የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ የሁለተኛ ዙር ጨዋታዎች በዛሬው ዕለት በአዳማ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ ስታድየም መደረግ ጀምረዋል።
ከቀን 9:00 ጀምሮ የተደረገው የዕለቱ ቀዳሚ ጨዋታ ሀዋሳ ከተማን ከሀድያ ሆሳዕና አገናኝቶ ግብ ሳይቆጠርበት ተጠናቋል።
በሊጉ የደረጃ ሰንጠረዥ ሁለተኛ ላይ የተቀመጠው ሀድያ ሆሳዕና ከመሪው ኢትዮጵያ መድን ያለውን የነጥብ ልዩነት ቢያንስ በጊዜያዊነት የማጥበብ ዕድሉን ሳይጠቀምበት ቀርቷል።
ቡድኑ የዛሬውን ጨምሮ በሊጉ ካደረጋቸው ያለፉት አምስት ተከታታይ ጨዋታዎች በአንድ ብቻ ያሸነፈ ሲሆን ማግኘት ከሚችለው 15 ነጥብ ማሳካት የቻለው አምስቱን ብቻ ነው።
- ማሰታውቂያ -
አሰልጣኝ ሙሉጌታ ምህረትን ዳግም ከሾመ በኋላ የመጀመሪያ የሊግ ጨዋታውን ያደረገው ሀዋሳ ከተማ በበኩሉ የውድድር ዘመኑን ሰባተኛ የአቻ ውጤት አስመዝግቧል።
ውጤቱን ተከትሎ ሀድያ ሆሳዕና ነጥቡን 31 በማድረስ በሁለተኛ ደረጃ ሲቀጥል ሀዋሳ ከተማ በበኩሉ ነጥቡን 16 በማድረስ በጊዜያዊነት ወደ 15ኛ ደረጃ ከፍ ብሏል።
በ21ኛው ሳምንት መርሐግብር ሲዳማ ቡና ከሀድያ ሆሳዕና እንዲሁም ሀዋሳ ከተማ ከመቀሌ 70 እንደርታ ይገናኛሉ።
በዕለቱ ሁለተኛ መርሐግብር ከአመሻሽ 12:00 ጀምሮ በተደረገው የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ እና መቀሌ 70 እንደርታ ጨዋታ የዓምናው ሻምፒዮን 1 ለ 0 አሸንፏል።
በጨዋታው ሳይመን ፒተር በ21ኛው ደቂቃ ላይ ያስቆጠረው ግብ ንግድ ባንክን አሸናፊ ለማድረግ በቂ ሆኗል።
ሳይመን ፒተር ያስቆጠረው ግብ አዲስ ግደይ ከማዕዘን ያሻገረውን ኳስ በመጠቀም በግንባር ከመረብ ያሳረፈው ነው።
በውድድር ዘመኑ እምብዛም በተጠበቀው ልክ ያልሆነው ንግድ ባንክ የዓመቱን ሰባተኛ የሊግ ድል ያስመዘገበ ሲሆን ካለፉት አራት ጨዋታዎች ማግኘት ከነበረበት 12 ነጥቦች 10 ማሳካት ችሏል።
ውጤቱንም ተከትሎ ንግድ ባንክ ነጥቡን 25 በማድረስ ደረጃውን በጊዜያዊነት ወደ 8ኛ አሳድጓል።
መቀሌ 70 እንደርታ በበኩሉ በውድድር ዓመቱ ለሁለተኛ ጊዜ ተከታታይ ሽንፈትን አስተናግዷል።
ቡድኑ በአዳማ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርስቲ ስታድየም ባደረጋቸው የመጀመሪያ ስድስት ጨዋታዎች ያለ ሽንፈት መጓዙ አይዘነጋም።
በፋይናንስ ተቆጣጣሪ ኮሚቴው ቅጣት ከተጣለባቸው ክለቦች አንዱ የሆነው መቀሌ 70 እንደርታ ባለፉት 10 የሊጉ ጨዋታዎች አምስት ግቦችን ብቻ ያስቆጠረ ሲሆን በአንፃሩ ያስተናገደውም አምስት ግቦችን ነው።
22 ነጥቦችን የሰበሰበው የአሰልጣኝ ዳንኤል ፀሐዬው ቡድን በነበረበት 13ኛ ደረጃ ለመቆየት ተገዷል።
በቀጣይ ሳምንት መርሐግብር መቀሌ 70 እንደርታ ከሀዋሳ ከተማ እንዲሁም ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በበኩሉ ከስሁል ሽረ ይጫወታል።


