የስምንተኛ ሳምንት የሁለተኛ ቀን ውሎ የመጀመሪያ ጨዋታ በዛሬው ዕለት ሀድያ ሆሳዕናን ከ ድሬዳዋ ከተማ አገናኝቶ ሀድያ ሆሳዕናዎቹ ሁለት ጊዜ ከመመራት ተነስተው በመጨረሻም 3 ለ 2 በሆነ ውጤት አሸንፈው መውጣት ችለዋል ።
ሀድያ ሆሳዕና በሰባተኛው ሳምንት መከላከያን ባሸነፉበት ጨዋታ ከተጠቀሙት ቋሚ አሰላለፍ ሶስት ተጫዋቾችን በመቀየር ሶሆሆ ሜንሳህ ፤ ፀጋዬ ብርሀኑ እና ፍቅረየሱስ ተክለብርሃን ወደ ጨዋታው ሲያስገቡ በድሬዳዋ ከተማ በኩል ደግሞ በኢትዮጵያ ቡና በተሸነፉበት ጨዋታ ከነበረው ቋሚ አስራአንድ አንድ ቅያሪ ብቻ በማድረግ አብዱራህማን ሙባረክ ጨዋታውን እንዲጀምር ማድረግ ችለዋል ።

ጨዋታው ገና ከጅምሩ በአወዛጋቢ ውሳኔ የተጀመረ መሆን ችሏል ። በ2ኛው ደቂቃ ላይ መሀመድ አብዱለጢፍ ከግራ መስመር በመነሳት ወደ ሳጥን ለመግባት ሲሞክር በፍሬዘር ካሳ በተሰራበት ጥፋት ምክንያት የዕለቱ የመሀል ዳኛ ለድሬዳዋ ከተማ የፍፁም ቅጣት ምት መስጠት የቻሉ ሲሆን ጥፋቱ የተሰራው ግን ከሳጥኑ ውጪ ነበር ። የፍፁም ቅጣት ምቱንም አብዱራህማን ሙባረክ አስቆጥሮ ድሬዳዋ ከተማን መሪ አደረገ ።

ከሁለት ደቂቃዎች በኋላ የሀድያ ሆሳዕናው ፍቅረየሱስ ተክለብርሃን በሳጥን ውስጥ ኳስ እየገፋ ሲገባ በመሀመድ አብዱለጢፍ በተሰራበት ጥፋት ሀድያ ሆሳዕናዎቸም የፍፁም ቅጣት ምት አገኙ ። ነገር ግን የፍፁም ቅጣት ምቱን አምበሉ ሄኖክ አርፊቹ መቶት በግብ ጠባቂው ፍሬው ጌታሁን ተመልሶበታል ።

በመመራት ላይ የነበሩት ሀድያ ሆሳዕናዎች ከተጋጣሚያቸው በተሻለ ጫና በመፍጠር ለመጫወት የቻሉ ሲሆን በሳጥን ውስጥ በቀላሉ ለመግባት መቸገራቸውን እና ከሳጥን ውጪ የሚመቱ ኳሶች ኢላማቸውን የጠበቁ አለመሆን ግብ ከማስቆጠር አግዷቸዋል ። የመጀመሪያው አጋማሽም በሙከራ ረገድ ቀዝቅዞ እና የመሀል ሜዳ ላይ እንቅሰቃሴዎችን በስፋት አስመልክቶ በድሬዳዋ ከተማ መሪነት ተጠናቋል ።

የሁለተኛው አጋማሽ ከመጀመሪያው አጋማሽ በጨዋታ እንቅስቃሴ ፤ በግብ ሙከራዎች እንዲሁም በተቆጠሩ ግቦች የተሻለ ጨዋታ ነበር ።
የሙሉጌታ ምህረት ልጆች የአቻነቷን ግብ ለማግኘት የፈጀባቸው አራት ደቂቃዎች ብቻ ነበሩ ። ከቀኝ መስመር ላይ ሀብታሙ ገዛኸኝ ያሻገረውን ኳስ ፍቅረየሱስ አረጋግቶ ወደ ግብ የሞከረውን ኳስ ፍሬው ጌታሁን በአግባቡ ሊይዘው ባለመቻሉ በአቅራቢያው የነበረው ሀብታሙ ታደሰ ኳሱን አግኝቶ ማስቆጠር ቻለ ። ግብ በማስቆጠሩ ረገድ እኩል የሆነው ጨዋታ በሁለቱም በኩል በሚደረጉ ፈጣን እንቅስቃሴዎች መቀጠል ችሏል ። በሃድያ ሆሳዕናም ሆነ በድሬዳዋ ከተማ በኩል ኳስን በፍጥነት ከራሳቸው ሜዳ ይዘው በመውጣት በተጋጣሚያቸው ላይ ጫና ለመፍጠር ጥረቶችን ማድረግ ችለዋል ።

ድሬደዋ ከተማዎች በተወሰነ መልኩ ከራሳቸው ሜዳ ወተው በሀድያ ሆሳዕና ላይ ብልጫ ወስደው ለመጫወት ሲያደርጉት የነበረው ጥረት ለመልሶ ማጥቃት ተጋላጭ አድርጓቸዋል ። በዚህም 51ኛ እና 57ኛ ደቂቃ ላይ ሀድያ ሆሳዕናዎች በፀጋዬ ብርሀኑ እና በሀብታሙ ታደሰ አማካኝነት የግብ ዕድሎችን ቢያገኙም ሳይጠቀሙበት ቀርተዋል ።
62ኛ ደቂቃ ላይ አብዱራህማን ሙባረክ በሳጥኑ ጫፍ ላይ የያዘውን ኳስ ከኋላው በፍጥነት ሮጦ ወደ ሳጥን ውስጥ ለገባው እንየው ካሳሁን አቀብሎት እነየውም በሄኖክ አርፊቹ የደረሰበት ጫና ተቋቁሞ ለአቤል ከበደ የላከለት ኳስ ተቆጥሮ ድሬዳዋ ከተማን በድጋሚ መሪ አደረገ ። ግብ ያስተናገዱት ሀድያ ሆሳዕናዎች በቀጣዮቹ ደቂቃዎች ብልጫ ወስደው ለመጫወት እና ግብ ለማግኘት ያደረጓቸው ጥረቶች ከድሬዳዋ ከተማ አስገዳጅ ቅያሪዎች ጋር ተዳምሮ ያማረ ውጤት አምጥቶላቸዋል ።

75ኛ ደቂቃ ላይ አውዱ ናፊያ በፍፁም ቅጣት ምት ሳጥን ውስጥ በባዬ ገዛኸኝ ላይ በተሰራው ጥፋት ምክንያት በጨዋታው ሶስተኛ ለሀድያ ሆሳዕና ደግሞ ሁለተኛ የፍፁም ቅጣት ምት ተሰጠ ። የመጀመሪያውን የፍፁም ቅጣት የሳተው ሄኖክ አርፊጮ በዚህ ጊዜ ግን ኳስን ከመረብ አገናኘ ።

ከዘጠኝ ደቂቃዎች በኋላ ከማዕዘን ምት ባዬ ገዛኸኝ ያሻገረውን ኳስ ፍሬዘር ካሳ በግንባር ገጭቶ ከግቡ ትይዩ ለብቻው ለነበረው ሀብታሙ ታደሰ ያቀበለው ሲሆን ሀብታሙም ኳሱን ዞሮ መትቶ በማስቆጠር ሀድያ ሆሳዕናን መሪ አደረገ ። የሀብታሙ ታደሰ ሁለተኛ ግብ በሁለት ተከታታይ ጨዋታዎች ያስቆጠረው አራተኛ ግቡ ሆኗለሰ ። በቀሪዎቹ ደቂቃዎች ሀድያ ሆሳዕናዎች ውጤቱን አስጠብቀው በመውጣት ተከታታይ ሁለተኛ ድላቸውን ማስመዝገብ ችለዋል ።

ውጤቱን ተከትሎም ሀድያ ሆሳዕና በ9 ነጥብ ወደ 11ኛ ደረጃ ከፍ ሲል ድሬዳዋ ከተማ ሽንፈቱን ተከትሎ በ8 ነጥብ ወደ 14ኛ ደረጃ ዝቅ ብሏል ።
አስተያየት ይስጡ