በቤትኪንግ ኢትዮጵያ ፕሪማየር ሊግ 29ኛው ሳምንት የመጀመሪያ ቀን ውሎ ሶስተኛ መርሀግብር ላለመውረድ በመታገል ላይ ያለውን ባህርዳር ከተማን መውረዱን ካረጋገጠው ሰበታ ከተማ ጋር ተገናኝተው 1 – 1 በሆነ ውጤት ተለያይተዋል ።
ባህርዳር ከተማዎች በ28ኛው ሳምንት ድሬዳዋ ከተማን 1 – 0 በረቱበት ጨዋታ ላይ ከነበረው የመጀመሪያ አሰላለፍ አንድ ለውጥ ብቻ በማድረግ ሰለሞን ወዴሳን በመናፍ ዐወል ምትክ ሲያሰልፉ በሰበታ ከተማ በኩል ደግሞ በሳምንቱ በአዲስ አበባ ከተማ በተሸነፉበት ጨዋታ ላይ ከነበረው የመጀመሪያ አሰላለፍ አረት ለውጦችን በማድረግ በረከት ሳሙኤል ፤ ታፈሰ ሰርካ ፤ በሀይሉ ግርማ እና ሳሙኤል ሳሊሶን በአንተነህ ተስፋዬ ፤ ሃይለሚካኤል አደፍርስ ፤ ቢያድግልኝ ኤልያስ እና ቢስማርክ አፒያ ተክተው ገብተዋል ።
በበርካታ የጣና ሞገዶቹ ደጋፊዎች ታጅቦየተደረገው ጨዋታ ገና ከጅምሩ ፈጣን እንቅስቃሴ የታየበት ኳሶች ቶሎ ቶሎ ወደ ግብ የሚደርሱበት ጠንከር ጠንከር ያሉ ሙከራዎችንም በተከታታይ የተመለከትንበት ነበር ።

ገና በመጀመሪያው ደቂቃ ላይ ኦሴ ማውሊ ከሳጥን ውጪ አክርሮ የመታው ኳስ በግብ ጠባቂው ሰለሞን ደምሴ ተመልሷል ። ከአንድ ደቂቃ በኋላም በተቃራኒው አቅጣጫ በሀይሉ ግርማ ከሳጥን ውጪ ያደረገውን ሙከራ አቡበከር ኑሪ በድንቅ ብቃት አድኖታል ።
በአራተኛው ደቂቃም ፍፁም አለሙ ያደረገው ሙከራ ለጥቂት ወደ ውጪ ሲወጣ ከሶስት ደቂቃዎች በኋላ ተጫዋቹ በድጋሚ ያደረገው አስደናቂ ሙከራ በሰለሞን ደምሴ ግብ ከመሆን ድኗል ።
ባህርዳር ከተማዎች በፈጣን እንቅስቃሴ የሰበታ ከተማን የኋላ ክፍል በመፈተን ተደጋጋሚ የግብ ዕድሎችን ለመፍጠር ቢችሉም በ17ኛው ደቂቃ ላይ ግብ አስተናግደዋል ። ሳሙኤል ሳሊሶ በፈጣን መልሶ ማጥቃት እንቅስቃሴ በሳጥኑ የቀኝ አቅጣጫ ላይ ሆኖ ከዱሬሴ ሹቢሳ በግሩም ሁኔታ የደረሰውን ኳስ በግሩም አጨራረስ ከመረብ ጋር አዋህዶታል ።

በባህርዳር ከተማ በኩል ግብ ካስተናገዱ በኋላም ጥቃት መሰንዘራቸውን ሲቀጥሉ በ22ኛው ደቂቃ ላይ ፍፁም አለሙ ለኦሴ ማውሊ አቀብሎ በድጋሚ የተቀበለውን ኳስ አስቆጠረው ተብሎ ሲጠበቅ ታፈሰ ሰርካ ደርሶ ኳሱን እንዳይጠቀም ማድረግ ቸሏል ።
ከውሀ እረፍት መልስ ኦሴ ማውሊ በ28ኛው ደቂቃ ላይ ከሳጥን ውጪ የመታውን ኳስ ሰለሞን ደምሴ ሲተፋው ወልደአማኑኤል ጌቱ ደርሶ ኳሱን ማራቅ ችሏል ። በፈጣን መልሶ ማጥቃት የጣና ሞገዶቹን ማስጨነቅ የቻሉት ሰበታ ከተማዎች በጌቱ ሀይለማርያም ከቀኝ መስመር በተሻገረ ኳስ ዱሬሳ ሹቢሳ ሁለተኛ ግብ ለማስቆጠር ያደረጉት ድንቅ ሙከራ በግቡ አግዳሚ ተመልሶ ወጥቷል ።
በ30ኛው ደቂቃ ላይ ማውሊ ከግራ መሰመር ይዞ የገባውን ኳስ አደም አባስ ሞክሮ ሰለሞን ደምሴ ግብ ከመሆን አግዶታል ።

የአጋማሹ መጨረሻ ሲቃረብ የግብ ሙከራዎች እየተቀዛቀዙ የሄዱ ሲሆን 44ኛው ደቂቃ ላይ አደም አባስ ከማዕዘን ያሻማውን ኳስ ፍፁም አለሙ በግንባር ገጭቶ ሰለሞን ደምሴ የመለሰው ኳስ የአጋማሹ የመጨረሻ የግብ ሙከራ ሆኗል ።
በሁለተኛው አጋማሽ ባህርዳር ከተማዎች የተጫዋቾች ቅያሪም በማድረግ የማጥቃት ሂደታቸውን በማጠናከር ግብ ፍለጋቸውን ሲቀጥሉ በሰበታ ከተማ በኩችፈሌ ደግሞ ያስቆጠሩትን አንድ ግብ አስጠብቀው ለመውጣት በመከላከሉ ላይ አተኩረው ጨዋታቸውን አድርገዋል ።
በአጋማሹ የመጀመሪያ ሙከራ 48ኛው ደቂቃ ላይ በሀይሉ ግርማ ከሳጥን ውጪ ያደረገው ጠንካራ ሙከራ በአቡበከር ኑሪ ተመልሰሏል።
የጣና ሞገዶቹ ግብ የማግኘት ጥረት በ53ኛው ደቂቃ ላይ ፍሬ አፍርቷል ። አደም አባስ ከግራ መስመር አቅጣጫ ወደ ግብ ክልል ያሻገረውን ኳስ ኦሴ ማውሊ በድንቅ የመቀስ ምት በሰለሞን ደምሴ መረብ ላይ አሳርፎታል ።

በአቻነቱ ግብ የተነቃቁት ባህርዳር ከተማዎች የሰበታ ተከላለካዮችን አልፈው የግብ ዕድሎችን ለመፍጠር በሚታትሩበት ወቅት ከሰበታ ከተማ አንድ ተጫዋች በቀይ ካርድ ከሜዳ በመወገዱ የቁጥር ብልጫም ማግኘት ችለዋል ።
በ65ኛው ደቂቃ ላይ በረከት ሳሙኤል በአህመድ ረሺድ ላይ ጥፋት ሰርቷል በሚል የዕለቱ የመሀል ዳኛ ባህሩ ተካ በቀጥታ የቀይ ካርድ ከሜዳ አሰናብተውታል ።
የጣና ሞገዶቹ የሰበታ ከተማ የግብ ክልል ላይ ማንዣበባቸውን ቀጥለው የአሸናፊነት ግብ ለማስቆጠር ቢጥሩም የሰበታ ከተማ የኋላ መስመር ግን የሚቀመስ አልነበረም ።
በዚህም ተቀይሮ የገባው አለልኝ አዘነ በ73 እና 84ኛ ደቂቃ ላይ ከሳጥን ውጪ ያደረጋቸው ሙከራዎች ኢላማቸውን መጠበቅ ሳይችሉ ቀርተዋል ።
በመጨረሻም ጨዋታው በ1 – 1 ውጤት ተጠናቋል ።
ውጤቱን ተከትሎ ባህርዳር ከተማ በ34 ነጥብ በነበረበት ደረጃ 10ኛ ላይ ሲቀጥል መውረዱን ያረጋገጠው ሰበታ ከተማ በ22 ነጥብ የሊጉ ግርጌ ላይ ተቀምጧል ።

በሊጉ የመጨረሻ ሳምንት ( 30ኛ ) ጨዋታዎች በመጪው ሰኔ 26 ( ቅዳሜ ) 7:00 ላይ ባህርዳር ከተማ ኢትዮጵያ ቡና ሲጫወት በዕለቱ 10:00 ላይ ሰበታ ከተማ አርባምንጭ ከተማን የሚገጥም ይሆናል ።
አስተያየት ይስጡ