በሰባተኛው ሳምንት የመጨረሻ ቀን ውሎ በቅድሚያ የተገናኙት በመሳይ ተፈሪ የሚመራው አርባምንጭ ከተማ እና በአሸናፊ በቀለ የሚመራው ጅማ አባጅፋር ጨዋታቸውን ያለምንም ግብ አጠናቀዋል ።
በጨዋታው ሁለቱም ክለቦች በስድስተኛው ሳምንት ጨዋታቸው ከተጠቀሙት ቋሚ አሰላለፍ ሁለት ሁለት ቅያሪዎቸን በማድረግ የገቡ ሲሆን ተጫዋቾቹም በአርባምንጭ ከተማ በኩል ፀጋዬ አበራ እና አሸናፊ ተገኝ ሲሆኑ እንዲሁም በጅማአባጅፋር በኩል ደግሞ በላይ አባይነህ እና ማላ ሮጀርን ናቸው ።

በጨዋታው በሁለቱም በኩል በፈጣን ኳሶች ወደ ፊት የመሄድ ፍላጎቶች በግልጽ የታዩበት ነበር ። አርባምንጭ ከተማም ሆነ ጅማ አባጅፋር የሚያገኟቸውን ኳሶች በፍጥነት ወደ ተቃራኒ የግብ ክልል በመውሰድ የማጥቃት ጥረቶችን ያደረጉ ሲሆን ከመስመር የሚነሱ ኳሶችም በብዛት የተስተዋሉበት ነበር ።
12ኛው ደቂቃ ላይ ዱላ ሙላቱ ከመሀል የተሻገረለትን ኳስ ተከላካዮችን በሩጫ አልፎ ለመግኘት ሲሞክር ግብ ጠባቂው ይስሀቅ ወቶ የመለሰበትን ኳስ መሀመድኑር አግኝቶ ለዳዊት ፍቃዱ ቢያቀብለውም ዳዊት ኳሱን ከግቡ አናት በላይ ልኮታል ።

በፈጣን ምልልሶች የቀጠለው ጨዋታ 32ኛ ደቂቃ ላይ አርባምንጭ ከተማዎች ጥሩ ዕድል አግኝተው የነበረ ቢሆንም በረጅም የተላከውን ኳስ የደረሰበት ሀቢብ ከማል በሳጥን ውስጥ ገብቶ ቢሞክረውም ለጥቂት ወደ ውጪ ወቶበታል ። በቀጣዮቹ የመጀመሪያ አጋማሽ ደቂቃዎች የአርባምንጭ ከተማ የበላይነት የታየበት ቢሆንም ወደ ግብ ክልል ይዘዋቸው የሚሄዱ ኳሶች በቀላሉ መክሸፍ ግብ ከማስቆጠር አግዷቸዋል ።
በሁለተኛው አጋማሽም ልክ እንደ መጀመሪያው አጋማሽ ሁሉ በሁለቱም ክለቦች በኩል ወደ ተጋጣሚ የግብ ክልል ለመድረስ የሚደረጉ ፈጣን እንቅስቃሴዎችን ያስመለከተ ነበር ። አርባምንጭ ከተማም ሆነ ጅማ አባጅፋር የአጥቂ ክፍላቸውን ለማጠናከር ሁለት ሁለት ቅያሪዎቸን በማድረግ ነበር የጀመሩት ።

47ኛው ደቂቃ ላይ ተቀይሮ የገባው ምስጋናው መላኩ እና መሃመድኑር ናስር ያደረጉት ጥሩ ቅብብል ሳጥን ውስጥ ለሚገኘው ሙሴ ከበላ ደርሶ አስቆጠረው ተብሎ ሲጠበቅ ወደ ውጪ መቶታል ። ከአንድ ደቂቃ በኋላ የአርባምንጩ 7 ቁጥር አሸናፊ ተገኝ በሳጥን ውስጥ ሆኖ የደረሰውን ኳስ አንድ ተከላካይ አልፎ የሞከረው ቢሆንም ግብ ጠባቂው አላዛር ማርቆስ ለጥቂት መልሶበታል ።
አርባምንጭ ከተማዎች በቀጣዮቹ ደቂቃዎች በኳስ ቁጥጥሩ ብልጫ በመውሰድ የተጫወቱ ሲሆን በጅማ አባጅፋር በኩል በተወሰኑ አጋጣሚዎች በመልሶ ማጥቃት ከመስመር በሚነሱ ኳሶች የግብ ዕድሎችን ለማግኘት ጥረቶችን ያደረጉበት ነበር ።

83ኛ ደቂቃ ላይ ሀቢብ ከማል ከማዕዘን ያሻማውን ኳስ ፀጋነፈዬ አበራ በግንባር ገጭቶ ለማስቆጠር ያደረገው ሙከራ በግቡ አግዳሚ ተመልሶበታል እንዲሁም መደበኛው የጨዋታ ጊዜ ተጠናቆ በተጨማሪ ደቂቃ ላይ ሀቢብ ከማል በሳጥን ውስጥ ያገኘውን ኳስ ወደ ግብ ቢሞክረውም በግብ ጠባቂው ይስሀቅ ተመልሶበት ግብ ሳይሆን ቀርቷል ። ጨዋታውም ግብ ሳያስተናግድ በአቻ ውጤት ተጠናቀቀ ።

ውጤቱን ተከትሎም ነጥቡን 10 ማድረስ የቻለው አርባምንጭ ከተማ በግቦ ክፍያ ተሽሎ ደረጃውን ወደ 8ኛ ከፍ ያደረገ ሲሆን በአመቱ የመጀመሪያ ነጥቡን ያገኘው ጅማ አባጅፋር በ1 ነጥብ ሊጉ ግርጌ ላይ ተቀምጧል ።
አስተያየት ይስጡ