የጨዋታ ዘገባ | የሸገር ደርቢ በፈረሰኞቹ የበላይነት ተጠናቋል

በርካታ አወዛጋቢ ክስተቶችን ያስተናገደው 43ኛው የሸገር ደርቢ በቅዱስ ጊዮርጊስ የ4 ለ 1 ድል ፍፃሜውን አግኝቷል ።

ጨዋታው ምሽት 12 ሰዓት በሀዋሳ ዩኒቨርስቲ ስታድየም ሲጀምር በበርካታ ደጋፊዎች ታጅቦ ነበር የተካሄደው ።

በጨዋታው በሁለቱም በኩል በቋሚ አሰላለፍ ከመጀመሪያ የሊግ ጨዋታቸው የተወሰኑ ለውጦች የነበሩ ሲሆን በቅዱስ ጊዮርጊስ በኩል ሶስት እንዲሁም በኢትዮጵያ ቡና በኩል ተመሳሳይ ቁጥር ያላቸው ቅያሪዎች ነበሩ ።

በመጀመሪያው የጨዋታ አጋማሽ ቡናማዎቹ በተለመደው ኳስን ከኋላ መስርቶ በመጫወት ላይ ያተኮረ የጨዋታ ዘይቤ በመጠቀም የጀመሩ ሲሆን ወደ ፊት ሄደው ተቃራኒ ተጋጣሚ ላይ ጫና በመፍጠር ረገድ ግን ሲቸገሩ ታይተዋል ። በፈረሰኞች በኩል ኳሶችን በክንፍ በኩል ለሚገኙት ተጫዋቾች በማድረስ ለማጥቃት ጥረትን አድርገዋል ። 20ኛው ደቂቃ ላይ የጨዋታውን የመጀመሪያ ግብ ቅዱስ ጊዮርጊሶች በአጨቃጫቂ ሁኔታ አስቆጠሩ ። የቡናው ተከላካይ አበበ ጥላሁን ህመም ተሰምቶት የህክምና ዕርዳታ ለማግኘት በሚል በእግሩ ስር የነበረችውን ኳስ ወደ ውጪ አወጣት ። የህክምና ዕርዳታ ከተደረገለት በኋላ ቡልቻ ሹራ በእጁ ወርውሮ ለሀይደር ሸረፋ ያቀበለው ሲሆን ሀይደርም ኳሱን ወደ ቡና የግብ ክልል ቀለል አድርጎ በሚመታበት ጊዜ የቅዱስ ጊዮርጊሱ ቶጎአዊ አጥቂ እስማኤል ኦጎሮ ሮጦ በመድረስ ግብ አደረጋት የዕለቱ ዳኛም ግቧን አፅድቋታል ።

በግቧ መፅደቅም የቡና ተጨዋቾች ከዳኛው ጋር ለደቂቃዎች የተከራከሩ ሲሆን ወደ ጨዋታው ተመልሰውም በተለይም በግራ ክንፍ ላይ በመጫወት ላይ በነበረው በአቡበከር ናስር በኩል ጫናዎችን ለመፍጠር ሞክረዋል ። 43ኛ ደቂቃ ላይ አቡበከር ናስር በሳጥኑ አቅራቢያ ያገኘውን የቅጣት ምት ወደ ግብ በጥሩ ሁኔታ ቢሞክረውም የግቡን አግዳሚ መትቶ ወደ ውጪ ወቶበታል ። ወደ መጀመሪያው አጋማሽ መጠናቀቂያ ቡናማዎቹ ከፍተኛ ጫና መፍጠር ቢችሉም ግብ ማግኘት ግን አልቻሉም በተለይም 46ኛው ደቂቃ ላይ ታፈሰ ሰለሞን ከግራ መስመር ወደ ግብ አሻምቶት የነበረውን አቡበከር ናስር እና ሮቤል ተክለሚካኤል ለማግኘት ቢሞክሩም ኳሱ አምልጧቸዋል ። የጨዋታው የመጀመሪያ አጋማሽም በቅዱስ ጊዮርጊስ 1 ለ 0 መሪነት ተጠናቀቀ ።

የሁለተኛው አጋማሽ ተጀምሮ ገና ሁለት ደቂቃ እንኳን ሳይሞላው በቡና ተከላካዮች ስህተት የተገኘውን ኳስ ተጠቅሞ ቡልቻ ሹራ የፈረሰኞቹን ሁለተኛ ግብ ማስቆጠር ቻለ ።

ከግቧ በኋላም ቡናማዎቹ ኳስን መስርተው ለመውጣት በሚሞክሩበት ጊዜ ቅዱስ ጊዮርጊሶች በቁጥር በዛ ብለው ወደ ተጋጣሚ ሜዳ በመግባት እና ጫና በመፍጠር በቀላሉ ኳሶችን የራሳቸው ያደርጉ ነበር ።

በጨዋታው 59ኛ ደቂቃ ላይ የጨዋታውን ውጤት ያጠበበች ግብ በቡና በኩል ተቆጠረ ። አቤል ያለው በታፈሰ ተስፋዬ ላይ ጥፋት ሰርቷል በሚል የመሀል ዳኛው ለቡና የቅጣት ምት የሰጡ ሲሆን በወቅቱ የፊት አጥቂው እንዳለ ደባልቄ አቤልን በመማታቱ ትንሽ አለመግባባቶች ተፈጥረው ነበር በዚህም ሁለቱም ተጨዋቾች የቢጫ ካርድ ተመልክተዋል ።

የቅጣት ምቱንም ታፈሰ ተስፋዬ አሻምቶት ግብ ጠባቂው ባህሩ ጥላሁን ወጥቶ ለመያዝ ሞክሮ ያመለጠውን ኳስ ተጠቅሞ እንዳለ ደባልቄ ግብ አስቆጠረ ። ከዚህ ግብ በኋላ ጨዋታው ግለቱ ጨመሮ ተካሂዷል ። ቀደም ብሎ ከነበረው እንቅስቃሴም በተሻለ መልኩ ቡናዎች ወደ ፊት ለመሄድ ቢሞክሩም የፈረሰኞቹን የተከላካይ መስመር አልፈው የግብ ሙከራ ለማድረግ አልቻሉም ።

78ኛው ደቂቃ ላይ በፈጣን የአጥቂ መስመር ተጨዋቾቻቸው በመልሶ ማጥቃት ወደ ፊት የሄዱት ቅዱስ ጊዮርጊሶች ሶስተኛውን ግብ አስቆጠሩ ። ግቧንም ከአማኑኤል ገብረሚካኤል የደረሰውን ኳስ ተቀብሎ ተከላካዮች በግሩም ሁኔታ በመሸወድ አምበሉ ሀይደር ሸረፋ ሊያስቆጥር ችሏል ።

በ83ኛው ደቂቃ ላይ በፍፁም ቅጣት ምት ክልል ውስጥ ሀይሌ ገብረትንሳኤ ደስታ ደሙ ላይ በሰራው ጥፋት ምክንያት ፈረሰኞቸለ የፍፁም ቅጣት ምት አገኙ ።

የፍፁም ቅጣት ምቱንም የ3ኛው ግብ አስቆጣሪ ሀይደር ሸረፋ አስቆጥሮ የጨዋታውን ውጤት ወደ 4 ለ 1 ቀየረው ። በቀሩት ደቂቃዎች ግብ ለማስቆጠር የጣሩት ቡናማዎቹ 90+4 ደቂቃ ላይ አቡበከር ናስር ከሞከረው የቅጣት ምት ውጪ ይህ ነው የሚባል ከባድ ሙከራ ሳያደርጉ ጨዋታው ተጠናቀቀ ።

Writer at Hatricksport

Facebook

Habtamu Mitku

Writer at Hatricksport