በቤትኪንግ ኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ 28ኛ ሳምንት የሁለተኛ ቀን ውሎ በሁለተኝነት በተደረገው ጨዋታ የሊጉ መሪ ቅዱስ ጊዮርጊስ በአማኑኤል ገብረሚካኤል ግብ ሲመራ ቢቆይም ኤፍሬም ዘካርያስ ባስቆጠረው ግብ ነጥብ ተጋርቶ ለመውጣት ተገዷል ።
ሀድያ ሆሳዕናዎች በ27ኛው ሳምንት በሰበታ ከተማ ነጥብ በተጋሩበት ጨዋታ ከነበረው የመጀመሪያ አሰላለፍ ሁለት ለውጦችን በማድረግ ፍሬዘር ካሳን እና አበባየሁ ዮሀንስን በቃልአብ ውብሸት እና በቅዱስ ጊዮርጊስ በኩል ደግሞ በሳምንቱ ወልቂጤ ከተማን በረቱበት ጨዋታ ላይ ከነበረው ምርጥ 11 አንድ ለውጥ ብቻ በማድረግ በአቤል ያለው ምትክ ዳግማዊ አርአያን አሰልፈዋል ።
የቀትር ሰባት ሰዓቱ ጨዋታ ገና ከጅምሩ በሁለቱም በኩል በፈጣን እንቅስቃሴዎች የተጀመረ እና ደቂቃዎች እየገፉ በመጡ ቁጥር ደግሞ ቅዱስ ጊዮርጊሶች በኳስ ቁጥጥሩም ሆነ የግብ ዕድሎችን በመፍጠሩ ረገድ ጥሩ እንቅስቃሴን ማድረግ የቻሉበት ነበር ።
ፈረሰኞቹ በተለይም ከመስመር እና ከቆሙ ኳሶች የሀድያ ሆሳዕናን መረብ ለማግኘት ጥረት አድርገዋል ። ነገር ግን ፈታኝ የሆነ እና ለግብ የቀረበ ሙከራ ለማድረግ እስከ 29ኛው ደቂቃ መጠበቅ የግድ ብሏቸው ነበር ።
- ማሰታውቂያ -
በተጠቀሰው ደቂቃ ላይ በረከት ወልዴ ከርቀት አክርሮ ወደ ግብ የመታው ኳስ በመሳይ አያኖ እና በግቡ አግዳሚ ግብ ከመሆን ድኗል ። ከውሀ እረፍት መልስ በተሻለ የግብ ዕድሎችን መፍጠር የቻሉት ፈረሰኞቹ በ36ኛው ደቂቃ ላይ ድካማቸው ፍሬ አፍርቷል ።
ሱሌማን ሀሚድ ከፍሪምፖንግ ኤድዊን በረጅም የደረሰውን ኳስ ወደ ግብ ሲያሻግረው ያገኘው አማኑኤል ገብረሚካኤል በግንባር ገጭቶ በመሳይ አያኖ መረብ ላይ አሳርፎ ቅዱስ ጊዮረሰጊስን መሪ አድርጓል ።
በግቡ የተነቃቁት ፈረሰኞቹ አጋማሹ ከመጠናቀቁ በፊት በነበሩ ደቂቃዎች ላይ ተጨማሪ የግብ ዕድሎችን መፍጠር ሲችሉ በሀድያ ሆሳዕና በኩል ግን አብዛኛው ጊዜ በራሳቸው ሜዳ ከማሳለፋቸው ባለፈ ወደ ተጋጣሚያቸወች የግብ ክልል ደርሰው የግብ ሙከራዎችን ማድረግ ሳይችሉ ነበር ወደ ዕረፍት ያመሩት ።
በ41ኛው ደቂቃ ላይ ሄኖክ አዱኛ በሳጥኑ የግራ አቅጣጫ ፈጥኖ በመግባት ከከነአን ማርክነህ የደረሰውን ኳስ በጠንካራ ምት ወደ ግብ መላክ ቢችልም ሙከራው ኢላማውን የጠበቀ አልነበረም ። ከአራት ደቂቃዎች በኋላ ደግሞ ሄኖክ አዱኛ ከማዕዘን ያሻገረው እና ቸርነት ጉግሳ በግንባር ገጭቶ ወደግብ የላከው ኳስ በፍሬዘር ተጨርፎ ከመረብ ሊያርፍ ሲል መሳይ አያኖ በድንቅ ብቃት ግብ ከመሆን አድኖታል ።
የሁለተኛው አጋማሽ የጨዋታ ክፍለ ጊዜ ጅማሮ ላይ ፈረሰኞቹ በአማኑኤል ገብረሚካኤል አማካኝነት በሁለቱ መስመሮች በኩል የግብ አጋጣሚዎችን ለመፍጠር ያደረጓቸው ጥረቶች ሳይሳኩ ቀርተዋል ።
በአጋማሹ ከመጀመሪያው በተሻለ ከሜዳ ክፍላቸው ወጥተው የግብ ዕድሎቾን ለመፍጠር የሞከሩት ሀድያ ሆሳዕናዎች በተከታታይ በ57 እና 59ኛ ደቂቃ ላይ ጥሩ ጥሩ የግብ ሙከራዎችን ማድረግ ችለው ነበር ። በ57ኛው ደቂቃ ላይ ከእጅ ውርወራ የተነሳን ኳስ ፍቅረየሱስ ተክለብርሃን በቀኝ አቅጣጫ ላይ ሁለት የቅዱስ ጊዮርጊስ ተጫዋቾችን አልፎ ከግብ ጠባቂው ጋር ፊት ለፊት ተገናኝቶ ያደረገው የግብ ሙከራ የግቡን አግዳሚ ለትሞ ወጥቷል ።
ከሁለት ደቂቃዎች በኋላም ከቅጣት ምት ሄኖክ አርፊቹ ወደ ግብ ያሻገረውን ኳስ ባዬ ገዛኸኝ በግንባር ገጭቶ የፈረሰኞቹ የግብ ዘብ ቻርስስ ሉክዋጎ ግብ ከመሆን አድኖታል ።
ፈረሰኞቹ በተለይም በመስመር ባደሉ የማጥቃት እንቅስቃሴዎቻቸው ወደ ሀድያ ሆሳዕና የግብ ክልል ለመድረስ የጣሩ ሲሆን በ66ኛው ደቂቃ በማኑኤል ገብረሚካኤል አማካኝነት እጅግ በጣም ለግብ የቀረበ ሙከራ ማድረግ ችለው ነበር ። ግብ አስቆጣሪው ተጫዋች ከዳግም አርአያ የደረሰውን ኳስ በግሩም ሁኔታ ኢያሱ ታምሩን አልፎ በመሳይ አያኖ እግሮች መሀል ወደ ግብ ቢልከውም ፍሬዘር ካሳ ከመስመር ላይ አውጥቶታል ።
ከሁለተኛው ውሀ እረፍት መልስ በአንፃራዊነት የተሻለ የማጥቃት እንቅስቃሴ ያደረጉት ሀድያ ሆሳዕናዎች በ80ኛው ደቂቃ ላይ የአቻነት ግብ አግኝተዋል ። ከማዕዘን የተሻገረውን ኳስ ተቀይሮ የገባው ኤፍሬም ዘካርያስ በግሩም ሁኔታ ከመረብ ላይ አሳርፎ ሀድያ ሆሳዕናን አቻ ማድረግ ችሏል ።
በቀጣዮቹ የመጨረሻ ደቂቃዎች ላይ የሊጉ መሪ የሆኑት ቅዱስ ጊዮርጊሶች በቁጥር በርከት ብለው በሀድያ ሆሳዕና የግብ ክልል በመገኘት ሁለተኛ ግብ ለማስቆጠር ጥረቶችን አድርገው ነበር ።
በ89ኛው ደቂቃ ላይ ሄኖክ አዱኛ ከቅጣት ምት ያሻገረውን ኳስ ተጨራርፎ ያገኘው ፍሪምፖንግ ሜንሱ በቀጥታ ወደ ግብ የመታውን ኳስ ብርሀኑ በቀለ የመለሰው ሲሆን ከሶስት ደቂቃዎች በኋላም በተመሳሳይ ከቅጣት ምት የተሻገረን ኳስ አማኑኤል ገብረሚካኤል አግኝቶ ግብ ለማድረግ ያደረገው ጥረት ሳይሳካ ቀርቷል ። በመጨረሻም በሃድያ ሆሳዕና በኩል ሀብታሙ ታደሰ ከሳጥን ውጪ ካደረገው ጠንካራ የግብ ሙከራ በኋላ ጨዋታው ተጠናቋል ።
ውጤቱን ተከትሎ ቅዱስ ጊዮርጊስ ነጥቡን 59 አድርሶ በመሪነቱ ሲቀጥል ፋሲል ከነማ ነገ ሀዋሳ ከተማን መርታት የሚችል ከሆነ የነጥብ ልዩነቱ ወደ አንድ ዝቅ የሚል ይሆናል ። ሀድያ ሆሳዕና በበኩሉ በ35 ነጥብ በነበረበት 8ኛ ደረጃ ላይ ለመቆየት ተገዷል ።
በ29ኛ ሳምንት ጨዋታዎች በመጪው ሰኔ 19 ( ዕሁድ ) 7:00 ላይ ሀድያ ሆሳዕና ወላይታ ድቻን ሲገጥም በተከታዩ ቀን 10:00 ላይ ቅዱስ ጊዮርጊስ ከአርባምንጭ ከተማ ይጫወታል ።