መነሻ ገጽ ባህርዳር ከተማ የጨዋታ ዘገባ | በብዙ ተጠብቆ የነበረው የጣና ሞገዶቹ እና የአፄዎቹ ጨዋታ በአቻ ውጤት ተጠናቋል
ባህርዳር ከተማቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግዜናዎችየጨዋታ ዘገባፋሲል ከነማ

የጨዋታ ዘገባ | በብዙ ተጠብቆ የነበረው የጣና ሞገዶቹ እና የአፄዎቹ ጨዋታ በአቻ ውጤት ተጠናቋል

አጋራ
አጋራ

ተጠባቂው የባህር ዳር ከተማ እና የፋሲል ከተማ ጨዋታ ልክ እንደተጠበቀው ከመጀመሪያው እስከመጨረሻው ደቂቃ ድረስ በግለት ተካሂዶ በበርካታ ጥፋቶች እና ካርዶች ( 8 የቢጫ ካርድ 1 የቀይ ካርድ ) ታጅቦ ያለ ምንም ግብ ተጠናቋል ።

ሁለቱም ክለቦች በሰባተኛው ሳምንት ጣፋጭ ድሎችን ( ባህርዳር 3 – 1 ወላይታ ድቻ ፤ ፋሲል ከተማ 4 – 0 ሲዳማ ቡና ) ባገኙባቸው ጨዋታዎች በቋሚ አሰላለፍ ከተጠቀሟቸው ተጫዋቾች በተመሳሳይ ሁለት ሁለት ቅያሪዎችን በማድረግ ጨዋታውን መጀመር የቻሉ ሲሆን ተጫዋቾቹም በባህርዳር ከተማ በኩል ሰለሞን ወዴሳ እና መሳይ አገኘሁ እንዲሁም በፋሲል ከተማ በኩል ደግሞ ከድር ኩሊባሊ እና በዛብህ መለዮ ናቸው ።

በጨዋታው የመጀመሪያ አጋማሽ ሁለቱም በተለይም በመስመር በሚደረጉ የማጥቃት እንቅስቃሴዎች የግብ ዕድሎችን ለመፍጠር የሞከሩበት ሲሆን ፋሲል ከተማዎች ኳሶቻቸው ከተከላካይ መስመር ጀምረው በመነሳት ወደፊት የሚሄዱ ነበሩ ። በአንፃሩ በባህርዳር ከተማ በኩል የሚነጠቁ ኳሶችን በፍጥነት ከፊት መስመር ለሚገኙት አሊ ሱሌማን እና ኦሴይ ማውሊ በማድረስ የግብ ሙከራዎችን ማድረግ ችለዋል ።

በጨዋታው የመጀመሪያ ሙከራ የተደረገው በኦኪኪ አፎላቢ ሲሆን በ3ኛው ደቂቃ ላይ ከበበረከት ደስታ የደረሰውን ኳስ በሳጥን ውስጥ ገብቶ አክርሮ የመታው ኳስ በግብ ጠባቂው ፋሲል ገብረሚካኤል ተመልሶ የማዕዘን ምት ሆኗል ።
በባህርዳር ከተማ በኩል በተደጋጋሚ ፈጣን ኳሶች ከፊት መስመር ላሉ ተጫዋቾች እየተላኩ ቢሆንም ከጨዋታ ውጪ በመሆን ግን የሚበላሹት በርከት ብለው ነበር ።

18ኛው ደቂቃ ላይ ከቆመ ኳስ ያሬድ ባየህ ለሽመክት ጉግሳ ያሻገረለትን ኳስ በፍጥነት ሮጦ ለማግኘት ቢጥርም ኳሱን በአመቺ ሁኔታ ሳያገኘው በመቅረቱ ወደ ውጪ ወቶበታል ። 26ኛው ደቂቃ ላይ ከሳጥኑ በቅርብ ርቀት አህመድ ረሺድ በበረከት ደስታ ላይ በሰራው ጥፋት ምክንያት የተገኘውን የቅጣት ምት ኦኪኪ አፎላቢ ወደ ግብ ሲሞክረው በፋሲል ገብረሚካኤል ተጨርፎ የግቡን አግዳሚ ገጭቶ ሊወጣ ችሏል ።

በሁለቱም በኩል ጉሽምያዎች እና ተደጋጋሚ ጥፋቶች እያስመለከተ የቀጠለውን ጨዋታ የዕለቱ የመሀል ዳኛ የተቆጣጠሩበት መንገድ በጥሩነቱ ሊነሳ የሚችል ነበር ።
አፄዎቹ በተለይም የመጀመሪያው አጋማሽ መጠናቀቂያ 10 ደቂቃዎች ላይ በይበልጥ ተጭነው በመጫወት የጣና ሞገዶቹን የተከላካይ መስመር ለመፈተን ጥረቶችን አድርገው የነበረ ቢሆንም ወደ ሶስተኛው የማጥቃት ክፍል ከገቡ በኋላ በተደጋጋሚ ኳሶቻቸው ይነጠቁ ነበር እነዚህ የሚነጠቁ ኳሶቸም በጣና ሞገዶቹ ፈጣን ሽግግር ጫና ሲፈጥርባቸው ተስተውሏል ። በዚህ አካሄድ ባህርዳር ከተማዎች 42ኛ ደቂቃ ላይ ያገኙትን ኳስ ፍፁም አለሙ ለአሴይ ማውሊ ያቀበለው ሲሆን በፍጥነት ክፍተት ተጠቅሞ ሲሮጥ የነበረው አብዱልከሪም ኒኪማ ከማውሊ የደረሰውን ኳስ ያሬድ ባየህን በፍጥነት ቀድሞ በሳጥን ውስጥ በመግባት አስቆጠረው ተብሎ ሲጠበቅ የመታው ኳስ ወደ ውጪ ወጥቶበታል ።

በሁለተኛው አጋማሽ ጅማሮ ላይ የጣና ሞገዶቹ በማጥቃቱ ብልጫ በመውሰድ ቢጀምሩም ቀስ በቀስ የጨዋታው የሀይል ሚዛን ወደ አፄዎቹ አመዝኗል ። በአጋማሹ የመጀመሪያው ኢላማውን የጠበቀ ሙከራ የተደረገው በባህርዳር ከተማ በኩል ነበር ።

47ኛው ደቂቃ ላይ ያሬድ ባየህ ኦሴ ማውሊ ላይ በሰራው ጥፋት የተገኘውን የቅጣት ምት ፍፁም አለሙ ወደ ግብ ሞክሮት በግብ ጠባቂው ሚካኤል ሳማኪ ተመልሷል ። ጨዋታውን ቀስ በቀስ መቆጣጠር የቻሉት አፄዎቹ በተደጋጋሚ ወደ ባህርዳር ከተማ የግብ ክልል መድረስ የቻሉ ሲሆን በተለይም ከቀኝ መስመር በሚነሱ ኳሶች የግብ ዕድሎችን ለመፍጠር ያደረጓቸው ጥረቶች በግብ ሙከራዎች የታጀቡ አልነበሩም ።

ለሳምንታት ከሜዳ ርቆ የነበረው የብሄራዊ ቡድኑ እና የአፄዎቹ ወሳኝ ተጫዋች ሱራፌል ዳኛቸው በይሁን እንደሻው ተቀይሮ ከገባ በኋላ የፋሲል ከተማን የማጥቃት ሀይል በማጠናከር ግብ ሊሆኑ የሚችሉ ኳሶችን ለቡድን አጋሮቹ ማመቻቸት ችሎ ነበር ።
80ኛው ደቂቃ ላይ በ26ኛ ደቂቃ በረከት ደስታ ላይ ጥፋት ሰርቶ የማስጠንቀቂያ የቢጫ ካርድ ተመልክቶ የነበረው የጣና ሞገዶቹ አምበል አህመድ ረሺድ በድጋሚ በራሱ በበረከት ላይ በሰራው ጥፋት በሁለተኛ የቢጫ ካርድ ከሜዳ ተሰናበተ ።

በቀሩት ደቂቃዎች ፋሲል ከተማዎች ያገኙትን የቁጥር ብልጫ ተጠቅመው ለግብ የቀረቡ ከአንድም ሁለት ግልፅ የማግባት ዕድሎችን ማግኘት ችለው ነበር ። በበረከት ላይ በተሰራው ጥፋት የተገኘውን የቅጣት ምት ሱራፌል ዳኛቸው ወደ ግብ አሻምቶት አለምብርሀን ማግኘት ቢችልም በግንባሩ የገጨው ኳስ ወደ ውጪ ወቶበታል ። ከሶስት ደቂቃዎች በኋላም በተመሳሳይ ከቀኝ መስመር ሱራፌል ያሻገረውን ኳስ በድጋሚ አሀምብርሀን ከመጀመሪያው በተሸላ ነፃ ሆኖ አግኝቶት አስቆጠረው ተብሎ ሲጠበቅ ከግቡ አናት በላይ ልኮታል ። በአፄዎቹ ፍፁም የበላይነት በቀጠሉት የጨዋታው የመጨረሻ ደቂቃዎች ላይ የባህርዳር ከተማው አጥቂ አሊ ሱሌማን በረጅም የተላከለት ኳስ ከሳጥኑ በግራ አቅጣጫ አግኝቶ ወደ ግብ አክርሮ የመታው ኳስ በግብ ጠባቂው ተመልሶ የማዕዘን ምት ሆኗል ። ሙሉ የጨዋታው ጊዜም ያለ ምንም ግብ 0 ለ 0 በሆነ ውጤት ተጠናቀቀ ።

ውጤቱን ተከትሎም ሁለቱም ክለቦች ባሉበት ደረጃ የቀጠሉ ሲሆን ባህርዳር ከተማ 14 ነጥብ እንዲሁም ፋሲል ከተማ ደግሞ 15 ነጥብ ይዘዋል።

አጋራ

አስተያየት ይስጡ

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

ተዛማጅ ጽሑፎች
ዜናዎችየኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግየጨዋታ ዘገባ

የሊጉ መሪ ሲዳማ ቡና በዝናባማው ጨዋታ በመቻል ሲረታ የጣናው ሞገድም አሸንፏል

እጅግ በከባድ ዝናብ ታጅቦ በተደረገው ጨዋታ መቻል የሊጉን መሪ ሲዳማ ቡናን 3ለ1...

ዜናዎችየኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግየጨዋታ ዘገባ

ሀድያ ሆሳዕና ፣ ፋሲል ከነማ እና ወላይታ ድቻ ወሳኝ ድል አግኝተዋል

በሊጉ የሳምንቱ የሁለተኛ ቀን መርሀግብር ሀዋሳ ከተማ ወደ ሊጉ መሪ የሚጠጋበትን ዕድል...

ዜናዎችየኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግየጨዋታ ዘገባ

ፈረሰኞቹ በድል ሲቀጥሉ ንግድ ባንክ እና ድሬዳዋም አሸንፈዋል

ቅዱስ ጊዮርጊስ ተከታታይ ድሉን ወደ ቋቱ ሲከት ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ከጨዋታ ብልጫ...

ዋልያዎቹዜናዎችየኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን

አንጋፋው አሰልጣኝ በስማቸው የእግር ኳስ ማሰልጠኛ አካዳሚ ሊገነባላቸው ነው

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን የቀድሞ አሰልጣኝ ኢንስትራክተር ሰውነት ቢሻውን ለማመስገን እና ዕውቅና ለመስጠት...