👉ፌዴሬሽኑ የሊግ ኩባንያውን መብት ነጥቋል
👉 የዲሲፕሊን ጥሰት የማየት መብት ወደ ፌዴሬሽኑ
መመለሱ የፍትህ ስርዓቱ ወደነበረበት ኋላቀር
አካሄድ እንዳይመለስ ተሰግቷል
👉 “ጌታነህ ከበደ በቀጣዩ ጨዋታ ይሰለፋል”
ፌዴሬሽኑ
የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን የሊግ ኩባንያ የውድድርና ስነስርዓት ኮሚቴ የዲሲፕሊን ጉዳዮች የማየት መብትን ማንሳቱ ከሊግ ኩባንያው ጋር ሌላ ውዝግብ ውስጥ እንዳይከተው ተሰግቷል።
በአቶ ተፈራ ደንበል የሚመራው የፌዴሬሽኑ የዲሲፕሊነሰ ኮሚቴ የወልቂጤውን አጥቂ ጌታነህ ከበደ የሶስት ጨዋታ ቅጣት ማንሳቱ በዶክተር ወገኔ ዋልታንጉስ የሚመራው የውድድርና ስነስርዓት ኮሚቴ አልቀበልም ማለቱን ተከትሎ በፌዴሬሽኑ ዋና ጸሃፊ አቶ ባህሩ ጥላሁን ፊርማ በወጣው ደብዳቤ” … የሊጉ የውድድርና ስነስርዓት ኮሚቴ ከተሰጠው ስልጣንና ሃላፊነት ውጪ የፍትህ አካላትን ውሳኔ እንደማይቀበል በደብዳቤ በማሳወቁ ከዛሬ ጀምሮ የሊጉ የውድድርና ስነስርዓት ኮሚቴ የቢጫና የቀይ ካርድ ካልሆነ በቀር የዲሲፕሊን ጉዳዮችን የመመልከት ስልጣኑ እንደተነሳና የዲሲፕሊን ጥሰቶችን ሪፖርት መርምሮ ውሳኔ የሚሰጠው የፌዴሬሽኑ የዲሲፕሊን ኮሚቴ ነው” ሲል አስታውቋል።
ፕሪሚየር ሊጉ በአክሲዮን ማህበሩ ስር መካሄድ ከጀመረበት ባለፉት 22 ወራቶች የይግባኝ ጥያቄ ያቀረቡት ጅማ አባጅፋር በዳዊት እስጢፋኖስ እንዲሁም ወልቂጤ ከተማ በጌታነህ ከበደ የቅጣት ውሳኔዎች ላይ ብቻ መሆኑን ከፌዴሬሽኑ የተገኙ መረጃዎች ያስረዳሉ። ባለፉት 22 ወራቶች ሁለቱ የይግባኝ ጥያቄዎች ብቻ መታየታቸው በጀ እንጂ የሁለቱ ተቋማት ውዝግብ ቀድሞ ሊነሳ የሚችልበት ዕድል እንደነበር ጉዳዩን በቅርበት የሚያውቁ ወገኖች ይናገራሉ። ፌዴሬሽኑ ከሁለቱ ይግባኝ ውጪ የቲሴራ ትክክለኝነት የህግ ማብራሪያ ብቻ ተጠይቆ ምላሽ መስጠቱም ታውቋል።
የየሳምንቱ 8 ጨዋታዎች ሲያልቁ የውድድር ውጤቶችን ለማጽደቅና የዲሲፕሊን ጥሰቶች ላይ ተወያይቶ ውሳኔ ለመወሰን በቀጣዩ ቀን የሚሰበሰበው በዶክተር ወገኔ ዋልታንጉስ የሚመራው የውድድርና ስነስርዓት ኮሚቴ ውድድሩን ከሞላ ጎደል በሰላም መምራቱን ያስተዋሉ ወገኖች የዲሲፕሊን ጥሰቶችን የማየት መብቱ በአቶ ተፈራ ደምበል ወደሚመራው ኮሚቴ መመለሱ የሊጉ ውድድር ላይ ውሃ መቸለስ እንዳይሆን ፌዴሬሽኑን ያስጠነቅቃሉ።
በፌዴሬሽኑ ስር ያሉት የፍትህ አካላት የሚባሉት የዲሲፕሊንና የይግባኝ ሰሚ ኮሚቴ አባላት አማተር ከመሆናቸውም በላይ ሲፈልጉና ሲመቻቸው የሚሰበሰቡ ናቸው ተብሎ ይታማሉ። የይግባኝ ሰሚ ኮሚቴ አባላቱ በቅርቡ በጅማ አባጅፋር የቀረበላቸውን ይግባኝ ያዩበት መንገድ ለአብነት ይጠቀሳል 7 ጨዋታና 7 ሺህ ብር የተቀጣው የዳዊትእስጢፋኖስ ክስ ኮሚቴው በአባላቱ የግል ስራ ከከተማ ውጪ መሆንና አለመመቸት አምስት ጨዋታ ካመለጠው በኋላ ይግባኙን ማየታቸው ከፍተኛ ቅሬታ መፍጠሩ ይታወሳል። ዲሲፕሊን ኮሚቴውም በአባላቱ የግል ስራ አለመመቸት ጉዳዮችን ሳያይ ረጅም ጊዜ የሚቆይ መሆኑ ሁለቱ አካላት በበርካታ ፍትህ ፈላጊ ወገኖች ሲተቹ የኖሩበት የአመታት ታሪካቸው ሆኗል።
የፌዴሬሽኑ ጽ/ቤትም ውሳኔውን ተከትሎ ተመሳሳይ ክፍተት እንዳይታይ የሚጠበቅበትን ሃላፊነት በብቃት ለመወጣት መዘጋጀቱን በመግለጽ የፌዴሬሽኑን መብትና ስልጣን በሚጋፉ ላይ ርምጃ እንደሚወስድ አስታውቋል። የዚህ አለመግባባት መነሻ ስለሆነው ጌታነህ ከበደ ቅጣት ዙሪያ የፌዴሬሽኑ የዲሲፕሊን ኮሚቴ የወሰነው ውሳኔ ተግባራዊ እንደሚደረግና ዛሬም መጫወት እንደነበረበት በቀጣይ ከሲዳማ ቡና ጋር ባለው ጨዋታ ላይ ተጨዋቹ የመሰለፍ መብቱ እንደሚከበርም አስታውቋል። በመቶ አለቃ ፈቃደ ማሞ የሚመራው የሊግ ኩባንያ በፌዴሬሽኑ ውሳኔ ዙሪያ የሚሰጠው ምላሽም አጓጊ ሆኗል።
ነሀሴ 21/22 በጎንደር የሚደረገው የፌዴሬሽኑ ጠቅላላ ጉባኤ የአመራሮች ምርጫ በተቃረበበት እንዲሁም ሊጉ ሊጠናቀቅ ቀናቶች በቀሩበት በአሁኑ ጊዜ በፌዴሬሽኑና በሊግ ኩባንያው መሃል የተፈጠረው አለመግባባት ሰላማዊ ሆኖ ባለፉት 22 ወራት የቆየውን እግርኳሱን ወደሌላ ውዝግብ እንዳይወስደው ሁለቱ ተቋማት ጥንቃቄ እንዲወስዱ የስፖርት ቤተሰቡ ጠይቋል።
ይህ በእንዲህ እንዳለ ጌታነህ ከበደ ዛሬ ወልቂጤ ከተማ በቅዱስ ጊዮርጊስ 2ለ0 በተረታበት ጨዋታ ባለመሰለፉና እንዲያሰልፉት ከክለቡ መመርያ የተሰጣቸው የቡድን መሪው አወል ከድር የክለቡን ትዕዛዝ ተግባራዊ ባለማድረጋቸው ከስራና ከደመወዝ መታገዳቸው ታውቋል።
አስተያየት ይስጡ