በኢንተርናሽናል ዋና ዳኛ ሊዲያ ታፈሰ የተመራዉ የሁለቱ ክለቦች ጨዋታ ልክ ከቀኑ 10:00 ሲል የተጀመረው በሁለት ነጥብ ብቻ ተበላልጠው አራተኛ እና አምስተኛ ደረጃ ላይ ተቀምጠዉ የነበሩት ወልቂጤ ከተማ እና ኢትዮ ኤሌክትሪክ ጥሩ በሚባል መልኩ ተመጣጣኝ የጨዋታ ፍሰት የተመለከትንበት ጨዋታ ነበር።
በሦስተኛ ሳምንት ጨዋታ በኮልፌ ቀራኒዮ 2ለ0 ተረተው ለዛሬው ጨዋታ የቀረቡት ኢትዮ ኤሌክትሪኮች ከተሸነፉበት ያለፈዉ ሳምንት ጨዋታ አምስት ለውጦችን አድርገዋል።

በአንፃሩ በሦስተኛ ዙር የውድድሩ መርሐ-ግብር ከአዳማ ከተማ ጋር ተገናኝተው በአቻ ዉጤት ያጠናቀቁት ወልቂጤዎች አንድ ተጫዋች ብቻ ቀይረዉ ወደ ሜዳ ገብተዋል።
ተመጣጣኝ በሚባል የኳስ ፍሰት የጀመረዉ የሁለቱ ክለቦች ጨዋታ የመጀመሪያውን 15 ደቂቃ ይህ ነዉ የሚባል የግብ ሙከራ አልተደረገበትም ነበር። ጨዋታውም ቀጥሎ 20ኛዉ ደቂቃ ላይ ከግራ መስመር በኩል የተገኘዉን ቅጣት ምት የወልቂጤ ከተማዉ ሀብታሙ ሸዋለም ወደ ኤሌክትሪክ የግብ ክልል አሻምቶ በጥሩ አቋቋም ላይ የነበረዉ አሜ መሀመድ ቢሞክርም ግብጠባቂዉ መሎሶታል ነገር ግን በቅርብ ርቀት ይገኝ የነበረዉ አህመድ ሁሴን በጭንቅላት በመግጨት ግብ ማስቆጠር ቻለ።

ከግቧ መቆጠር በኋላም በጥሩ የመነቃቃት መንፈስ ወልቂጤዎች ኳስን መስርተዉ በመጫወት ወደ ኤሌትሪክ የግብ ክልል በተደጋጋሚ ሲደርሱ ተስተዉሏል። በዚህም በዉድድሩ ላይ ጥሩ እየተንቀሳቀሰ የሚገኘዉ አቡበከር ሳኔ በሚገርም የአጨራረስ ብቃት ሁለተኛዉን ግብ በ28ኛዉ ደቂቃ ላይ በማስቆጠር ወልቂጤ ከተማ 2ለ0 እንዲመራ አሰቻለ።
ከሁለተኛው የወልቂጤ ግብ በኋላ በመልሶ ማጥቃት የተገኘዉን ኳስ የኤሌክትሪኩ አቅሌሲያስ ግርማ ቢሞክርም ኢላማዉን ሳይጠብቅ ቀርቶ ወደ ዉጭ ወጥቷል። የመጀመሪያው አጋማሽም በወልቂጤ ከተማ የ2ለ0 መሪነት ተጠናቋል።
ከዕረፍት መልስ ወደ ጨዋታው ለመመለስ የሞከሩት ኢትዮ ኤሌክትሪኮች ወደ አራት የሚጠጉ ተጫዋቾችን ቀይረዉ ወደ ሜዳ ቢያስገቡም ይህ ነዉ የሚባል የተለየ የግብ ሙከራን እንኳን ማድረግ ሳይችሉ ቀርተዋል።

በአንፃሩ ወልቂጤ ከተማዎች ወጤቱን አስጠብቀው ለመዉጣት በሚመስል መልኩ በራሳቸዉ ሜዳ ኳስን ተቆጣጥረው በቅብብሎሽ ሲጫዎቱ ተመልክተናል። መደበኛው የጨዋታ ሂደት በዚሁ ዉጤት ተጠናቆ በተጨመረው አምስት ደቂቃ ላይ ወልቂጤዎች በበኃይሉ ተሻገር አማካኝነት ግብ አስቆጥረዉ ኢትዮ-ኤሌክትሪክን በድምሩ 3ለ0 በሆነ ዉጤት በማሸነፍ በቀጣይ አመት በሊጉ ከሚሳተፉት ሶስት ክለቦች መካከል ለመሆን የሚረዳቸዉን ወሳኝ ሶስት ነጥብ አሳክተዋል።

አስተያየት ይስጡ