የጨዋታ ዘገባ | አዞዎቹ ከመመራት ተነስተው አዲስአበባ ከተማን አሸንፈዋል

በሊጉ የሁለተኛ ሳምንት በሁለተኛ ቀን የመጀመሪያ ጨዋታ ከከፍተኛ ሊጉ ያደጉትን አዲስ አበባ ከተማን እና አርባ ምንጭ ከተማን ያገናኘ ሲሆን ጨዋታውን አርባ ምንጭ ከተማዎች ከ1 ለ 0 መመራት ተነስተው 2 ለ 1 በሆነ ውጤት አሸንፈዋል ።

በሊጉ የመጀመሪያ ጨዋታ አዲስ አበባ ከተማ በባህር ዳር ከተማ 3 ለ 0 እንዲሁም አርባ ምንጭ ከተማ በመከላከያ 1 ለ 0 በሆነ ውጤት ተሸንፈው የነበረ ሲሆን በመጀመሪያ አሰላለፍ ላይ ከመጀመሪያው ጨዋታቸው በሁለቱም ክለቦች በኩል አምስት አምስት ቅያሪዎች ነበሩ ።

በጨዋታው በአዲስ አበባ ከተማ ቡድን መሪ እና ዋና አሰልጣኙ መካከል በተፈጠረ አለመግባባት ቡድኑ በምክትል አሰልጣኙ የተመራ ሲሆን ዋና አሰልጣኙ እስማኤል አቡበከር በተመልካቾች መቀመጫ ወንበር ላይ ሆነው ጨዋታውን ተከታትለዋል ።

በጨዋታው የመጀመሪያ አጋማሽ ላይ አርባምንጭ ከተማ በተሻለ ተጭነው የተጫወቱ ሲሆን በአዲስ አበባ ከተማ በኩል ከግብ ክልላቸው ጀምረው ኳስን መስርተው ለመውጣት ጥረቶችን ሲያደርጉ ተመልክተናል ። በአጋማሹ በሁለቱም በኩል ጠንካራ ሊባሉ የግብ ሙከራዎች ያን ያህል ያላስመለከተ ሲሆን በመጀመሪያው አጋማሽ መጠናቀቂያ 45ኛ ደቂቃ ላይ ጨዋታው በአዲስ አበባ ከተማ በኩል የመጀመሪያውን ጎል ማግኘት ቻለ ።

ከግራ መስመር ተከላካዩ ያሬድ ሀሰን የተቀበለውን ኳስ ሙሉቀን አዲሱ ከሳጥን ውጪ አክርሮ በመምታት ክለቡን መሪ አደረገ ። ከዕረፍት መልስ በአርባ ምንጭ ከተማ በኩል የተደረጉት ቅያሪዎች ግልፅ የሆነ የሜዳ ላይ ለውጥን አሳይተዋል ። በ56ኛው ደቂቃ ላይ ከወርቅይታደል አበበ የደረሰውን ፍቃዱ መኮንን ከሳጥኑ ውጪ መትቶ በማስቆጠር የጨዋታውን 1 ለ 1 አደረገ ።

ግቧ ከተቆጠረች ሁለት ደቂቃ በኋላ የአዲስ አበባ ከተማው ተጫዋች ሳጥን ውስጥ ኳስ በእጅ በመንካቱ አርባ ምንጭ ከተማዎች የፍፁም ቅጣት ምት አገኙ ። የፍፁም ቅጣት ምቱንም አምበሉ ወርቅይታደል አበበ አስቆጥሮ አዞዎቹ መሪ መሆን ቻሉ ።

ጨዋታው ቀዝቀዝ ብሎ ቀሪዎቹን ደቂቃዎች የቀጠለ ሲሆን አርባምንጭ ከተማዎች በፍቃዱ መኮንን እና በእንዳልካቸው መስፍን ለግብ የቀረቡ ሙከራዎች ማድረግ የቻሉ ሲሆን በመዲናዋ ክለብ በኩል በተለይም በሮቤል ግርማ በኩል ጥሩ የሚባሉ ሙከራዎች ቢያደርጉም ከሽንፈት የታደጋቸውን ግብ ማስቆጠር አልቻሉም ። ጨዋታውም በመሳይ ተፈሪ የሚመሩት አዞዎቹ 2 ለ 1 አሸናፊነት ተጠናቀቀ ።

Writer at Hatricksport

Facebook

Habtamu Mitku

Writer at Hatricksport