የጨዋታ ዘገባ | ሲዳማ ቡና እና ሰበታ ከተማ ያደረጉት ጨዋታ በአንድ አቻ ውጤት ተጠናቋል

በሊጉ የአራተኛ ሳምንት የመጨረሻ ቀን በመጀመሪያ ጨዋታ የተገናኙት ሲዳማ ቡና እና ሰበታ ከተማ ከቆሙ ኳሶች በተቆጠሩ ግቦች ጨዋታቸውን በ1 ለ 1 ውጤት አጠናቀዋል ።

ሁለቱም ተጋጣሚዎች በሶስተኛ ሳምንት ጨዋታቸው ከተጠቀሙት ቋሚ 11 ሶስት ሶስት ለውጦችን ያደረጉ ሲሆን ሲዳማ ቡናዎች ጊት ጋትጉት ፤ ሙሉአለም መስፍንን እና ዳዊት ተፈራን ሰበታ ከተማዎቾ ደሞ ቢያድግልኝ ኤልያስ ፤ ዮናስ አቡሌን እና ዘላለም አሳይያስን ወደ ቋሚ አሰላለፉ አስገብተው ጨዋታቸውኖ ጀምረዋል ።

በጨዋታው ጅማሮ ሲዳማ ቡናዎች በተሻለ ሁኔታ በመንቀሳቀስ ቢጀምሩም ቀስ በቀስ ወደ ጨዋታው የተመለሱት ሰበታ ከተማዎች ጥሩ እንቅስቃሴን ማድረግ ችለው ነበር ።

በጨዋታው 13ኛ ደቂቃ ላይ የሲዳማ ቡና ተከላካዮችን ስህተት ተጠቅሞ ዘካርያስ ፍቅሬ ለማስቆጠር ቢሞከርም በግብ ጠባቂው ተክለማርያም ሻንቆ ተመልሶበታል ። ቀስ በቀስ ሲዳማ ቡናዎች የኳስ ቁጥጥር ብልጫ በተወሰነ መልኩ ብልጫ ቢወስድባቸውም በመልሶ ማጥቃት ረጃጅም ኳሶችን በመጠቀም የግብ ዕድሎችን ለመፍጠር ጥረቶችን አድረዋል ።

23ኛው ደቂቃ ላይ ቴዎድሮስ ታፈሰ ከመሀል ሜዳው አካባቢ በአየር ላይ ያሻገረውን ኳስ ፍሬው ሰለሞን በጭንቅላቱ ወደ ግብ ቢልከውም ኢላማውን ሳይጠብቅለት ቀርቷል ። በ32ኛው ደቂቃ ላይም ከግራ መስመር ወደ ገብ ክልሉ በመሬት የተላከውን ኳስ ፍሬው ሰለሞን መትቶ አስቆጠረው ሲባል ከግቡ አናት በላይ ልኮታል ። ከሁለት ደቂቃዎች በኋላ የሰበታ ከተማው አጥቂ ጁልያስ ናንጄቦ ነፃ ሆኖ አግኝቶ ቢሞክረውም ወደ ውጪ ወቶበታል ።

ብዙም የግብ ሙከራዎችን ያለሳየን የመጀመሪያው አጋማሽ ያለ ምንም ግብ ተጠናቀቀ ።

የሁለተኛው አጋማሽ ከጅምሩ በሁለቱም በኩል ወደ ፊት በመሄድ ረገድ ፈጣን እንቅሰቃሴዎችን አስመልክቶ 49ኛ ደቂቃ ላይ የመጀመሪያው ግብ ሊቆጠር ችሏል ።

በቀኝ መስመር ላይ የተገኘውን የቅጣት ምት ሰለሞን ሀብቴ ወደ ግብ ሲልከው ሀብታሙ ገዛኸኝ በጭንቅላቱ ጨርፎ ሲዳማ ቡናን ቀዳሚ ያደረገች ግብ አስቆጠረ ። ከግቧ መቆጠር በኋላ ሰበታ ከተማ በተሻለ መልኩ ኳሱን በመቆጣጠር እና ጫና ፈጥረው በመጫወት የግብ ዕድሎችን ለመፍጠር ሞክረዋል ። በሲዳማ ቡና በኩል በተፈጠረባቸው ጫና በራሳቸው ሜዳ በዛ ብለው ቢታዩም አልፎ አልፎ ረጃጅም ኳሶችን በመጠቀም ወደ ግብ ለመድረስ ሙከራዎችን አድርገዋል ።

75ኛው ደቂቃ ላይ ዘላለም ኢሳይያስ ከረጅም ርቀት ከቅጣት ምት ያሻገረውን ኳስ ተቀይሮ የገባው ፍፁም ገብረማርያም በጭንቅላቱ በመግጨት ለሰበታ ከተማ ግብ አስቆጠረ ። ከሁለት ደቂቃዎች በኋላም ግብ አስቆጣሪው ፍፁም በእንቅስቃሴ በረጅሙ የተሻገረለትን ኳስ አግኝቶ በድጋሚ በጭንቅላት ለማስቆጠር ቢሞክርም የግቡ አግዳሚ መልሶበታል ።

ከአቻነቷ ግብ በኋላ በኳስ ቁጥጥሩ እና ወደፊት በመሄድ ሲዳማ ቡናዎች ተሽለው ቢታዩም ሰበታ ከተማዎች የሚያገኟቸውን ኳሶች በፍጥነት ወደ ግብ ክልል በመውሰድ ሁለተኛ ግብ ለማስቆጠር ጥረቶችን አድርገዋል ። 84ኛው ደቂቃ ላይ በግራ መስመር የደረሰውን ኳስ ወደ ሳጥን ይዞ የገባው ጁልያስ ናንጄቦ ኳሱን ወደ ግብ ለመምታት በሚዘጋጅት ወቅት ግርማ በቀለ ደርሶ ሊያወጣበት ችሏል ።


ሲዳማ ቡናዎች በመጨረሻዎቹ ደቂቃዎች ቀደም ብሎ ከነበረው በተሻለ ወደ ፊት ለመሄድ ቢሞከሩም ግብ ማግኘት ግን አልቻሉም ። ጨዋታውም በ1 አቻ ውጤት ፍፃሜውን አገኘ ።

በዚህም መሰረት ሲዳማ ነጥቡን ወደ አምስት ሲያሳድግ ሰበታ ከተማ ደግሞ ነጥቡን ሶስት ማድረስ ችሏል ።

Writer at Hatricksport

Facebook

Habtamu Mitku

Writer at Hatricksport

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *