መነሻ ገጽ ቅዱስ ጊዮርጊስ የጨዋታ ዘገባ | ፈረሰኞቹ ወደ ድል ተመልሰዋል
ቅዱስ ጊዮርጊስቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግወልቂጤ ከተማዜናዎችየኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግየጨዋታ ዘገባ

የጨዋታ ዘገባ | ፈረሰኞቹ ወደ ድል ተመልሰዋል

አጋራ
አጋራ

በቤትኪንግ ኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ 27ኛ ሳምንት የመጀመሪያ ጨዋታ ለረጅም ሳምንታት ሊጉን በመምራት ላይ ያለውን ቅዱስ ጊዮርጊስ ከወልቂጤ ከተማ አገናኝቶ በከነአን ማርክነህ እና በጋቶች ፓኖም ሁለት ግቦች ፈረሰኞቹ ወሳኝ ሶስት ነጥብ አሳክተዋል ።

ቅዱስ ጊዮርጊሶች በ26ኛው ሳምንት ከባህርዳር ከተማ ነጥብ በተጋሩበት ጨዋታ ላይ ከነበረው የመጀመሪያ አሰላለፍ ሁለት ለውጦችን በማድረግ በሀይደር ሸረፋ እና ያብስራ ተስፋዬ ምትክ በረከት ወልዴን እና ከነአን ማርክነህን አሰልፈዋል ። በወልቂጤ ከተማ በኩል ደግሞ በሳምንቱ ከመከላከያ ጋር አቻ በተለያዩበት ጨዋታ ላይ ከነበረው ምርጥ 11 አራት ለውጦችን በማድረግ ዮናታን ፍስሀ ፤ ሙሉጌታ ወልደጊዮርጊስን እና አቡበከር ሳኒን በረመዳን የሱፍ ፤ በሀይሉ ተሻገር እና ተስፋዬ ነጋሽ ምትክ ጨዋታው እንዲጀምሩ ማድረግ ችለዋል ።

 

የጨዋታው የመጀመሪያ አጋማሽ የነበረው የጨዋታ እንቅስቃሴ በቅዱስ ጊዮርጊስ ፍፁም ብልጫ የተደረገ ነበር ። ፈረሰኞቹ ከፍተኛ ጫና ፈጥረው በመጫወት ቀድመው ግብ ለማስቆጠር ያደርጉ የነበረው ጥረት ወልቂጤ ከተማዎችን ጫና ውስጥ እንዲገቡ ያደረገም ነበር ።

በተለይም በቀኝ መስመር ላይ ይደረግ የነበረው የቅዱስ ጊዮርጊስ የማጥቃት ሂደት በሄኖክ አዱኛ በሚሻገሩ ኳሶች እና ከፊት መስመር ባሉት ፈጣን ተጫዋቾች እንቅስቃሴ የሰራተኞቹን የኋላ መስመር በዕጅጉ መፈተን የቻለ ነበር ።

በጨዋታው የነበረው የመጀመሪያ የግብ ሙከራ በ9ኛው ደቂቃ ላይ የተደረገ ሲሆን ሄኖክ አዱኛ ከቀኝ መስመር ያሻገረውን ኳስ ከነአን ማርክነህ በግንባር ገጭቶ ግብ ጠባቂው ሰይድ ሀብታሙ ተቆጣጥሮታል ።

ከአራት ደቂቃዎች በኋላ ፈረሰኞቹ ከኋላ መስርተው የጀመሩትን ኳስ ከነአን ማርክነህ እየገፋ ሄዶ በሳጥኑ የቀኝ አቅጣጫ ለነበረው ለአቤል ያለው አቀብሎት አቤል ለቸርነት ጉግሳ ለመቀነስ ያደረገው ጥረት በዋሁብ አዳምስ ተመልሷል ።

በመከላከሉ ላይ ትኩረት አድርገው ጨዋታውን የጀመሩት ወልቂጤ ከተማዎች በ15ኛው ደቂቃ ላይ የመሀል ክፍል ተጫዋቻቸው ኤዲ ኤሞሞ ንጎይ ጉዳት ማስተናገዱን ተከትሎ በበሀይሉ ተሻገር ቀይረው ለማስወጣት ተገደዋል ።

ኳስ እና መረብን ለማገናኘት ጥረታቸውን የቀጠሉት ቅዱስ ጊዮርጊሶች በ20ኛው ደቂቃ ላይ በፍሪምፖንግ ሜንሱህ አማካኝነት ከቅጣት ምት በቀጥታ ኢላማውን የጠበቀ ሙከራ ማድረግ ቢችሉም ሰይድ ሀብታሙ ሙከራውን ግብ ከመሆን አድኖታል ።

በውድድር አመቱ የቅዱስ ጊዮርጊስ የግብ ማስቆጠሪያ መንገዶች አንዱ ከቆሙ ኳሶች የሚቆጠሩ ግቦች ናቸው ። በተለይም ደግሞ የሄኖከ አዱኛ ከቅጣት ምት እና ከማዕዘን ምት የሚነሱ ኳሶች ተጠቃሽ ናቸው ። ነገር ግን በተከታታይ ጨዋታዎች ላይ ከሄኖክ አዱኛ የሚነሱ ኳሶች ውጤታማ አልነበሩም ። በዚህ ጨዋታ ግን ተጫዋቹ በቀደሙ ጨዋታዎች ላይ ሲያደርግ እንደነበረው ከቆሙ ኳሶችም ሆነ ከመስመር የሚያሻግራቸው ኳሶች አደጋ መፍጠር የሚችሉ ነበሩ ።

በ24ኛው ደቂቃ ላይም ከሄኖክ አዱኛ የተነሳ የማዕዘን ምት ኳስ አማኑኤል ገብረሚካኤል በግንባር ገጭቶት የግቡን አግዳሚ ለትሞ ሲመለስ ያገኘው ከነአን ማርክነህ መረብ ላይ አሳርፎታል ። ለግቡ መቆጠር የግብ ጠባቂው ሰይድ ሀብታሙ ስህትትም አስተዋጽኦ ነበረው ።

ከውሀ እረፍት መልስ በተወሰነ መልኩ ኳሱን ይዘው በመጫወት ወደ ፊት ለመድረሰ ቀደም ባሉት ደቂቃዎች ከነበረው እንቅስቃሴ በተሻለ ለመንቀሳቀስ ጥረቶችን አድርገዋል ። በዚህም በ37ኛው ደቂቃ ላይ ለመጀመሪያ ጊዜ ወደ ቅዱስ ጊዮርጊስ ሳጥን መግባት የቻሉ ሲሆን በጫላ ተሺታ አማካኝነት ያደረጉት የግብ ሙከራም ኢላማውን ሳይጠብቅ ቀርቷል ።

የቅዱስ ጊዮርጊሱ አቤል ያለው ባጋጠመው ጉዳት ጨዋታውን መቀጠል ባለመቻሉ በ38ኛው ደቂቃ ላይ በዳግማዊ አርዓያ ተቀይሮ ለመውጣት ተገዷል ።

በአጋማሹ የመጨረሻ ደቂቃዎች ላይ ፈረሰኞቹ በቀኝ መስመር በኩል ዳግም የግብ ዕድል ለመፍጠር ጥረቶችን ማድረግ ችለው ነበር ። የመጀመሪያ አጋማሽ የጨዋታ ክፍለ ጊዜም በቅዱስ ጊዮርጊስ የ1 ለ 0 መሪነት ተጠናቀቀ ።

ወልቂጤ ከተማዎች ሁለተኛውን አጋማሽ ረመዳን የሱፍን እና አላዛር ዘውዱን ቀይረው በማስገባት በተለይም በግራ መስመር በኩል ወደ ፊት ለመድረስ ቢጥሩም የቅዱስ ጊዮርጊስ የኋላ ክፍልን አልፈው ዕድል መፍጠር የቻሉ አልነበሩም ።

ቅዱስ ጊዮርጊሶች ጫናቸውን አጠናክረው በመቀጠል ተጨማሪ የግብ ዕድሎችን ለመፍጠር የሞከሩ ሲሆን በ53ኛው ደቂቃ ላይ ከነአን ማርክነህ ከጋቶች ፓኖም ተቀብሎ በሳጥኑ የግራ አቅጣጫ ወደ መሀል የቀነሰውን ኳስ ዋሁብ አዳምስ ለማውጣት ሲሞክር በረከት ወልዴ ደርሶ ለማስቆጠር ያደረገው ሙከራ ኳሱ ከግቡ አናት በላይ ወጥቷል ።

በቀጣዮቹ ደቂቃዎች ላይ ወልቂጤ ከተማዎች በአንድ ሁለት ቅብብሎች ወደ ፊት ለማለፍ ቢጥሩም የተሳኩ አልነበሩም ። በአንፃሩ ቅዱስ ጊዮርጊሶች በፈጣን እንቅስቃሴዎች በቀኝ መስመር በኩል ከሚነሱ ኳሶች ተጨማሪ የግብ ዕድሎችን ለመፍጠር ሞክረዋል ።

ከውሀ እረፍት መልስ ዳግም የማጥቃት ሀይላቸውን አጠናክረው የተመለሱት ፈረሰኞቹ በ79ኛው ደቂቃ ላይ ሁለተኛ ግብ ማግኘት ችለዋል ። ዳግማዊ አርአያ በቀኝ መስመር በኩል ወደ ሳጥን ለመግባት ሲሞክር በጫላ ተሺታ ጥፋት በተሰራበት ጥፋት የተገኘውን የፍፁም ቅጣት ምት ጋቶች ፓኖም አስቆጥሮታል ።

መሪነታቸውን ከፍ ያደረጉት ቅዱስ ጊዮርጊሶች በመጨረሻዎቹ ደቂቃዎች ላይ መከላከሉን የሚያጠናክሩ ተጫዋቾችን በማስገባት ውጤቱን አስጠብቀው ለመውጣት የቻሉ ሲሆን ከረጅም ጨዋታዎች በኋላ ተቀይሮ ወደ ሜዳ የገባው እስማኤል ኦሮ ኦጎሮ በተጨማሪ ደቂቃዎች ላይ ከዳግማዊ አርአያ የደረሰውን ኳስ በግንባር ገጭቶ ሰይድ ሀብታሙ የመለሰው ኳስ የጨዋታው የመጨረሻ የግብ ሙከራ ነበር ።

 

ውጤቱን ተከትሎ ቅዱስ ጊዮርጊስ ነጥቡን 58 በማድረስ ከተከታዩ ፋሲል ከነማ ያለውን የነጥብ ልዩነት ወደ ስድስት ከፍ ሲያደርግ ወልቂጤ ከተማ በበኩሉ በ31 ነጥብ በነበረበት 10ኛ ደረጃ ለመቆየት ተገዷል ።

በ28ኛ ሳምንት ጨዋታዎች በመጪው ሰኔ 15 ( ረቡዕ ) 10:00 ላይ ወልቂጤ ከተማ ሲዳማ ቡናን ሲገጥም በተከታዩ ቀን 7:00 ላይ ቅዱስ ጊዮርጊስ ከሀድያ ሆሳዕና ይጫወታል ።

 

አጋራ

አስተያየት ይስጡ

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

ተዛማጅ ጽሑፎች
ዜናዎችየኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግየዲሲፕሊን ውሳኔዎችዲሲፕሊን ውሳኔ

የዲሲፕሊን ውሳኔዎች

ገዛኸኝ ደሳለኝ (ሸገር ከተማ) : ክለቡ ከ ኢትዮጵያ ቡና ጋር ባደረገው የ26ኛ...

ዜናዎችየኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግየጨዋታ ዘገባ

የሊጉ መሪ ሲዳማ ቡና በዝናባማው ጨዋታ በመቻል ሲረታ የጣናው ሞገድም አሸንፏል

እጅግ በከባድ ዝናብ ታጅቦ በተደረገው ጨዋታ መቻል የሊጉን መሪ ሲዳማ ቡናን 3ለ1...

ዜናዎችየኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግየጨዋታ ዘገባ

ሀድያ ሆሳዕና ፣ ፋሲል ከነማ እና ወላይታ ድቻ ወሳኝ ድል አግኝተዋል

በሊጉ የሳምንቱ የሁለተኛ ቀን መርሀግብር ሀዋሳ ከተማ ወደ ሊጉ መሪ የሚጠጋበትን ዕድል...

ዜናዎችየኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግየጨዋታ ዘገባ

ፈረሰኞቹ በድል ሲቀጥሉ ንግድ ባንክ እና ድሬዳዋም አሸንፈዋል

ቅዱስ ጊዮርጊስ ተከታታይ ድሉን ወደ ቋቱ ሲከት ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ከጨዋታ ብልጫ...