስ ቁጥጥሩ ብልጫ ወስደው መጫወት የቻሉት ሰበታ ከተማዎች ወደ ፊት አልፈው የግብ ሙከራዎችን በማድረጉ ረገድ ደከም ብለው የታዩ ሲሆን በአንፃሩ የኳስ ቁጥጥር ብልጫው የተወሰደባቸው ዘላይታ ድቻዎች ረጃጅም ኳሶችን በመጠቀም ወደ የተጋጣሙ ተከላካዮችን ለመፈተን ጥረዋል ።

33ኛ ደቂቃ ላይ በረከት ወልደዮሐንስ በረጅም የመታውን ስንታየሁ መንግስቱ በግንባሩ ገጭቶት ኳሱን ያገኘው ምንይሉ ወንድሙ ተከላካዩን በመሸውድ ለቃልኪዳን ዘለዓለም ለማቀበል ሲል አንተነህ ተስፋዬ በራሱ ላይ አስቆጠረው ።

ከሰባት ደቂቃዎች በኋላ ሰበታ ከተማ የአቻነቷን ግብ በፍፁም ቅጣት ምት አስቆጥረው ጨዋታው 1 ለ 1 ሆነ ። ከክንፍ የተሻገረውን ኳስ ለማውጣት ሲሞክር በረከት ወልደዮሀንስ በእጁ በመንካቱ ነበር የፍፁም ቅጣት ምቱን ያስቆጠረው በረከት ሳሙኤል ነበር ።

የመጀመሪያው አጋማሽ ሊጠናቀቅ ሁለት ያህል ደቂቃዎች ሲቀሩት ሳሙኤል ሳሊሶ ከሳጥን ውጪ ወደ ግብ የሞከረው ኳስ በያሬድ ዳዊት ተጨርፎ ሊገባ ሲል ፅዮን መርዕድ ለጥቂት አውጥቶታል ።

ሁለተኛው አጋማሽ ከጅምሩ እስከ ፍፃሜው ብርቱ ፉክክር የታየበት እና ለዕይታ ሳቢ የነበረ ጨዋታ አሳይቶናል ።

የሁለተኛው አጋማሽ ከተጀመረ 6 ደቂቃ ሲሆነው ከቀኝ መስመር ጌቱ ሀይለማርያም ወደ ግብ ያሻገረውን ኳስ ፍፁም ገብረማርያም በጭንቅላት በመግጨት ሰበታ ከተማን መሪ ማድረግ የቻለች ግብ 51ኛው ደቂቃ ላይ አስቆጠረ ። ከግቧ በኋላ ጫና መፍጠር የቻሉት ወላይታ ድቻዎች በምንይሉ ወንድሙ አማካይነት በፈጣን እንቅስቃሴ ሁለት ሙከራዎችን ቢያደርጉም ኢላማውቸውን የጠበቁ አልነበሩም ።

ጨዋታው 64ኛ ደቂቃ ላይ ሲደርስ ወላይታ ድቻዎች ሁለተኛ ግብ ማስቆጠር ቻሉ ። ከቀኝ መስመር ከቅጣት ምት ያሬድ ዳዊት ወደ ግብ ያሻማውን ኳስ በረከት ወልደዮሐንስ በግንባሩ ገጭቶ በማስቆጠር ነበር የጦና ንቦቹን አቻ ማድረግ የቻለው ።

ጫና ማሳደራቸውን የቀጠሉት የፀጋዬ ኪዳነማርያም ልጆች የመሪነቱን ግብ ለማግኘት የፈጀባቸው ሁለት ደቂቃ ብቻ ነበር ። የሰበታ ከተማ ተከላካዮች በሰሩትን ስህተት ኳሱ የደረሰው ስንታየሁ መንግስቱ ለቃልኪዳን ዘላለም አቀብሎት ቃልኪዳን በቀጥታ ወደ ግብ በመምታት ሶስተኛውን የወላይታ ድቻ ግብ አስቆጠረ ።

ሰበታ ከተማዎች በኳስ ቁጥጥሩ ብልጫ በመውሰድ ወደ ፊት መሄድ ቢችሉም የወላይታ ድቻን ተከላካይ መስመር ማለፍ ከባድ ፈተና ሆኖባቸዋል ። ወላይታ ድቻዎች የሚነጠቁ ኳሶችን በረጅም እንዲሁም በፈጣን ሽግግር ወደ ፊት ይዘው በመሄድ ተጨማሪ ግብ ለማግኘት ጥረቶችን ማድረግ ችለው ነበር ። 72ኛ ደቂቃ ላይ ከመስመር የተሻገረ ኳስ በረከት ሳሙኤል በግንባሩ ገጭቶ ወደ ግብ ቢሞክረውም በፅዮን መርዕድ ተይዞበታል ።

በፈጣን ሽግግር ግብ ለማግኘት ሲሄዱ የነበሩት ወላይታ ድቻዎች 81ኛ ደቂቃ ላይ በምንይሉ ወንድሙ ባስቆጠረው ግብ 4 ለ 2 መምራት ቻሉ ። በቀሪዎቹ ደቂቃዎች ሰበታ ከተማዎች ተጭነው መጫወት ቢችሉም ግብ ማስቆጠር ሳይችሉ ጨዋታው በጦና ንቦቹ 4 ለ 2 አሸናፊነት ተጠናቀቀ ።

ውጤቱን ተከትሎም ወላይታ ድቻ በ12 ነጥብ የደረጃ ሰንጠረዡ አናት ላይ ሲቀመጥ ሰበታ ከተማ በነበረበት 3 ነጥብ ላይ የሚቆይ ይሆናል ።

Writer at Hatricksport

Facebook

Habtamu Mitku

Writer at Hatricksport