በዕለቱ ሁለተኛ ጨዋታ ከምሽት 12 ሰዓት ጀምሮ በፋሲል ከተማ እና በአርባ ምንጭ ከተማ መካከል የተደረገው ጨዋታ በርካታ የሜዳ ላይ ክስቶችን አስመልክቶን በ 1 ለ 1 ውጤት ተጠናቋል ።
ሁለቱም ክለቦች በአራተኛ ሳምንት ጨዋታቸው ከተጠቀሙት ቋሚ 11 የተወሰኑ ለውጦችን ያደረጉ ሲሆን በፋሲል ከተማ በኩል ሽመክት ጉግሳ እና ዓለምብርሀን ይግዛው እንዲሁም በአርባምንጭ ከተማ በኩል መላኩ ኤልያስ ወደ ቋሚ አሰላለፉ መልሰው ጨዋታቸውን ጀምረዋል ።

በጥሩ ፉክክር የተጀመረው ጨዋታ ጥሩ ጥሩ እንቅስቃሴዎች ያስመለከተ ሲሆን አፄዎቹ ኳሱን ይዘው በመጫወት ወደ ፊት ለመሄድ ጥረት ሲያደርጉ የነበረ በአዞዎቹ በኩል ደግሞ ከኋላ በሚነሱ ፈጣን ሽግግሮች የተጋጣሚን የተከላካይ መስመር ለመፈተን ሞክረዋል ።
በ7ኛው ደቂቃ ላይ በፈጣን በፈጣን እንቅስቃሴ በላይ ገዛኸኝ ወደ ሳጥን ውስጥ ኳስ ይዞ ሲገባ በአምሳሉ ጥላሁን ከኋላው በተሰራበት ጥፋት አዞዎቹ የፍፁም ቅጣት ምት አገኙ ። የፍፁም ቅጣት ምቱንም በአራተኛ ሳምንት ጨዋታ ባህርዳር ከተማ ላይ የማሸነፊያውን ጎል በፍፁም ቅጣት ምት ያስቆጠረው ወርቅይታደስ አበበ መቶት የነበረ ቢሆንም የግቡን ቋሚ መልሶ ወቶበታል ።

ከአጋጣሚው በኋላ አዞዎቹ ወደ ተጋጣሚ የሜዳ ክፍል በመጠጋቴ አፄዎቹ በቀላሉ ኳስን መስርተው እንዳይጫወቱ ማድረግ ችለዋል ። አልፎ አልፎ በፋሲል ከተማ በኩል ወደ ማጥቃቱ ዞን የሚሄዱ ኳሶችም በቀላሉ ይበላሹ ነበር። በሁለቱም በኩል ግብ ለማስቆጠር የነበሩ ጥረቶች በግብ ሙከራዎች ሳይታጀቡ የመጀመሪያው አጋማሽ ተጠናቀቀ ።
በተመሳሳይ በጥሩ እንቅስቃሴ የተጀመረው የሁለተኛ አጋማሽ የፋሲል ከተማ የበላይነት የታየበት ነበር ። በ57ኛ ደቂቃ ላይ በረከት ደስታ ከሽመክት ጉግሳ የተሰነጠቀለትን ግሩም ኳስ ለማስቆጠር በሚሞክርበት ጊዜ በአሸናፊ ፊዳ በተሰራበት ጥፋት ፋሲል ከተማዎቾ የፍፁም ቅጣት ምት ማግኘት የቻሉ ሲሆን ጥፋቱን የሰራው አሸናፊም በሁለተኛ የቢጫ ካርድ ከሜዳ ተሰናበተ ። የፍፁም ቅጣት ምቱንም አምበሉ ያሬድ ባየህ 59ኛ ደቂቃ ላይ አስቆጥሮ ፋሲል ከተማን መሪ ማድረግ ቻለ ።

አርባምንጭ ከተማዎቾ ከግቧ መቆጠር በኋላ በተሻለ ተንቀሳቅሰው ወደ ፊት ለመሔድ ጥረቶችን ማድረግ ችለው ነበር ። 66ኛው ደቂቃ ላይ አስናቀ በረጅም ወደ ግብ ክልል ያሻገረውን ኳስ በሳጥን ውስጥ ሆኖ ያሬድ ባየህ በእጁ ቢነካውም የመሀል ዳኛው በዝምታ አልፈውታል ። 73ኛ ደቂቃ ላይ አዞዎቹ ያገኙት የማዕዘን ምት ተሻምቶ በላይ ገዛኸኝ በግንባሩ በሚገጭበት ጊዜ ያሬድ ባየህ በእጁ በድጋሚ ነክቶት አዞዎቹ የፍፁም ቅጣት ምት አገኙ ። በውሳኔው ብስጭቱን በመሀል ዳኛው ላይ የገለፀው አምበሉ ያሬድ ባየህ በሁለተኛ የቢጫ ካርድ ከሜዳ ሊወጣ ቻለ ። የፍፁም ቅጣት ምቱንም ኬንያዊው አጥቂ ኤሪክ ካፓይቶ አስቆጥሮ አቻ መሆን ቻሉ ።

ከአራት ደቂቃዎች በኋላም በጨዋታው ሶስተኛ በፋሲል ከተማ በኩል ደግሞ ሁለተኛው የቀይ ካርድ ታየ ። በፋሲል ከተማ የግራ መስመር በኩል የአርባምንጩ ወርቅይታደስ አበበ ኳሱን ለማግኘት በሚጥርበት ጊዜ ሸፍኖት የነበረው ሀብታሙ ተከስተ በክርኑ ፊቱን በመምታቱ በቀጥታ የቀይ ካርድ ከሜዳው ተባሯል ።
የጨዋታው መጠናቀቂያ ደቂቃዎች ሲቃረቡ ፋሲል ከተማዎች በተሻለ የግብ ዕድሎችን መፍጠር ችለው ነበር ። 83ኛ ደቂቃ ላይ በኦኪኪ አፎላቢ እንዲሁም በ86ኛ ደቂቃ ላይ በሽመክት ጉግሳ አማካኝነት ጠንካራ የግብ ሙከራዎችን አድርገው በግብ ጠባቂው ሳምሶን ተመልሶባቸዋል ።

ጨዋታውም በፍፁም ቅጣት ምት በተቆጠሩት ግቦች በ 1 አቻ ውጤቶ ተጠናቀቀ ። ውጤቱን ተከትሎም ፋሲል ነጥቡን 10 ሲያደርስ አርባምንጭ ከተማ 8 ነጥብ ላይ ደርሷል ።
አስተያየት ይስጡ