የጨዋታ ዘገባ | መከላከያ ሁለተኛ ድሉን አስመዝግቧል

በቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ሁለተኛ ሳምንት የመጨረሻ ቀን ውሎ በመጀመሪያው ጨዋታ ሰበታ ከተማን ከመከላከያ አገናኝቶ በዮሀንስ ሳህሌ የሚመራው መከላከያ በአቤል ነጋሽ ብቸኛ ግብ 1 ለ 0 አሸንፎ ወቷል ።

ቀን 9 ሰዓት ላይ በተጀመረው ጨዋታ በሰበታ ከተማ በኩል ቅዱስ ጊዮርጊስን ከገጠመው ቡድን 2 ቅያሪ አድርገው የገቡ ሲሆን በመከላከያ በኩልም በተመሳሳይ አርባ ምንጭ ከተማን ካሸነፍው ቡድን 2 ቅያሪዎችን አድርገዋል ።

በጨዋታው የመጀመሪያ አጋማሽ በኳስ ቁጥጥሩ ሰበታ የተሻለ የነበረ ሲሆን ወደ ግብ ቀርቦ የግብ ሙከራ በማድረግ ረገድ ግን መከላከያዎች የተሻሉ ነበሩ ።

16ኛው ደቂቃ ላይ ሰበታ ከተማ መሪ መሆን የሚችልበትን ዕድል አግኝቶ ሳይጠቀምበት ቀርቷል ። ከቅጣት ምት የተሻገረውን ኳስ ናንጄቦ አግኝቶ ቢሞክረውም የግቡ ቋሚ መልሶት በጦሩ ተከላካይ ኢብራሂም ሁሴን እግር ስር ገብቶ በድጋሚ ቋሚውን መልሶ ሊወጣ ችሏል ።

በ25ኛው ደቂቃ ላይ ሰበታ ከተማ አግኝቶት የነበረው የማዕዘን ምትን ወደ መልሶ ማጥቃት በመቀየር የመከላከያው የክንፍ ተጫዋች ሰመረ ሀፍተይ በፍጥነት ይዞ ቢያድግልኝ ኤልያስንም በማለፍ ለግቡ ቀርቦ ያደረገው ሙከራ በግቡ አግዳሚ ተመልሶበት ሊወጣ ችሏል ። ኳሱን ይዘው ወደ ፊት በመሄድ በንፅፅር ጥሩ የነበሩት ሰበታ ከተማዎች በ34ኛው ደቂቃ ላይ ጌቱ ሀይለማሪያም ያሻማውን ኳስ ፍፁም ገብረማርያም በጭንቅላት ገጭቶት ግብ ጠባቂው በመውጣቱ ምክንያት ሊቆጠር ቢቃረብም አሌክስ ተሰማ ደርሶ ግብ ከመሆን አድኖታል ።

የመጀመሪያው አጋማሽም ያለምንም ግብ ተጠናቀቀ ።
በሁለተኛው አጋማሽ የነበረው የጨዋታ ፍሰት በብዛት በሰበታ ከተማ ብልጫ የቀጠለ ነበር ። ነገር ግን በግብ ሙከራ 74ኛ ደቂቃ ላይ ፍፁም ገብረማርያም በሳጥን ውስጥ የደረሰውን ኳስ ጠንከር አድርጎ ወደ ግብ ባለመላኩ በግብ ጠባቂው ክሌመንት ቦዬ በቀላሉ ተይዞበታል ።

ከአንድ ደቂቃ በኋላ በመከላከያ በኩል በፈጣን እንቅስቃሴ በመሀረድ ኦኩቱ ኢማኑኤል ከክንፍ ሳጥን ውስጥ ለነበረው አዲሱ አቱላ ቢያቀብለውም ኳሱን ቀለል አድርጎ ወደ ግብ በመምታቱ ለአለም ብርሀኑ በቀላሉ ሊቆጣጠረው ችሏል ።

78ኛው ደቂቃ ላይ የጨዋታውን ውጤት የቀየረች ግብ በመከላከያ በኩል ልትቆጠር የቻለች ሲሆን ተቀይሮ የገባው አቤል ነጋሽ ከኦኩቱ ኢማኑኤል የደረሰውን ኳስ ከፍፁም ቅጣት ምት ክልል ውጪ አክርሮ በመምታት ጦሩን መሪ ያደረገ ግብ አስቆጠረ ።

ከግቡ መቆጠር በኋላ ባሉ ደቂቃዎች መከላከያዎች ጨዋታውን ተቆጣጥረው ብቸኛዋን ግብ በማስጠበቅ ሶስት ነጥብ ይዘው መውጣት ችለዋል ። መከላከያ ውጤቱን ተከትሎ ከባህርዳር ከተማ እና ከፋሲል ከተማ ቀጥሎ ሁለቱንም ጨዋታዎች ማሸነፍ የቻለ ሶስተኛ ክለብ መሆን ችሏል ።

Writer at Hatricksport

Facebook

Habtamu Mitku

Writer at Hatricksport