በዕለቱ ሁለተኛ ጨዋታ ኢትዮጵያ ቡናን ከሀድያ ሆሳዕና ያገናኘ ሲሆን ሁለቱም ከድል መልስ መገናኘታቸው ጨዋታውን ተጠባቂ ያደረገው ነበር ። በጨዋታውም ፍሬዘር ካሳ ባስቆጠረው ብቸኛ ግብ የሙሉጌታ ምህረት ልጆች አሸንፈው ወጥተዋል ።

ሁለቱም ክለቦች በስምንተኛው ሳምንት ድል ባደረጉባቸው ጨዋታዎች ከተጠቀሙት ቋሚ አሰላለፍ አንድ አንድ ቅያሪ አድርገው ወደ ጨዋታው ገብተዋል ። በኢትዮጵያ ቡና በኩል አቤል እንዳለ እንዲሁም በሀድያ ሆሳዕና በኩል ኡመድ ኡክሪ በቋሚ አሰላለፉ መካተት የቻሉ ተጫዋቾች ናቸው ።
ጨዋታው ከመጀመሩ ኢትዮጵያ ቡናዎች ለቀድሞ ተጫዋቻቸው እያሱ ታምሩ የፎቶ ስጦታ አበርከተውለታል ።
ጨዋታው በአመዛኙ በመሀል ክፍል ላይ ኳስ ስትንሸራሸር የቆየችበት ነበር ። ቡናማዎቹ በተለመደው ከኋላ መስመርቶ በመጫወት ወደ ፊት ለመሄድ ሲያደርጓቸው የነበሩ ጥረቶች በሀድያ ሆሳዕና ከፍተኛ ጫና ምክንያት እንዳሰቡት ለመጫወት እንዲቸገሩ አድርጓቸዋል ። በሀድያ ሆሳዕና በኩልም የሚገኙ ኳሶችን በፍጥነት ወደ ተጋጣሚ ክልል በመላክ ከፊት መስመር ባሉ ተጫዋቾች አማካይነት የግብ ዕድሎችን የሚፈጥሩበትን መንገድ ሲፈልጉ ቆይተዋል ።

ኢትዮጵያ ቡናም ሆነ ሀድያ ሆሳዕና የግብ ሙከራዎችን በማድረግ ግብ ጠባቂዎችን ማስጨነቅ አልቻሉም ነበር ። በኢትዮጵያ ቡና በኩል አቡበከር ናስርን ብቻ መሰረት ያደረጉ ኳሶች በማጥቃት መስመሩ ላይ በተደጋጋሚ መታየታቸው ተጫዋቹ በቀላሉ በተከላካዮች ዕይታ ውስጥ እንዲገባ እና እንደፈለገው ለመንቀሳቀስ እንዳይችል አድርጎታል ።


በ28ኛው ደቂቃ ላይ የኢትዮጵያ ቡናው ተከላካይ ቴዎድሮስ በቀለ ለሌኛው ተከላካይ አበበ ጥላሁን ለማቀበል ሲሞክር ኳሱ ሀብታሙ ታደሰ እግር ስር ቢገባም ሀብታሙ ኳሱን መቆጣጠር ሳይችል ቀርቶ ወቶበታል ። በተመሳሳይ ከሁለት ደቂቃዎች በኋላም አበበ ለሀይሌ ገብረትንሳይ ለማቀበል ሲሞክር ሀብታሙ አግኝቶ አስቆጠረው ተብሎ ሲጠበቅ ኳሱን በሚገፊበት ሰዓት በሰራው ስህተት ኳሱ አምልጦት ወደ ውጪ ወጥቷል ።

41ኛው ደቂቃ ላይ በኢትዮጵያ ቡና በኩል አስራት ቱንጆ ለአቡበከር ናስር በጥሩ ዕይታ ያቀበለው ኳስ አቡበከር ሳይደርስበት ቀርቶ በሶሆሆ ሜንሱ ተይዟል ።
በሁለተኛው አጋማሽ በተመሳሳይ እንቅሰቃሴ የቀጠለው ጨዋታ በተለይም በቡናማዎቹ በኩል ወደ ግብ ለመድረስ የነበሩ ጥረቶች ከሀድያ ሆሳዕና ተከላካዮች ማለፍ የቻሉ አልነበሩም ።
በ63ኛ ደቂቃ ላይ ሳምሶን ጥላሁን ከግራ መስመር በረጅሙ የመታውን የቅጣት ምት ፍሬዘር ካሳ በግንባር ገጭቶ በማስቆጠር ሀድያ ሆሳዕናን መሪ አደረገ ። ከግቡ በኋላ ጨዋታው ቀድሞ ከነበረው በተሻለ መነቃቃት የተካሄደ ሲሆን ሀድያ ሆሳዕናዎች በመከላከል ላይ አመዝነው ግቡን አስጠብቀው ለመውጣት ጥረቶችን ያደረጉበት ነበር ።

66ኛ ደቂቃ ላይ የሀድያ ሆሳዕና ተከላካዮች ኳስ ለማውጣት ሲሞክሩ ኳሱን ያገኘው አቤል እንዳለ የግብ ጠባቂውንም መውጣት ተመልክቶ ወደ ግብ የመታው ኳስ ለጥቂት ወደ ውጪ ወቶበታል ። 80ኛው ደቂቃ ላይም አቡበከር ናስር ከሮቤል ተክለሚካኤል የደረሰውን ኳስ በግሩም ሁኔታ በመቆጣጠር ወደ ሳጥን ይዞት የገባውን ኳስ ረዝሞበት ግብ ጠባቂው ሶሆሆ ሜንሱ ይዞታል ።
በ80ዎቹ ደቂቃዎች መገባደጃ ላይ ሀድያ ሆሳዕናዎች ባገኟቸው ክፍተቶች ተጠቅመው በፀጋዬ ብርሀኑ እና በሳምሶን ጥላሁን የፈጠሯቸው የግብ ዕድሎች በግብ ጠባቂው በረከት አማረ በቀላሉ ተይዘዋል ። ጨዋታውም በሀድያ ሆሳዕና 1 ለ 0 አሸናፊነት ተጠናቀቀ ።

ውጤቱን ተከትሎም ሀድያ ሆሳዕና ነጥቡን 12 በማድረስ ደረጃውን ወደ 7ኛ ሲያሻሽል ኢትዮጵያ ቡና በ14 ነጥብ ባለበት 4ኛ ደረጃ ላይ ቆይቷል ።
አስተያየት ይስጡ