የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ 19ኛ ሳምንት የሁለተኛ ቀን ጨዋታዎች በዛሬው ዕለት ሲደረጉ ኢትዮጵያ ቡና እና ሀድያ ሆሳዕና ድል ቀንቷቸዋል።
በቀዳሚው ጨዋታ መቻልን የገጠመው ኢትዮጵያ ቡና አንተነህ ተፈራ በ49ኛው ደቂቃ ላይ ባስቆጠረው ብቸኛ ግብ 1 – 0 አሸንፏል።
የመቻል ተከላካዮች አለመረጋጋት ፤ የአማኑኤል እና ዲቫይን ጥረቶች ከአንተነህ ድንቅ አጨራረስ ጋር ተደምረው ግቡ እንዲቆጠር አስችሏል።
ባለፉት ተከታታይ ስምንት የሊግ ጨዋታዎች ሁለት ግቦችን ብቻ ያስተናገደው የቡናማዎቹ የተከላካይ ክፍል ብቸኛዋን ግብ አስጠብቆ ሶስቱን ነጥቦች ይዞ መውጣት ችሏል።
- ማሰታውቂያ -
የአሰልጣኝ ገብረክርስቶስ ቢራራው ቡድን ሊጉ ወደ አዳማ ሲመጣ መሪ የነበረ ቢሆንም አዳማ ላይ ካደረጋቸው ሰባት የሊጉ ጨዋታዎች ማሸነፍ የቻለው በአንድ ብቻ ነው።
እንደ ሽመልስ በቀለ እና ምንይሉ ተሾመ አይነት ሁነኛ የማጥቃት ሂደቱ ተዋናዮችን በጉዳት ምክንያት በጨዋታው ያልተጠቀሙት አሰልጣኙ ፊት መስመር ላይ ያለው አለመረጋጋት እና የሚገኙ ዕድሎች አለመጠቀም ዋጋ እንዳስከፈላቸው ተናግረዋል።
ውጤቱንም ተከትሎ ኢትዮጵያ ቡና ነጥቡን 26 ያደረሰ ሲሆን መቻል በ27 ነጥቦች በነበረበት ለመቆየት ተገዷል።
በሁለተኛው ዙር ቀዳሚ ሳምንት ጨዋታዎች ኢትዮጵያ ቡና ከስሁል ሽረ እንዲሁም መቻል ከድሬዳዋ ከተማ ይጫወታሉ።
በዕለቱ ሁለተኛ መርሐግብር ከአመሻሽ 12:00 ጀምሮ በመሪነት ተርታ የሚገኙትን ሀድያ ሆሳዕና እና ቅዱስ ጊዮርጊስን ያገናኘው ጨዋታ በሀድያ ሆሳዕና አሸናፊነት ተጠናቋል።
በተመሳሳይ የ1 – 0 ውጤት በተጠናቀቀው ጨዋታ አምበሉ ሔኖክ አርፊጮ በ61ኛው ደቂቃ ላይ ከቅጣት ምት ያስቆጠረው ኳስ ቡድኑን አሸናፊ አድርጓል።
በተከታታይ ሁለተኛ ጨዋታ ላይ ከቆመ ኳስ ግብ ያስቆጠረው ሔኖክ በልምምድ ቦታ ላይ በሚገባ ሰርተን የመጣነው ነው ሲል ስለ ግቡ ተናግሯል።
ከሶስት ጨዋታዎች በኋላ ወደ ድል የተመለሰው ቡድኑ ነጥቡን 30 በማድረስም የሁለተኛ ደረጃን ከተጋጣሚው ቅዱስ ጊዮርጊስ ተረክቧል።
በውድድር ዓመቱ አዳማ ላይ የመጀመሪያ ሽንፈቱን ያስተናገደው ቅዱስ ጊዮርጊስ ከመሪው ኢትዮጵያ መድኅን ለመጠጋት የሚያስችለው ዕድል ዳግም ሳይጠቀምበት ቀርቷል።
ቡድኑ የሁለተኛ ደረጃውን ለሀድያ ሆሳዕና አስረክቦ በነበረበት 29 ነጥብ ላይ የሚቆይ ይሆናል።
በ20ኛው ሳምንት ጨዋታዎች ሀድያ ሆሳዕና ከሀዋሳ ከተማ እንዲሁም ቅዱስ ጊዮርጊስ ከባህርዳር ከተማ ይጫወታሉ።


