በቤትኪንግ ኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ 29ኛ ሳምንት የሁለተኛ ቀን ውሎ ሁለተኛው ጨዋታ በበርካታ ደጋፊዎቹ ፊት የተጫወተው ፋሲል ከነማ ኢትዮጵያ ቡናን 3 – 0 በሆነ ውጤት ማሸነፍ ችሏል ።
ፋሲል ከነማዎች በ28ኛው ሳምንት ሀዋሳ ከተማን በረቱበት ጨዋታ ላይ ከነበረው የመጀመሪያ አሰላለፍ አንድ ለውጥ ብቻ በማድረግ ከድር ኩሊባሊን በማሳረፍ ያሬድ ባየህን ሲያሰልፉ በኢትዮጵያ ቡና በኩል በሳምንቱ በአርባምንጭ ከተማ በተረቱበት ጨዋታ ላይ ከነበረው ምርጥ 11 አራት ቅያሪዎችን አድርገው በመግባት ገዛኸኝ ደሳለኝ ፤ አላዛር ፤ ሮቤሎ ተክለሚካኤል ፤ እና አቡበከር ናስር ምትክ ቴዎድሮስ በቀለ ፤ አብነት ደምሴ ፤ አቤል እንዳለ እኔ እንዳለ ደባልቄን አሰልፈዋል ።
በጨዋታው የመጀመሪያ አጋማሽ ላይ ኢትዮጵያ ቡናዎች ኳስን ከኋላ መሰርተው በመጫወት ወደ ፋሲል ከነማ የሜዳ ክፍል ለመድረስ ጥረቶችን ሲያደርጉ በፋሲል ከነማ በኩል ተረጋግተው በመጫወት በተለይም በመስመሮች በኩል የማጥቃት ሂደቶችን ለማድረግ ጥረዋል ።
- ማሰታውቂያ -
በተከታታይ ጨዋታዎች ላይ በአስደናቂ ጉዞ ላይ ያሉት አፄዎቹ ጨዋታው በተጀመረ 12ኛው ደቂቃ ላይ ቀዳሚ የሆኑበትን ግብ አስቆጥረዋል ። ሱራፌል ዳኛቸው ከራሱ የሜዳ ክፍል ከኢትዮጵያ ቡና ተከላካዮች ጀርባ የጣለለተን ኳስ በአግባቡ የተቆጣጠረው ሙጂብ ቃሲም ፋሲል ከነማን መሪ ያደረገ ግብ ከመረብ አዋህዷል ።
በቀጣዮቹ ደቂቃዎች ቡናማዎቹ በኳስ ቁጥጥሩ የበላይ ሆነው ቢቀጥሉም ወደ ማጥቃት ሶስተኛው ዞን ለመግባት የሚያደርጉት እንቅስቃሴ ደካማ ነበር ።
በፋሲል ከነማ በኩል በመሰመሮች ከሚያደርጓቸው ጥቃቶች ባለፈ የኢትዮጵያ ቡና ተጫዋቾች ኳሱን ይዘው በሜዳ ክፍላቸው በሚገቡበት ወቅት ጫና ፈጥረው ኳሱን በማስጣል እና ኳሶችን በቀጥታ ከተጋጣሚያቸው ተከላካዮች ጀርባ በመጣል የግብ ዕድሎቾን ለመፍጠር ሞክረዋል ።
በ41ኛው ደቂቃ ላይ አፄዎቹ አከታትለው የግብ ሙከራዎችን ያደረጉ ሲሆን ሱራፌል ዳኛቸው ከቅጣት ምት ወደ ግብ የመታው ኳስ በኢትዮጵያ ቡና ተከላካይ ተመልሶ የማዕዘን ምት ሆኗል ። ከማዕዘን ምቱ የተነሳው ኳስ ወደ ግብ ክልል ተሻግሮ ሽመክት ጉግሳ በግንባር መግጨት ቢችልም ሙከራው ኢላማውን የጠበቀ አልነበረም ።
የመጀመሪያው አጋማሽም በፋሲል ከነማ የ 1 – 0 መሪነት ተጠናቀቀ ።
በሁለተኛው አጋማሽ የጨዋታ ክፍለ ጊዜ ቡናማዎቹ በኳስ ቁጥጥሩ በመጀመሪያ አጋማሽ የነበረውን ብልጫቸውን አስቀጥለው መሄድ የቻሉ ቢሆንም በተመሳሳይ የግብ ዕድሎችን በመፍጠሩ ረገድ ግን ይህ ነው ሊባል የሚችል ሳማኪን የፈተነ የግብ ሙከራ ማድረግ አልቻሉም ነበር ።
በፋሲል ከነማ በኩል ከኢትዮጵያ ቡና የሚነጠቁ ኳሶችን በፈጣን ወደ ተጋጣሚ የግብ ክልል በማድረስ በፊት መስመር ተጫዋቾቻቸው አማካኝነት ተጨማሪ ግቦችን ለማግኘት ጥረቶችን አድርገዋል ።
በአጋማሹ ቀዳሚ ግልፅ የግብ ዕድል በ52ኛው ደቂቃ ላይ በረከት ደስታ በግራ መስመር ለብቻው ሆኖ ያገኘውን ኳስ እየገፋ ሄዶ ለማስቆጠር ያደረገው ጥረት በኢትዮጵያ ቡናው ግብ ጠባቂ በረከት አማረ ተመልሶበታል ።
ከሁለት ደቂቃዎች በኋላ ቡናማዎቹ በአጋማሹ ጥሩ ሊባል የሚችል ዕድል መፍጠር ቢችሉም እንዳለ ደባልቄ ከአብነት ደምሴ የተላከለት ኳስ ላይ መድረስ ሳይችል ቀርቶ ሚኬል ሳማኪ ወጥቶ ይዞበታል ።
ጨዋታው 65ኛው ደቂቃ ላይ ሲደርስ አፄዎቹ ሁለተኛ ግብ አግኝተዋል ። ሱራፌል ዳኛቸው ከኢትዮጵያ ቡና ተከላካዮች ጀርባ የጣለውን ኳስ በረከት ደስታ ከበረከት አማረ ጋር ተገናኝቶ ለማስቆጠር ሲሞክር ግብ ጠባቂው ኳሱን መመለስ ቢችልም በቅርብ የነበረው ሙጂብ ቃሲም ለቡድኑም ሆነ ለራሱ ሁለተኛ ግብ አስቆጥሯል ።
በ84ኛው ደቂቃ ላይ በረከት ደስታ በቀኝ የሳጥኑ አቅጣጫ ላይ ሆኖ የደረሰውን ኳስ አክርሮ ወደ ግብ ሞክሮት በረት አማረ በድጋሚ አድኖበታል ። ከዚህ ሙከራ ሁለት ደቂቃዎች በኋላ ደግሞ አፄዎቹ የፍፁም ቅጣት ምት አግኝተዋል ። በረከት ደስታ ቴዎድሮስ በቀለን ለማለፍ ሲሞክር ጥፋት ተሰርቶበታል በሚል የዕለቱ የመሀል ዳኛ የፍፁም ቅጣት ምት ሊሰጡ ችለዋል ።
ለሁለቱ ግቦች መቆጠር ትልቅ ሚና የተጫወተው ሱራፌል ዳኛቸውም የፍፁም ቅጣት ምቱን በማስቆጠር የፋሲል ከነማን መሪነት ወደ 3 – 0 ከፍ አድርጓል ።
በመጨረሻዎቹ ደቂቃዎች ላይ አፄዎቹ በይሁን እንደሻው እና ሙጂብ ቃሲም የግብ ሙከራዎችን ማድረግ ቢችሉም ወደ ግብነች መቀየር ሳይችሉ ጨዋታው ተጠናቋል ።
ውጤቱን ተከትሎ ፋሲል ከነማ ነጥቡን 61 በማድረስ ለጊዜው መሪነቱን ከቅዱስ ጊዮርጊስ ሲረከብ ኢትዮጵያ ቡና በበኩሉ በ41 ነጥብ በነበረበት 6ኛ ደረጃ ላይ ለመቆየት ተገዷል ።
በሊጉ የመጨረሻ ሳምንት ( 30ኛ ) ጨዋታዎች በመጪው ሰኔ 24 ( አርብ ) 10:00 ላይ ፋሲል ከነማ ድሬዳዋ ከተማን ሲገጥም በተከታዩ ቀን ሰኔ 25 ( ቅዳሜ ) 7:00 ላይ ኢትዮጵያ ቡና ከባህርዳር ከተማ የሚጫወት ይሆናል ።