የዕለቱ ሁለተኛ ጨዋታ ሰበታ ከነማን ከሲዳማ ቡና አገናኝቶ ለወራት ከሜዳ ርቆ በቅርቡ ሲዳማ ቡናን በተቀላቀለው ባለ ብዙ ልምድ ባለቤት በሆነው ሳልሀዲን ሰዒድ ሶስት ግቦች ሲዳማ ቡና አሸንፎ ወጥቷል ።
ሰበታ ከተማዎች በ18ኛው ሳምንት ጨዋታዎች በኢትዮጵያ ቡና በተረቱበት ጨዋታ ላይ ከነበረው የመጀመሪያ አሰላለፍ ሁለት ለውጦትን በማደረጉ በጌቱ ሀይለማርያም እና ሳሙኤል ሳሊሶ ምትክ አለማየሁ ሙለታን እና ቢያድግልኝ ኤልያስን ሲያረልፉ በሳምንቱ ሀዋሳ ከተማን የረቱት ሲዳማ ቡናዎች በጨዋታው ከነበረው ምርጥ 11 በተመሳሳይ ሁለት ቅያሪዎችን በማድረግ አማኑኤል እንዳለን እና ተመስገን በጅሮንድን ደግፌ አለሙን እና ፍሬው ሰለሞንን ተክተው እንዲገቡ አድርገዋል ።
የምሽቱ ጨዋታ ገና አንድ ደቂቃ እንኳን ሳይሞላው ነበር ግብ ያስተናገደው ። በቅርቡ ሲዳማ ቡናን የተቀላቀለው አንጋፋው እና ውጤታማው አጥቂ ሳልሀዲን ሰዒድ ከሰበታ ከተማው ተከላካይ አንተነህ ተስፋዬ የነጠቀውን ኳስ በመጠቀም ነበር በጨዋታው ላይ ቡድኑን መሪ ያደረገ እንዲሁም በአዲሱ ክለቡ የመጀመሪያውን ግብ ማስቆጠር የቻለው ።
ከግቡ መቆጠር በኋላ ሰበታ ከተማዎች በኳስ ቁጥጥሩ ብልጫ በመውሰድ ወደ ፊት አልፈው የአቻነቷ ግብ ለማግኘት ጥረቶችን አድርገዋል ። በአንፃሩ ሲዳማ ቡናዎች በራሳቸው የሜዳ ክፍል ላይ በቁጥር በርከት ብለው በረጃጅም እና ፈጣን ኳሶች ተጨማሪ ግቦችን ለማስቆጠር ሲታትሩ ቆይተዋል።
በ6ኛው ደቂቃ ላይ ዳዊት ተፈራ ከሳጥን ውጪ ወደ ግብ የመታው ኳስ በግብ ጠባቂው ምንተስኖት አሎ ተመልሷል ።
ምንም እንኳን ሰበታ ከተማዎች ብልጫውን ወስደው ቢጫወቱም የግብ ዕድሎችን በመፍጠሩ ረገድ የተሳካ ጊዜን አላሳለፉም ። ይባስኑም በ29ኛው ደቂቃ ላይ 2ኛውን ግብ አስተናግዱ ።
ቀዳሚውን ግብ ያስቆጠረው ሳልሀዲን ሰዒድ የሁለተኛውም ግብ ባለቤት ሲሆን ከአማኑኤል እንዳለ የደረሰውን ኳስ በመጠቀም ነበር ኳስ እና መረብን ማገናኘት የቻለው ። ሰበታ ከተማዎች በአጋማሹ አንድ ኢላማውን የጠበቀ ሙከራ አድርገው የወጡ ሲሆን በመከላከያው ጨዋታ ላይ በመጨረሻ ሰዓች ግብ አስቆጥሮ አሸናፊ ያደረጋቸው ዴሪክ ንስባምቢ ከጊት ጋትኩት የቀማውን ኳስ አክርሮ በመምታት ወደ ግብ ቢልከውም ግብ ጠባቂው ተክለማርያም ሻንቆ አድኖበታል ። በ40ኛው ደቂቃ ላይ ሰበታ ከተማዎች በማራኪ አንድ ሁለት ቅብብል ካለፉ በኋላ ዱሬሳ ሹቢሳ ወደ ግብ ክልል ያሻገረውን ኳስ ንስባምቢ ለግቡ ቅርብ ሆኖ አግኝቶት የነበረ ቢሆንም የመታው ኳስ ከግቡ አናት በላይ ወጥቷል ። የመጀመሪያው አጋማሽም በሲዳማ ቡና የ2 – 0 መሪነት ተጠናቀቀ ።
በሁለተኛው አጋማሽ ጅማሮ ላይ ሰበታ ከተማዎች የመጀመሪያው አጋማሽ እንቅስቃሴያቸው ያስቀጠሉበት ነበር ። በዚህም 53ኛ ደቂቃ ላይ በፍፁም ገብረማርያም ያደረጉት ሙከራ ኢላማውን ሳይጠብቅ ሲቀር በ66ኛው ደቂቃ ላይ ደግሞ ከማዕዘን ከተነሳ ኳስ ሳሙኤል በረከት ወደ ግብ የላከው ኳስ በተክለማርያም ሻንቆ ተይዟል ።
ሲዳማ ቡናዎች ቀስ በቀስ ወደ ጨዋታው በመመለስ ለረጅም ደቂቃዎች ተወስዶባቸዝ የነበረውን የኳስ ቁጥጥር ብልጫ በአንፃራዊነት በመውሰድ ተጨማሪ ግብ ለማግኘት ጥረቶችን ያደረጉ ሲሆን በ72ኛው ደቂቃ ላይም 3ኛ ግባቸውን አግኝተዋል ። ሀብታሙ ገዛኸኝ ነፃ ሆኖ ከዳዊት ተፈራ ያገኘውን ኳስ ወደ ግብ ሞክሮት ምንተስኖት አሉሎ ሲመልሰው በቅርብ የነበረው ሳልሀዲን ሰዒድ በማስቆጠር ሶስታ መስራት ችሏል ።
በቀጣዮቹ ደቂቃዎች ሲዳማ ቡና ጨዋታውን አቀዝቅዘው የተጫወቱ ሲሆኖ የሰበታ ከነማዎች ጥረት በግብ ሳይታጀብ ጨዋታው በሲዳማ ቡና የ3 – 0 አሸናፊነት ተጠናቋል ።

ውጤቱን ተከትሎ ሲዳማ ቡና ነጥቡን 33 በማድረስ ወላይታ ድቻ በግብ ልዩነት በልጦ 2ኛ ረጀጃ ላይ ሲቀመጥ ሰበታ ከነማ በ12 ነጥብ በሊጉ ግርጌ ላይ ለመቆየት ተገዷል ።
በ20ኛ ሳምንት ጨዋታዎች ሰበታ ከተማ በመጪው እሁድ ቀን 9 ሰዓት ላይ ከወላይታ ድቻ ሲጫወት ሲዳማ ቡና ደግሞ ቅዳሜ ምሽት 12 ሰዓት ላይ ቅዱስ ጊዮርጊስን ይገጥማል ።
አስተያየት ይስጡ