በኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ የ20ኛ ሳምንት የመጨረሻ ቀን መርሐግብሮች አስቀድመው 129ኛውን የዓድዋ ድል በዓልን በመዘከር ተደርገዋል።
በዕለቱ ቀዳሚ ጨዋታ የተገናኙት መቻል እና ድሬዳዋ ከተማ ጨዋታቸውን ያለ ግብ በማጠናቀቅ ከድል ጋር እንደተራራቁ ቀጥለዋል።
በጨዋታው መቻሎች የተሻለ የኳስ ቁጥጥር እና የግብ ዕድል መፍጠር ቢችሉም ኳስ እና መረብን ማገናኘት ሳይችሉ ቀርተዋል።
የአሰልጣኝ ገብረክርስቶስ ቢራራው ቡድን የዛሬውን ጨምሮ ባለፉት ስድስት ተከታታይ ጨዋታዎች ማሸነፍ አልቻለም።
- ማሰታውቂያ -
በተጨማሪም ቡድኑ ካለፉት ዘጠኝ ጨዋታዎች በአንዱ ብቻ ያሸነፈ ሲሆን በሶስት ተከታታይ የሊጉ ጨዋታዎችም ግብ ማስቆጠር አልቻለም።
ድሬዳዋ ከተማ በበኩሉ ተከታታይ ዘጠነኛ ድል አልባ የሊግ ጨዋታውን አድርጓል።
በአስረኛው ሳምንት ሳምንት ሲዳማ ቡናን ካሸነፈ በኋላ ሶስት ነጥብ ማሳካት ያልቻለው ድሬዳዋ ከተማ ባለፉት ሰባት የሊጉ ጨዋታዎች ማስቆጠር የቻለው ሁለት ግቦችን ብቻ ነው።
ውጤቱን ተከትሎ መቻል ነጥቡን 28 ሲያደርስ ድሬዳዋ ከተማ በበኩሉ ነጥቡን 21 አድርሷል።
በ21ኛው ሳምንት መርሐግብር መቻል ከወልዋሎ አዲግራት ሲገናኝ ድሬዳዋ ከተማ በበኩሉ የሊጉን መሪ ኢትዮጵያ መድንን ይገጥማል።
በሳምንቱ የመጨረሻ እና በዕለቱ ሁለተኛ መርሐግብር አስቀድሞ ግብ አስቆጥሮ ይመራ የነበረው ቅዱስ ጊዮርጊስ በባህርዳር ከተማ 4 ለ 1 ተረቷል።
በጨዋታው 14ኛ ደቂቃ ላይ ተገኑ ተሾመ ከቢንያም ፍቅሬ የደረሰውን ኳስ ተጠቅሞ ፈረሰኞቹን መሪ ማድረግ ችሎ ነበር።
ግብ ካስተናገዱ በኋላ ከቆሙ ኳሶች በተለይም ደጋግመው ካገኟቸው የማዕዘን ምቶች ቅዱስ ጊዮርጊስን የፈተኑት ባህርዳር ከተማዎች በ39ኛው ደቂቃ ላይ አቻ ሆነዋል።
መሳይ አገኘሁ ከርቀት የተገኘውን የቅጣት ምት በቀጥታ ወደ ግብ ልኮት በቅዱስ ጊዮርጊስ መረብ ላይ አርፏል።
ከዕረፍት መልስ ደግሞ በ61ኛው ደቂቃ ላይ ከማዕዘን ምት የተሻገረን ኳስ ወንደሰን በለጠ አስቆጥሮ ቡድኑን መሪ አድርጓል።
ሁለተኛውን የባህርዳር ከተማ ግብን ያስቆጠረው ወንደሰን በለጠ የቅዱስ ጊዮርጊስ ተከላካዮችን መዘናጋት እና የባህሩ ነጋሽን ትክክል ያልነበሩ ቦታ አያያዞችን በመጠቀም በ83 እና 85ኛ ደቂቃዎች ላይ ሁለት ግቦችን አስቆጥሮ ሀትሪክ በመስራት ቡድኑ 4 ለ 1 እንዲያሸንፍ አስችሏል።
ወንደሰን በለጠ በ2017 ዓመተ ምህረት የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ሀትሪክ የሰራ ቀዳሚው ተጫዋችም ሆኗል።
ውጤቱን ተከትሎ ባህርዳር ከተማ ነጥቡን 29 በማድረስ ወደ 3ኛ ደረጃ ከፍ ሲል ቅዱስ ጊዮርጊስ ወደ 5ኛ ደረጃ ዝቅ ብሏል።
በቀጣይ ሳምንት መርሐግብር ባህርዳር ከተማ ከፋሲል ከተማ እንዲሁም ቅዱስ ጊዮርጊስ ከወላይታ ድቻ ይገናኛሉ።


