በዕለቱ የተካሄደው ሁለተኛ ጨዋታ በበርካታ ድራማዊ ትዕይንቶች የታጀበ ሲሆን አምሰት ግቦች አምሰት የፍፁም ቅጣት ምቶች አንድ የቀይ ካርድ በተመዘገበበት ጨዋታ ሀዋሳ ከተማ መከላከያን 3 ለ 2 በሆነ ውጤቶ አሸንፏል ።
በ13ኛው ሳምንት ጨዋታ ሀዋሳ ከተማ ፋሲል ከተማን ሲረታ በቋሚ አሰላለፍ ከነበሩተ ተጫዋቾች ሁለት ቅያሪ ያደረጉ ሲሆን በወንድማገኝ ማዕረግ እና ተባረክ ሄፌሞ ምትክ አዲስአለም ተስፋዬን እና ብሩክ በየነን ያሰለፉ ሲሆን በመከላከያ በኩል አዳማ ከተማን ካሸነፉበት ምርጥ 11 አኔድ ለውጥ ብቻ ያደረጉ ሲሆን ገናናው ረጋሳን በኢብራሂም ሁሴን ተክተው ጨዋታቸውን ጀምረዋል ።
በጨዋታው የመጀመሪያ አጋማሽ በሁለቱም በኩል ቶሎ ቶሎ ወደ ተጋጣሚ የግብ ክልል በመድረስ ግቦችን ለማግኘት ጥረት ያደረጉበት ሲሆን በመጀመሪያዎቹ ደቂቃዎች ላይ በተወሰነ መልኩ ሀይቆቹ በኳስ ቁጥጥሩ ብልጫ በመውሰድ የመከላከያን የተከላካይ ክፍል ለመፈተን ችለዋል ።
12ኛው ደቂቃ በዳንኤል ደርቤ አማካኝነት ከቅጣት ምት ወደ ግብ የተሻገረውን ኳስ አዲስአለም ተስፋዬ በግንባር በመግጨት ሀይቆቹን ቀዳሚ አድርጓል ። የግብ ዕድል በመፍጠሩ ደከም ብለው የነበሩት መከላከያዎች 23ኛ ደቂቃ ላይ በላርዬ ኢማኑኤል አማካኝነት በግንባር ተገጭቶ በመሀመድ ሙንታሪ ከተመለሰበት ኳስ ሌላ ለግብ የቀረበ ሙከራ ለማድረግ ተቸግረው ነበር ።
29ኛው ደቂቃ ላይ በፋሲል ከተማው ጨዋታ ላይ የማሸንፊያውን ግብ ባስቆጠረው ወንድማገኝ ሀይሉ ላይ ዳዊት ማሞ በሰራው ጥፋት ምክንያት ሀዋሳ ከተማዎች ያገኙትን የፍፁም ቅጣት ምት ብሩክ በየነ 31ኛው ደቂቃ ላይ አስቆጥሮ የሀዋሳ ከተማን መሪነት ከፍ ማድረግ ችሏል ።
ከአምሰት ደቂቃዎች በኋላ ደግሞ በመከላከያ በኩል ከማዕዘን የቸሻገረውን ኳስ ቢንያም በላይ ለግቡ ቅርብ ሆኖ ለማስቆጠር ሲሞክር በላርዬ ኢማኑኤል ጥፋት ተሰርቶበት ያገኙትን የፍፁም ቅጣት ምት ኦኩቱ ኢማኑኤል አስቆጥሯል ። የጨዋታው የመጀመሪያ አጋማሽም በሀዋሳ ከተማ 2 ለ 1 መሪነች ተጠናቋል ።
ሁለተኛው አጋማሽ ገና ከጅምሩ ግብ ያስተናገደ ነበር ተቀይሮ የገባው ሰመረ ሀፍተይ የግበሰ ጠባቂውን መሀመድ ሙንታሪ ስህተት ተጠቅሞ 47ኛው ደቂቃ ግብ በማስቆጠር ክለቡን ከ2 ለ 0 መመራት 2 እኩል እንዲሆን አድርጓል ። ከሁለት ደቂቃዎች በኋላም መከላከያዎች ከማዕዘነሰ በተነሳ ኳስ ግብ ለማስቆጠር ያደረጉት ጥረት በመሀመድ ሙንታሪ ሊመክን ችሏል።
ጨዋታው ወደ ሁለት እኩል ከተቀየረ በኋላ በሁለቱም ክለቦች በኩል የነበረው በጨዋታው ላይ ውጤት ይዞ የመውጣት ፍላጎት የጨዋታውን ግለት ከፍ ያደረገ ነበር ። 57ኛው ደቂቃ ላይ ኤፍሬም አሻሞ በመከላከያ ሳጠን ውሰጥ ሆኖ ለማቀበል የሞከረው ኳስ ምንም እንኳን ላርዬ ኢማኑኤል በእጁ ባይነካውም የዕለቱ የመሀል ዳኝ ለሀዋሳ ከተማ የፍፁም ቅጣት ምት ሰጥተዋል ። የፍፁም ቅጣት ምቱንም መስፍን ታፈሰ በመሀመድ ሙንታሪ መረብ ላይ አሳርፎታል ።
74ኛው ደቂቃ ላይ የሀዋሳ ከተማው ተከላካይ ላውረንስ ላርቴ ሆን ብሎ ኳስ በእጅ መንካቱን ተከትሎ በሁለተኛ የቢጫ ካርድ ከሜዳ ተሰናብቷል ። መደበኛው የጨዋታ ክፍለ ጊዜ ሊጠናቀቅ አራት ያህል ደቂቃዎች ሲቀሩት የሀዋሳ ከተማው ተከላካይ ፀጋሰው ድማሙ በኦኩቱ ኢማኑኤል ላይ በሰራው ጥፋት መከላከያዎቹ ዳግም አቻ መሆን የሚችሉበተን የፍፁም ቅጣት ምት ማግኘት ቢችሉም ቢንያም በላይ የመታው ኳስ በመሀመድ ሙንታሪ ተመልሷል ።
ከሁለት ደቂቃዎች በኋላም በጨዋታው አምስተኛው ለሀዋሳ ከተማ ደግሞ ሶስተኛ የፍፁም ቅጣት ምት አሌክስ ተሰማ በሳጥን ውሰጥ ኳስ በእጅ በመንካቱ ምክንያት የተሰጠ ቢሆንም ተቀይሮ የገባው ተባረክ ሄፌሞ የመታው የፍፁም ቅጣት ምት በክሌመንት ቦዬ ተመልሷል ። በመጨረሻም የጨዋታው ውጤት ሀዋሳ ከተማ 3 መከላከያ 2 ሆኖ ተፈፅሟል ።
ውጤቱን ተከትሎ ሀዋሳ ከተማ ነጥቡን 26 በማድረስ 2ኛ ደረጃውን መልሶ ሲረከብ መከላከያ በ17 ነጥብ 10ኛ ደረጃ ላይ ለመቆየት ተገዷል ።
በ15ኛው ሳምንት ሀዋሳ ከተማ አዳማ ከተማን መከላከያ ደግሞ ጅማ አባጅፋርን የሚገጥሙ ይሆናል ።
አስተያየት ይስጡ