የጨዋታ ዘገባ | ቅዱስ ጊዮርጊስ እና መከላከያ ጨዋታቸውን ያለምንም ግብ አጠናቀዋል

በሊጉ የአራተኛ ሳምንት የመጨረሻ ጨዋታ የተገናኙት መከላከያ እና ቅዱስ ጊዮርጊስ ምንም ግብ ሳያስቆጥሩ በ 0 ለ 0 ውጤት ሙሉ ዘጠና ደቂቃውን አጠናቀዋል ።

ሁለቱ ክለቦች በሶስተኛ ሳምንት ጨዋታዎቻቸው ከተጠቋሙት ቋሚ አሰላለፍ የተወሰኑ ቅያሪዎችን ያደረጉ ሲሆን መከላከያ አለምአንተ ካሳን ፤ ብሩክ ሰሙን እና ቢንያም በላይን ቅዱስ ጊዮርጊስ ደግሞ ሱሌይማን ሀሚድን ፤ ከነአን ማርክነህን እና አማኑኤል ገብረሚካኤልን ወደ ቋሚ አሰላለፍ በማስገባት ጨዋታውን ጀምረዋል ።

በጨዋታው የመጀመሪያ ደቂቃዎች ቅዱስ ጊዮርጊሶች ወደ ፊት በመሄድ ረገድ የተሻለ መንቀሳቀስ ችለው ነበር ። ነገር ግን ደቂቃዎች እየገፉ ሲሄዱ መከላከያዎች በአንዳንድ አጋጣሚዎች ለግብ የቀረቡ ሙከራዎችን ማድረግ ችለው ነበር ።

ገና በጨዋታው ጅማሮ 2ኛ ደቂቃ ላይ አቤል ያለው ከአማኑኤል ገብረሚካኤል የደረሰውን ኳስ በሳጥን ውስጥ ይዞ ገብቶ ቢመታውም ኳሱ ላይ ደርሶ የነበረው ከነአን ማርክነህ ሳይጠቀምበት ቀርቷል ። ከሶስት ደቂቃዎች በኋላም አማኑኤል ገብረሚካኤል ከቡልቻ ሹራ የተሻገረለትን ኳስ በጭንቅላት ቢገጨውም ለጥቂት ከግቡ አናት በላይ ወቷል ።

በ15ኛው ደቂቃ ላይ መከላከያ በቢንያም በላይ አማካኝነት ከሳጥኑ ጫፍ የመታውን ኳስ የፈረሰኞቹ ግብ ጠባቂ ቻርለስ ሉክዋጎ መልሶበታል ። ከሶስት ደቂቃዎች በኋላ ከቀኝ መስመር ከቅጣት ምት የተሻገረውን ኳስ ኡኩቱ ኢማኑኤል በግንባሩ ገጭቶ ወደ ግብ ቢሞክረውም ለጥቂት የግቡን አግዳሚ ታኮ ሊወጣበት ችሏል ። ጥሩ ጥሩ የግብ ዕድሎችን መፍጠር የቻሉት መከላከያዎች 23ኛ ደቂቃ ላይ ኡኩቱ ኢማኑኤል ከግብ ጠባቂው ጋር ፊት ለፊት ቢገናኝም ሉክዋጎ ወጥቶ መልሶበታል ። ጨዋታው 34ኛ ደቂቃ ላይ ሲደርስ የመከላከያው ግብ ጠባቂ ቦዬ በረጅም የመታው ኳስ የቅዱስ ጊዮርጊስ ተከላካዮችን አልፎ ግሩሜ ሀጎስ አግኝቶ በሳጥን ገብቶ ቢሞክረውም በድጋሚ ቻርለስ ሉክዋጎ አድኖታል ።

በግብ ሙከራ ረገድ ደከም ብለው የታዩት ፈረሰኞቹ 41ኛ ደቂቃ ላይ በፈጣን እንቅስቃሴ ከግራ መስመር በመነሳት ከነአን ማርክነህ ወደ ሳጥን ይዞ ገብቶ ቢሞክረውም ኢላማውን ሳይጠብቅ ቀርቷል ።

የመጀመሪያ የጨዋታ አጋማሽ ሊጠናቀቅ ተጨማሪ ደቂቃላይ እያለ አማኑኤል ገብረሚካኤል ወደ ግብ የላከው ኳስ ግብ ጠባቂውን አልፎ ፍሪምፖንግ ሜንሱ ቢያገኘውም ወደ ግብ ሳይመታው በቦዬ በደረሰበት ጫና ኳሱን ሳይጠቀምበት ቀርቷል ።

የሁለተኛው አጋማሽ በአብዛኛው የፈረሰኞቹ ፍፁም የበላይነት የታየበት ነበር ። ፈረሰኞቹ በተደጋጋሚ ወደ መከላከያ ግብ ክልል ደርሰው በተለያዩ አጋጣሚዎች ጥሩ ሙከራዎችን ቢያደርጉም በአጨራረስ ድክመት እና በግብ ጠባቂው ቦዬ ብቃት ግብ ለማስቆጠር ተቸግረዋል ።

የአጋማሹ የመጀመሪያ ኢላማውን የጠበቀ የግብ ሙከራ የተደረገው በ62ኛ ደቂቂ በእስማኤል ኦጎሮ አማካኝነት ነበር ። በተጠቀሰው ደቂቃ በሳጥኑ የግራ መስመር አካባቢ የተገኘውን ኳስ ኦጎሮ በግሩም ሁኔታ ወደ ግብ ቢልከውም ግብ ጠባቂው ተቆጣጥሮታል ። በ76ኛው ደቂቃ ላይ ከማዕዘን የተነሳውን ኳስ ያብስራ ተስፋዬ ለግቡ አቅራቢያ ለነበረው ከነአን አድርሶት ተጫዋቹ ተረጋግቶ ጠንከር አድርጎ ወደ ግብ ቢሞክረውም በድጋሚ በግብ ጠባቂው ተመልሶበታል ።

በጨዋታው የመጨረሻ ደቂቃዎች ላይ ወደ ኋላ አፈግፍገው የነበሩት መከላከያዎች በተወሰነ መልኩ ወደ ፊት ለመሄድ ቢሞክሩም ያን ያህል የሚባል የግብ ሙከራ ሳያደርጉ ጨዋታው ያለምንም ግብ 0 ለ 0 ተጠናቋል ።

በዚህም መሰረት መከላከያ ነጥቡን ወደ ሰባት ሲያሳድግ ቅዱስ ጊዮርጊስ በበኩሉ ነጥቡን ስድስት ማድረስ ችሏል ።

Writer at Hatricksport

Facebook

Habtamu Mitku

Writer at Hatricksport

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *