በ19ኛው ሳምንት የሁለተኛ ቀን ውሎ በተደረገው የመጀመሪያ ጨዋታ ከ10ኛ ሳምንት በኋላ ምንም ጨዋታ ማሸነፍ ያልቻለው ድሬዳዋ ከነማ ጅማ አባጅፋርን ከእረፍት መልስ በተቆጠሩ ግቦች 2 – 1 በሆነ ውጤት አሸንፏል ።
ድሬዳዋ ከነማዎች በ18ኛው ሳምንት በቅዱስ ጊዮርጊስ በተረቱበት ጨዋታ ላይ ከነበረው ምርጥ 11 አምሰት ለውጦችን አድርገው ሲገቡ መሳይ ጳውሎስ ፤ አማረ በቀለ ፤ አባይነህ ፊኖ ፤ ሙኽዲን ሙሳ እና ሄኖክ አየለ ፤ ከድር ኸይረዲንን ፤ መሀመድ አብዱለጢፍን ፤ ብሩክ ቃልቦሬን ፤ ዳንኤል ሀይሉን እና ማማዱ ሲዲቤን ተክተው ጨዋታውን እንዲጀምሩ ሲያደርጉ በጅማ አባጅፋር በኩል ደግሞ በሳምንቱ በፋሲል ከነማ ሲረቱ ከተጠቀሙት የመጀመሪያ አሰላለፍ ሁለት ለውጦችን በማድረግ ተስፋዬ መላኩን እና ዳዊት እስጢፋኖስን በወንድማገኝ ማርቆስ እና ሙሴ ከበላ ምትክ በጨዋታውን ላይ አሰልፈዋል ።
የጨዋታው የመጀመሪያ አጋማሽ ያን ያህል ሳቢ ያልነበረ ቀዝቀዝ ያለ የሜዳ ላይ እንቅስቃሴ የታየበት እና የግብ ሙከራ የናፈቀው ነበር ።
ጅማ አባጅፋሮች በተወሰነ መልኩ የኳስ ቁጥጥር ብልጫ ወስደው መጫወት የቻሉ ሲሆን የተጋጣሚያቸውን የኋላ ክፍል ለማስከፈት ግን በእጅጉ ተቸግረዋል ። በአጋማሹ የነበረው ቀዳሚ የግብ ዕድል በእነሱ በከል የተደረገ ሲሆን ሱራፌል አስማማው ለመስዑድ መሀመድ አቀብሎት በፍጥነት ወደ ሳጥን ገብቶ መልሶ የተቀበለውን ኳስ ወደ ግብ ቢልከውም ኢላማውን ሳይጠብቅለት ቀርቷል ።
ድሬዳዋ ከነማዎች በተወሰኑ አጋጣሚዎች በረጃጅም ኳሶች እና በመልሶ ማጥቃት የተጋጣሚያቸውን የኋላ ክፍል ለማለፍ ጥረቶችን አድርገው ነበር ። በ11ኛው ደቂቃ ላይም ከጅማ አባጅፋር ተጫዋቾች የነጠቁትን ኳስ በአባይነህ ፊኖ አማካኝነት ወደ ግብ የላኩት ኳስ በግብ ጠባቂው አላዛር ማርቆስ ሲመለስ እንየው ካሳሁን አግኝቶ በድጋሚ ቢሞክረውም ኳሱ ከግቡ አናት በላይ ወጥቷል ።
ከውሀ እረፍት መልስ እዮብ አለማየሁ ከቀኝ መስመር አቅጣጫ ወደ ግብ ክልል ያሻገረውን ኳስ ቦና አሊ ነፃ ሆኖ አግኝቶ በግንባር የሞከረው ኳስ ወደ ውጪ ወጥቷል ። የመጀመሪያው አጋማሽም ያለ ግብ ተጠናቋል ።
በሁለተኛው አጋማሽ ከመጀመሪያው የተሻለ እንቅስቃሴ የታየበት እና በሁለቱም በኩል ግቦችን የተመለከትንበት ነበር ። የአጋማሹ ቀዳሚ ደቂቃዎች ድሬዳዋ ከነማዎች ጥሩ በመንቀሳቀስ ወደ ተጋጣሚያቸው የግብ ክልል ደጋግመው በመድረስ ነበር የጀመሩት ። በተለይም ተቀይሮ የገባው አቤል ከበደ በግራ መስመር ሲያደርገው የነበረ እንቅስቃሴ ለጅማ አባጅፋር ተከላካዮች ራስ ምታት የሆነ እንዲሁም ለድሬዳዋ ከነማ የግብ ዕድሎችን የፈጠረ ነበር ።
በ54ኛው ደቂቃ ላይም አቤል ከበደ በመስመር ኳሱን እየገፋ ወደ ሳጥን ይዞ በመግባት የቀነሰውን ኳስ ጋዲሳ መብራቴ ከመረብ ማሳረፍ ችሏል ።
ግቡ በተቆጠረ በሰከንዶች ልዩነት ጅማ አባጅፋሮች ጥሩ የግብ ዕድል ፈጥረው የነበረ ቢሆንም የድሬዳዋ ከነማ ተከላካዮች ኳሱን አውጥተውታል ።
የአቻነቱን ግብ ፍለጋ በተለያዩ አቅጣጫዎች ወደ ግብ ክልል ለመድረስ ጅማ አባጅፋሮች ጥረቶችን ያደረጉ ሲሆን በ58ኛው ደቂቃ ላይ ሱራፌል አስማማው ያሻገረው እና ቦና አሊ በግንባር ገጭቶ ሳይጠቀምበት የቀረው ኳስ ለዚህ ተጠቃሽ ነው ።
ድሬዳዋ ከነማዎች ግብ እንዳይቆጠርባቸው በጥሩ መከላከል በመቀጠል አልፎ አልፎም በፈጣን መልሶ ማጥቃት ወደ ጅማ አባጅፋር የግብ ክልል በመድረስ የግብ ሙከራዎችን ማድረግ ችለው ነበር ። 62ኛው ደቂቃ ላይ በዚሁ እንቅስቃሴ ይዘው የሄዱትን ኳስ አቤል ከበደ ከግብ ጠባቂው አላዛር ማርቆስ ጋስ ተገናኝቶ ሳይጠቀምበት ቀርቷል ።
አሰልጣኝ አሸናፊ ከበደ ያደረጉት ቅያሪ ብዙም ሳይቆይ ፍሬ አፍርቶላቸዋል ። ተቀይሮ የገባው ዳዊት ፍቃዱ ሲሆን በ71ኛው ደቂቃ ላይ ከመሀመድኑር ናስር የደረሰውን ኳስ ግብ ጠባቂውን ፍሬው ጌታሁንን በማለፍ ጭምር ከመረብ አሳርፎታል ። ከአራት ደቂቃዎች በኋላም ዳዊት ፍቃዱ ከመስዑድ መሀመድ ጥሩ ኳስ ደርሶት የነበረ ቢሆንም ከዳዊት እግር የሄደው ኳስ ከግቡ በርቀት ሆኖ ወደ ውጪ ወጥቷል ።
የመጨረሻዎቹ አስር ደቂቃዎች ቀዝቅዞ የነበረው የድሬዳዋ ከነማዎች የማጥቃት እንቅስቃሴ ዳግም የታየበት ነበር ። በዚህም 81ኛው ደቂቃ ላይ አቤል ከበደ ፍጥነቱን ተጠቅሞ ወደ ሳጥን ይዞ ገብቶ የቀነሰውን ኳስ ሙኽዲን ሙሳ በአምስት ከሀምሳ ሳጥን ውስጥ ሆኖ ከግቡ አግዳሚ በላይ መቶታል ።
ከስድስት ደቂቃዎች በኋላ ግን ሙኽዲን ሙሳ የሳተውን ኳስ መካሻ እንዲሆነው በቀኝ መስመር አቅጣጫ ወደ ሳጥን ይዞ የገባውን ኳስ ለሄኖክ አየለ ቀንሶለት ሄኖክም በአላዛር ማርቆስ መረብ ላይ በማሳረፍ የምስራቅ ኢትዮጵያ ተወካይ የሆነውን ድሬዳዋ ከነማ አሸናፊ አድርጓል ።
ውጤቱን ተከትሎ ድሬዳዋ ከነማ ነጥቡን 20 በማድረስ ወደ 12ኛ ደረጃ ከፍ ሲል ተሸናፊው ጅማ አባጅፋር በነበረበት 12 ነጥብ እና 15ኛ ደረጃ ለመቆየት ተገዷል ።
በ20ኛ ሳምንት ጨዋታዎች ጅማ አባጅፋር በመጪው ቅዳሜ ቀን 9 ሰዓት ላይ ኢትዮጵያ ቡናን ሲገጥም ከሁለት ቀናት በኋላ ምሽት 12 ሰዓት ላይ ድሬዳዋ ከነማ ከወልቂጤ ከነማ ይጫወታል ።
አስተያየት ይስጡ